SHINCHEONJI - የኮርያዎች መጽሀፍ ቅዱስ ጥናት

SHINCHEONJI - የኮርያዎች መጽሀፍ ቅዱስ ጥናት

በናሆም ሙሉነህ ተዘጋጀ @BenChabod

የምንከተለውና የዳንንበት ወንጌል በዘመናት መካከል ተግዳሮት ጠፍቶትና ከትግል ውጪ ሆኖ የሚያውቅበት ታሪክ የለም። በየወቅቱ ከውስጥና ከውጪ በሚነሱ የስህተት ትምህርቶችና ተቃውሞዎች ሳቢያ በየዘመናቱ ራሱን ሲከላከልና በተነሱበት ተቃውሞዎች ሁሉ እያሸነፈ ያለንበት ዘመን ላይ ደርሷል። አሁንም በተለይም ከተሀድሶ ዘመን በኋላ ለመቁጠር በሚታክቱ አያሌ የውጭና የውስጥ ተግዳሮቶች መካከል እያለፈ ሲሆን በተለይ ከውስጥ በሚነሱና ሰይጣን አስርጎ ባስገባቸው የወንጌሉ ጠላቶች ሳቢያ ቤተ ክርስቲያን ስትታመስ ኖራለች። በእኛም ዘመን በተለይ ከብልጽግና ወንዴል ጋር ተያይዞ አሌ የማይባሉ የምንፍቅና ትምርቶች የገቡ ሲሆን ከዚህ ቀጥሎ የምናየው የ Shincheonji ትምህርት ደግሞ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ ለየት ብሎ ብዙም ትኩረት ሳይፈልግ በቀላሉ ሊታያ በሚችልበት ሁኔታ ትምህርቱን እያስፋፉ ይገኛል።

በርግጥ ይህ አስተምህሮ በጣም ግልጽ የሆነ ከወንጌሉ ያፈነገጠ ትምህርት ቢሆንም እንኳ በጣን በሆነ ሁኔታ የምንፍቅና ሥራውን እያቀላጠፈ ያለና እየተጠቀሙበት ካለው አካሄድ የተነሳም (Technical Strategy) ሰዎቻችን በተለይም አዳጊ ወጣቶች እና ወጣቶችን በከፍተኛ ቁጥርና ፍጥነት በመማረክ ላይ ይገኛል።


ወደ አስተምህሮው እንግባ

Shincheonji በደቡክ ኮሪያ የተነሳ የስህተት ትምህርት ሲሆን አስተማሪው ደግሞ ሊ ማን-ሂ (Lee Man-Hee) የተባለ ግለሰብ ንወ። እንግዲህ ይህ ግለሰብ በደቡብ ኮርያ ብቻ ከ 200,000 በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን በ Korea domain line church ወይንም በቀደምት ጉምቱ የወንጌላውያን አማኞች የተወገዘና ትምህርቱ በቀጥታ የስህተትና የምንፍቅና እንደሆነ የተተቸ ትምህርት ሆኖ እናገኘዋለን።

የትህምርቱ ዋና ገጽታም ከታረደው በግ ከክርስቶስ ውጪ ማዕከልነቱን ወደ ምንፍቅናው ደራሲ ወደ ሊ ማን-ሂ ያደላ መሆኑ በግልጽ ከትምህርቶቹና ከአቋሞቹ መረዳት ይቻላል።

ይህ ሰው (ሊ ማን-ሂ) ራሱን ዳግም የተገለጠ ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሆነ በግልጽ የሚያስተምርና የራሱንም የታደሰና እንደሚመቸው አድርጎ የተስተካከለ መጽሀፍ ቅዱስ (በተለይ በዮሐንስ ራዕይ ላይ) እስከ ማሳተም የደረሰ በቅዱስ ቃሉ ስልጣን ላይ የተዳፈረ ሰው ነው።

ለዚህም በማሳያነት ራሱን ዳግም የተገለጠ ዮሐንስ (አዲሱ ዮሐንስ) አድርጎ ከመቁጠሩ ጋር በተያያዘ ዮሐንስ ራዕይ ዳግም በሙላት ተገልጦልኛል በማለትና በዮሐንስ ራዕይ 1 - 3 ያሉት በእስያ ያሉት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የእስያ ሳይሆኑ በኮርያ ለሚገኙ ከተሞች ናቸው ማለት አስተካክሎ የራሱን መጽሀፍ ቅዱስ አስትሟል። ያም ከተማ በዋናነት Gwa-Cheon የምትባል ለሰሜን ኮርያ የቀረበች ከተማ ስትሆን የአስተምህሮ ተቋሙ ዋና መቀመጫ ናት።


ትምህርቶቹ በጥቂቱ

ከሰውዬው ማንነት አንጻር

1. ከላይ እንደተገለጸው ሊ ማን-ሂ ራሱን ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን ያስተምራል ወይንም አዲሱ ዮሐንስ እያለ ራሱን ያቆላምጣል (Fact 52)

  • ይህ ትምህርት ፈጽሞ በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ የሌለና ሰዎች ዳግም ሌላ ሰው ሆኖ ይወለዳሉ ለሚለው የህንድ(ሁድሃ)፣ የጥንት ቻይናና፣ የጥንት ግሪኮች ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የዳግም ስጋ ውልደት ትርክት ነው።

2. ሊ ማን-ሂ አዲሱ ዮሐንስ ነኝ እንደማለቱ የዮሐንስ ራዕይን "እውነታ" እንደተቀበለ ያስተምራል (Fact 43, Exposition III-2, 71) ይህም ልክ አይደለም ብሎ ያመነበትን የዮሐንስ ራዕይ ክፍል እንዲያወጣና በራሱ ሃሳብ እንዲተካ ነጻነትን ለራሱ አጎናጽፎታል።

  • ይህ ሰው ዘርፈ ብዙ ስህተቶች የሚታይበት ቢሆንም የቃሉን ስልጣን የዳሰበት ግን ሰፊውን ድርሻ ይይዛል። ራዕይ መጽሐፍን ራሱ ራዕም መጽሐፉ ማንም እንዳይጨምርበትም ሆነ እንዳይቀንስበት ቆልፎ ያስቀመጠና ማንም ልሰርዝ ልደልዝ ቢል እግዚአብሔር የተገለጹትን እርግማኖች ኣንደሚያወርድበት ቢናገርም ይህ ሰው ይህንን በመተላለፍ አያሌ ስህተቶችን በመጽሐፉ ላይ ሲሰራ እናገኘዋለን። የዚህም ነገር መጨረሻ ጥፋት መሆኑ ከማንም ያልተሰወረ ሀቅ ነው።

3. በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 2፥26-27 ላይ የተገለጸውና ሕዝቡን በብረት በትር ይገዛል የተባለው ለእርሱ (ሊ ማን-ሂ) የተጻፈ ቃል እንደሆነ ያስተምራል።

  • ክፍሉ ድል ለሚነሳው ተብሎ ለትያጥሮን የተጻፈውን ቃል እንደፈለገ ለራሱ ፍላጎት ለመተርጎም የሚታትር ግልብ ሀሳኢ መሆኑን እንረዳለን።

4. በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 12፥1-9 ባለው ክፍል ላይ የተገለጸችው ሴት ታሪክ ከሴቲቱ የተወለደውና(ቁ5) ዘንዶው ሊውጠው በተዘጋጀ ጊዜ(ቁ4) ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የተነጠቀው(ቁ5) የያኔው ህጻን ያሁኑ ሊ ማን-ሂ መሆኑን በድፍረትና ያለ ምንም ፈሪሃ እንግዚአብሔርም ሆነ አክብሮተ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል።

  • ይህ ሰው በአጭር አገላለጽ በ 2ጴጥ 1:20 ያለውን "ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤" የሚለውን ክፍል ወይ አላነበበውም አልያም ሊቀበለው አልፈቀደም ማለት ነው።

5. የእርሱ (ሊ ማን-ሂ) ንግግር አጽናኝና የመንፈስ ቅዱስ ቃል መሆኑን ይናገራል (Exposition 18)

  • በርግጥ ቃሉ እኛ እግዚአብሔር እኛን ባጽናናበት መጽናናት ሌሎችን እንደምናጽናና ይገልጻል (2ቆሮ 1:4) ይሁንና ግን አጽናኝ ተብሎ የተገለጸው የየትኛውም የሰው ልጅ የሌለና ክርስቶስ ራሱ የመሰከረለት ቅዱስ መንፈሱ ብቻ መሆኑን እንረዳለን።(ዮሐ 14:15-16, 26, 15:26) በዚህም ይህ ሰው የመንፈስ ቅዱስን ድርሻ ለመውሰድ ያልፈራና ራሱን በመንፈስ ቅዱስ ስፍራ ያስቀመጠ ደፋር አስተማሪ ሆኖ እናገኘዋለን።

ከድኅነት(Salvation) አንጻር

ይህ ሰው ከድኅነት አንጻር ራሱን በወንጌሉና በክርስቶስ ስፍራ ያስቀመጠ ራሱን የመዳን መንገድ አድርጎ የሚቆጥር ሰው ነው። ለአበይትም ከንግግሮቹ ከተወሰዱት መካከል፦

  1. ዘፍ 2:9 ላይ የተቀመጠው የሕይወት ዛፍ በመባል የተገለጠው ሕይወት ሰጪ ራሱ ሊ ማን-ሂ መሆኑን ያስተምራል (Exposition 57) ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሊ ማን-ሂ ራሱን የእግዚአብሔር መንግስት የሕይወት ዛፍ እያለም ይጠራል (Exposition 11, 57)
  2. ከ ሊ ማን-ሂ ውጪ መዳን፣ ዘላለማዊ ሕይወትም ሆነ መንግስተ ሰማይ አለመኖሩን በግልጽ ያለ አንዳች መስቀቅ ያስተምራል። (Exposition 195)
  3. በክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ጊዜ ጻድቅ የሆነውና የሚድነው አሁን ክርስቶስ "በመንፈስ" እንደመጣ (Already come) የሚያምን ብቻ ነው ይላል። (Exposition III-2, 26)
  • ይህ ትምህርት የክርስቶክ ምፅዓት ከሆነ ዕንደቆየና አሁን የምንጠብቀው ክርስቶስ እንደሌለ መናስተማር አማኞችን የጌታቸውን መምጣት ከመናፈቅ እንዲናጥቡ የሚያደርግ ሲሆን አሁን ክርስቶስ መጥቶ በኮርያ ውስጥ እንደሚገኝ ለሚያስተምሩት ትምህርት መሰረትን ያስጥልላቸዋል።
  • ክርስቶስ ሲመጣ እንዲህ በድብቅ ሳይሆን በግልጽና በገሀድ የወጉት ሁሉ እያዩት(ራዕይ 1:7) በታላቅ ክብር በታላቅ ክብርና በመላዕ አጀብ እንደሚመጣ(1ተሰ 4:16)፤ የመምጣቱም ቀን እንዳሁኑ መንደላቀቅና አለማዊ አትኩሮት ባለበት እየቀጠለ ሳይሆን ላላመኑበት ታላቅ ጭንቅና ተራሮች ሆይ ውደቁብን የሚያሰኝ የታላቅ ምጥ ቀን መሆኑን ቃሉ ያስተምረናል።(1ተሰ 5:3)

4. በክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ጊዜ ሊ ማን-ሂ እውነት፣ ሕይወትና መንገድ እንደሚሆን በድፍረት ያስተምራል (Exposition III-2, 11)

  • የዚህ ሰው ድፍረት ልክ ያጣና ክርስቶስ ራሱን "እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።" ዮሐ 14:6 ብሎ የገለጸበትን ሃሳብ የመዳን ብቸኛ መንገድነቱንና አዳኝነቱን ያሳየበትን ሃሳብ ይህ ሰው እንደቀላል ሲዘርፍና ለራሱ ስም ሲለጥፍበት የማይፈራ ሰው ነው። በዚህም ራሱን ከክርስቶስ ጋር ለማላከክ የሞከረ አስተምሮን የያዘ ነው።

ከቤተ ዕምነት አንጻር

  1. በደምሳሳው የኦርቶዶስ፣ የኦርቶዶስ ፕሮቴስታንት ኣንዲሁም የፕቶቴስታንት አስተማሪዎች ለሰይጣን የተገቡ (Belongs to Devil) እንደሆኑ ያስተምራል (Exposition 297)
  2. በተጨማሪም በዮሐንስ ራዕይ 14፥1፣3 ላይ የምናገኘው በጽዮን ተራራ ስለተሰበሰቡት ከ አስራ ሁለቱ ነገዶች የተውጣቱ 144 ሺህ ሰዎች የሚናገረውን ሃሳብ ኣነዚህ 144 ሺህ ሰዎች የእርሱ ተከታዮች አልያም የ Schincheonji አስራ ሁለት ነገዶች ኣንደሆኑና እነርሱም የቅዱስ ሕዝብና የንጉስ ካህናቶች "እንደሚሆኑ" ያስተምራል። (Exposition III-1, 193, 4)
  • ይህ ክፍል ከምድር ሁሉ ስለተዋጁና በጉን የሚከተሉ ሲሆኑ ለዚህ ምርጫ እንደመስፈርትነት የቀረበው ውሸት በአፋቸው አለመገኘቱ፣ ከሴት ጋር አለመተኛታቸው፣ ነውር ያልተገኘባቸው መሆናቸውና የመሳሰሉት እንጂ ፈጽሞ የ Shincheonji አባልነት በራዕዩ ላይ ቀርቦ አናገኝም። ይህ ፍጹም የእግዚአብሔርን ምርጫ ብቻ የምናይበት ክፍል ነው።
  • በተጨማሪም ከንጉስ ካህንነት አንጻር ያነሳው ሃሳብ በ 2ጴጥ 2፥9 ላይ "እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤" የተገለጠ ሃሳብ ሲሆን እርሱ ለዚህ መስፈርትነት ያነሳው የ Shincheunji አባልነት በቃሉ ውስጥ የሌለና ከዛ ይልቅ እንደውም የንጉስ ካህንነት ጉዳይ እንደርሱ አገላለጽ የተስፋ(የወደፊት) ጉዳይ ሳይሆን በአማኞች ሕይወት የተከናወነ ጉዳይ መሆኑን እንረዳለ።

3. ከዚህ በተጨማሪም የነዚህ የShincheonji አስራ ሁለት ነገድና 144 ሺህ አባል ለመሆን በሊ ማን-ሂ የሚዘጋጅ 300 ጥያቄዎችን የያዘ ፈተና ማለፍ ግዴታ ሲሆን ፈተናውን ያለፉት ብቻ የነገዱ አባል እንደሚሆኑ ያስተምራል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ይህንን ፈተና መመለስ የሚችሉት የ Shincheonji አባላት ብቻ መሆናቸውንና ከዛ ውጪ ያሉ ሰዎች ቢፈተኑ እንኳን መመለስ እንደማይችሉ የእግዚአብሔር ማጣሪያ ወንፊት የርሱ የወረቀት ፈተና እንደሆነ አድርጎ አባላቱን ያስተምራቸውል።

  • ይህ ፈጽሞ ስህተት የሆነና እኛ ድኅነትን ያገኘነው እንዲሁ በጸጋ መሆኑን ቅዱስ ቃሉ በማያወላዳ ሁኔታ አስረግጦ ያስተምረናል። (ቆላ1:13-14፣ ዮሐ3:16፣ ኤፌ 2፥9. . . ) የዳንነው በጸጋ ብቻ ነው!

ከቃሉ ባለስልጣንነት አንጻር

ለዚህ ሀሳብ ከላይ ያየናቸው ሃሳቦች ብቻ በቂ ሲሆኑ የቅዱስ ቃሉን ስልጣን በመዳፈርና በመጋፋት ቃሉን ለራሱ ጥቅምና ሃሳብ ብቻ እየተረጎመ ከመገኘቱም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ዳግም ለማስተካከል በድፍረት የተነሳ ሰው ነው። በዚህም ከቦታ ስም እስከ ጭብጥ ለውጥ ድረስ በማድረቅ ለራሱ የሚመቸውን ትርጓሜ ሰጥቶ የሚያስተምር ሰው ነው።

ማስታወሻ

ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ የተነሳሳነው የዚህ የአስተምህሮ ቡድን በዚህ ወቅት በከተማችን አያሌ ቦታዎች በከባድ ፍጥነት እየተንቀሳቀሰ ያለ በመሆኑና አቀራረባቸውና ትምህርታቸው ለምድ ለባሽ ተኩላ እንደሚባለው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አሳበው ይህንን ፍጹም ከቃሉ ያፈነገጠ ይምህርት በቀስታ የሚያሰርፁ የገንፎ ውስጥ ስንጥር የጭቃ ውስጥ እሾህ የሆኑ ቡድኖች ናቸው።

በዚህ ጊዜ በአብዛናው በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ኮሌጅና ዩኒቨርስቲዎች ደጃፍ የማይጠፉ ሆነዋል። እነዚህ ቡድኖች በዋናነት ክርስቲያን(ፕሮቴስታንት) የሚያድኑ(Hunt) ሲሆን በምንም መልኩ የጠለቀ ስነመለኮታዊ ውይይቶችን የማያደርጉና ሃሳቡ ሲነሳም ካዘጋጁት ትምህርት በኋላ እንደሚደርስ አድርገው በማድበስበስ በማለፍ ይታወቃሉ።

ተወዳጆቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በተባለበት ስፍራ ሁሉ መገኘት መንፈሳዊነት አይደለምና ነገሮችን በማስተዋል ልታደርጉ እንደሚገባ አሳስበን ማለፍ እንወዳለን።

እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ኤፌ 4:14


ለተጨማሪና ለበለጠ መረጃ በ @BenChabod ሊያነጋግሩንና ግብአቶችን ማድረስ እንችላለን። እንዲሁም www.21church.com ላይ ስለ ትምህርቱ የበለጠ ማግኘት ይችላሉ።

Report Page