TG
በሰላም ስምምነቱ መሰረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋሚያ ኮንፈረንስ በዚህ ሳምንት ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።
በኮንፈረንሱ የተለያዩ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ተገልጿል።
የኮንፋረንሱ ውክልልና አስተዳደር፣ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ተልዕኮ፣ የአስተዳደሩ አደረጃጀት እና የስልጣን ክፍፍል ላይ ውይይት እንደተደረገበት እና ስምምነት ላይ እንደተደረሰባቸው ተገልጿል።
ወደ ጦርነት ያስገቡ የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በሰላም ምላሽ እንዲያገኙ ሁሉም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተመላክቷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በሁለቱም ተደራዳሪዎች ስምምነት ፀድቆ ወደ ተገባር የሚገባ ሲሆን አስተዳደሩ ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት ይቆያል ተብሏል።
ኮንፈረንሱ 11 ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ በማውጣት የተጠናቀቀ ሲሆን የትግራይ ህዝብ ፍላጎት የሚሟላበት፣ የጦርነት ሰለባዎች ትኩረት የሚያገኙበት፣ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው የሚመለሱበት፣ በትግራይ ያጋጠሙ ሁለንተናዊ ችግሮች የሚፈታ እንዲሆን ሁሉም ለሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቁን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ጀነራል ታደሰ ወረደ ከቀናት በፊት ኮንፈረንሱ ሲካሄድ እንደተናገሩት ከሆነ የሚቋቋመው ጊዚያዊ አስተዳደር ፦
👉 30 ከመቶ ከህወሓት፣
👉 25 ከመቶ ከትግራይ ታጣቂ ሐይሎች፣
👉 30 በመቶ የሲቪል ተቋማት
👉 15 በመቶ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የያዘ ነው።
ለሁለት ቀናት ከተደረገው ኮንፈረንስ ጋር በተያያዘ ከዓሲምባ በስተቀር በክልሉ ያሉ የተቃዋሚ ኃይሎች እንዳልተካፈሉ በስፋት ተነግሯል።
ለአብነት ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ጊዚያዊ አስተዳደር የማቋቋም ሂደቱ አሳታፊነት፣ ሕጋዊነት እና ተቀባይነት ላይ ጥያቄ በማንሳት ራሱን ከሂደቱ ማግለሉን አስታውቆ ነበር።
የጊዚያዊ አስተዳደር አቋቋሚ ኮሚቴው ፤ የፕሪቶርያው ስምምነት የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት ጊዚያዊ አስተዳደር ያቋቁማሉ እንደሚል፤ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትም ፥ " ጊዚያዊ አስተዳደር አቋቁሙ፣ በተቋቋመው ላይ ሀሳብ እንሰጣለን " ማለቱን ገልጾ " ህወሓት በራሱ ውሳኔ አካታች ለማድረግ ጥረት ማድረጉን በተቃዋሚዎች ዘንድ ለሚነሳው ትችት ምላሽ መስጠቱን ከዶቼ ቨለ ሬድዮ ጣቢያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።