Sheger FM
በሶስት ክልሎች ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵካ በተደረገ የሰላም ልኬት የናሙና ጥናት የክልሎቹ ተወላጆች በሌላ ክልል ተወላጆች ላይ ያላቸው እምነት 14 በመቶ ብቻ መሆኑ ተጠቁሟል።
የክልሎቹ ጎሳዎች / ተወላጆች እርስ በእርስ ያላቸው እምነት 48 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።
በሶስቱም ክልሎች 801 ሰዎችን ፣ 101 የቀበሌ አስተዳደሮችን እና 101 የሀገር ሽማግሌዎችን በናሙናነት ተወስደዋል።
ጥናቱ እንዲካሄድ ያደረጉት የሰላም ሚኒስቴር ከኢንተርፒስ በጋራ ሆነው ነው።
በዚሁ ጥናት ፤ የኢትዮጵያ ሰላም ጥናት ልኬት (Peace Index) በሶስቱ ክልሎች ከአስር ፤ 6.7 እንደሆነ ተመላክቷል።
በግለሰብ በቤተሰብ፣ በህብረተሰብ እና በወሰን መካከል ያለው የሰላም ልኬት ውጤት ይለያያል ተብሏል።
ጥናቱን ያቀረቡት ተመራማሪ ፤ ሙሉ ተካ ፤ " መለኪያው ከ0 - 10 ነው ፤ በግለሰቦች ውስጥ ያለው ሰላም 8.1 ነው። በቤተሰብ ጋር 7.1 ነው። ማህበረሰብ ጋር 6.3 ነው ፤ በአካባቢ ድንበሮች 5.4 ነው " ብለዋል።
እነዚህ ሶስቱ ክልሎች በአንፃራዊነት ሰላማዊ የነበሩ እና ሆነው የቆዩ ክልሎች ናቸው ነጥባቸው ግን ትልቅ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ አሁን የተመዘገበው ውጤት የአንድ ችግር አለመላካች ነው ያሉ ሲሆን " የጥናቱ አንድምታ አሁን መተንተን አይቻልም። መጠንቀቅ አለብን ከዚህ አንድምታውን እና ድምዳሜውን መስጠት አቸጋሪ ነው ፤ ይሄ ጥናት መነሻ ነው " ብለዋል።
በሶስቱ ክልሎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በሌላው ጎሳ ላይ ያላቸው እምነት 14 በመቶ፣ በሌል ሃይማኖት ላይ ያላቸው እምነት 14 በመቶ እና በሌሎች ክልሎች ላይ ያላቸው እምነት 13 በመቶ ብቻ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።
ክልሎቹ ምን አሉ ?
የሲዳማ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ አሰፋ ፦
" ሲዳማ ከራሱ ይልቅ ሌላውን ብሔር ይወዳል።
ይሄ ጥናት ከዚህ በፊት የነበሩ እንደሀገር ከለውጡ ማግስት ወዲህ ያለው አለመረጋጋት ነበር በዛ መነሻ በእኛ አካባቢም የተወሰኑ ግጭቶች ነበሩ።
ከዚህ በፊት የተጠኑ ጥናቶች ይሆናሉ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ይሄን አያመላክትም። አብሮነት ሲዳማ ከየትኛውም ወገን ፣ ከጉርብትና ፣ በጋብቻ የተሳሰረ ነው ለምሳሌ ከደቡብ፣ ከወላይታ ፣ ኦሮሚያ ጋር በጋብቻ የተሳሰረ ነው።
ከዛም አልፎ አብረው የሚኖሩ ህዝቦች ከሀዋሳ ጀምሮ ትልልቅ ከተሞች ላይ የትኛውም ብሄር አብሮ የሚኖር ነው። አቃፊ ህዝብ ነው። "
የደቡብ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ የሰላም ግንባታና ብዝሃነት አያያዝ ዘርፍ ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ፦
" ጥናቱ ያላለቀለት ነው።
የመጀመሪያ የሙከራ ደረጃ ጥናት ነው ይፋ የተደረገው።
አጠቃላይ ጥናቱ ላይ ያሉ አንዳንድ ከሌላው ጋር የመጋባት ፣ ከሌላው ጋር የመኖር ችግር የለበትም ፣ ከሌሎች ማህበረስብ ጋር ተቀላቅሎ ይኖራል ፣ ውስጡም ያኖራል ሄዶም ከሌላው ጋር ይኖራል። ይሄ አንዱ መሰረታዊ የደቡብ መገለጫ ነው።
ጥናቱ ላይ ውስንነት ነበር። ምናልባት የመረጃ አሰባሰብ ወቅት ላይ የጥናት ቡድን የተሰማራው ሲሰበስብ የተወሰነ ክፍተት እናዳለ ተሰምቶናል። የዳታ ችግር አለ ብለን አስተያየት ሰጥተናል።
በቀጣይ የመጨረሻው ጥናት ሲወጣ ይስተካከላል የሚል እምነት አለን። "
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገብረማርያም ሰጠኝ ፦
" በተጨባጭ በምንሰራው ስራ ስናይ ፤ ከብሄር ብሄረሰቦች ጋር ተከባብሮ በመኖር በኩል ብዙ የጎላ ችግር አለ ብዬ አልልም።
የተወሰኑ ከዚህ ቀደም በሸካ ዞን ቴፒ አካባቢ የነበሩ የቆዩ ግጭቶች ጋር ተያይዞ የመገፋፋት ሁኔታዎች ነበሩ እነዚህን ክልሉ ከተመሰረተበት ከ2011 ህዳር ወር ጀምሮ በሰራናቸው ስራዎች አንፃራዊ ሰላም መጥቷል ቴፒ አካባቢ አሁን ክልሉም አንድ የክላስተር ማዕከል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሻለ ለውጥ እየመጣ ነው በቀጣይ የምንሰራው እንደተጠበቀ ሆኖ ለውጥ አለ።
ሌሎች አካባቢዎች ላይ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ተከባብሮ በመኖር ብዙ የጎላ ችግር የለም። ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው ቤች ሸኮ ጉራ ፈርዳ ወረዳ አካባቢ በተለይ ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሄዶ እዛ የሰፈሩ ነበሩና ከእነዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ወቅት የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ አሁን ባለው ሁኔታ ከእነዚህ ጋር ተያይዞ የጎላ ችግር የለም።
እርስ በእርስ ካሉን ነባር ብሄረሰቦች ጋር በቀጣይ በምንሰራቸው ስራዎች ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ካልሆኑ በስተቀር ሌላውን በመግፋት በኩል ችግር አለ ብዬ አልወስድም። "
የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው ፤ እንዲህ አይነት ጥናት በሁሉም ክልሎች ተጠንቶ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ያሉ ሲሆን እንዲህ አይነት ጥናት መደረጉ ችግሮችን በግምት ከመለየት ይልቅ ሳይንሳዊ በመሆነ መንገድ በመለየት መፍትሄ ለመስጠት ይረዳል ሲሉ አሳውቀዋል።
(ሸገር ኤፍ ኤም 102.1)