Speed limit
በመዲናዋ የፍጥነት ገደብ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጅ በመተግበሩ ከፍተኛ ፍጥነት በ10 በመቶ ቀንሷል
በአዲስ አበባ የፍጥነት ገደብ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጅ (ራዳር) በመተግበሩ ከፍተኛ ፍጥነትን በ10 በመቶ መቀነስ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ 70 በመቶ የሚሆኑት የትራፊክ አደጋዎች መንስኤ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር መሆኑ ይነገራል፤ በአደጋው ከሚሞቱት ውስጥም ከ80 በመቶ በላይ እግረኞች ናቸው።
አደጋዎችን ለመቀነስም የፍጥነት ወሰን መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጅን ተደጋጋሚ አደጋ በሚደርስባቸው አካባቢዎች በ2010 ዓ.ም ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን፥ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅሬኛ ሂርጳ ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም መንገዶችን በአራት ደረጃ በመለየት ከፍተኛው የፍጥነት ልክ በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በቀለበት መንገዶች ላይ በሰዓት 70 ኪሎ ሜትር እንዲሆን ተወስኗል።
አሁን ላይም በከተማዋ ለከፍተኛ ፍጥነት ተጋላጭ ናቸው በተባሉ አካባቢዎች በ5 ሚሊየን ብር ወጪ የተገዙ 21 የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን በመጠቀም የተሽከርካሪዎችን ፍጥነት የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
መሳሪያዎቹ ከ30 እስከ 180 ሜትር ባለ ርቀት ክልል ውስጥ የፍጥነት ወሰንን መቆጣጠር የሚያስችሉ ሲሆን፥ በተጠናቀቀው በጀት አመት 122 ሺህ አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ሲያሽከረክሩ ተገኝተው ተቀጥተዋል።
እንደ ኤፍ ቢሲ ዘገባ ከዚህ ቀደም በከተማዋ ከሚገኙት አሽከርካሪዎች መካከል 49 በመቶዎቹ ከፍጥነት በላይ ሲያሽከረክሩ የነበረ ሲሆን፥ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያው መተግበር ከጀመረ ወዲህ ግን ይህ አሃዝ ወደ 39 በመቶ ዝቅ ማለቱንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከትራፊክ ደህንነት ጋር ተያይዞ በተደረገ ጥናት የአሽከርካሪዎችን ፍጥነት በ5 በመቶ መቀነስ ቢቻል የትራፊክ አደጋን 20 በመቶ መቀነስ እንደሚቻልም ጠቅሰዋል።
@YeneTube @FikerAssefa