'SHANE' & 'TPLF '

'SHANE' & 'TPLF '

DW , AL AIN , HoPR

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪ :

ዛሬ ኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባስተላለፈው ማስታወቂያ "ህወሓት" እና "ሸኔ" የሚባሉት ድርጅቶች በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ሚንስትሮች ምክር ቤት ባቀረበው ውሳኔ ሃሳብ ላይ የተቃውሞ ማስረጃ ካላቸው እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።

ምክር ቤቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 2ዐ ንኡስ አንቀጽ 2 መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ/ም ባካሄደው 23ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ህዝበ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/ እና ‘’ሸኔ’’ ድርጅቶች በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሃሳብ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መቅረቡ ገልጿል።

በአዋጁ አንቀጽ 21 ንኡስ አንቀጽ 1 በተደነገገው መሠረት ሁለቱ ድርጅቶች የውሳኔ ሀሳቡን ለመቃወም የሚያስችል ማንኛውም ማስረጃ ካላቸው ይህ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙሃን ከተነገረበት ሰዓት ጀምሮ ባሉት 48 ሰዓታት ውስጥ በም/ቤቱ ጽ/ቤት በአካል በመገኘት እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።


ህግ ምሁራን እና ባለሞያዎች ምን ይላሉ ?

በሚኒስትሮች ምክር ቤት በአሸባሪነት እንዲፈረጁ የውሳኔ ሀሳብ ስለቀረበባቸው 'ሕወሓት' እና 'ሸኔ' የህግ ሰዎች ምን ይላሉ ? ድርጅቶቹን በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚያመጣው ውጤት ምንድነው ?

ህወሓት እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን ሀሳብ ተከትሎ ብዙ ሀሳቦች እየተነሱ ነው። በተለይ 'ሸኔ' ማነው ? የሚለውን ብዙዎችን አወዛግቧል። ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ለሚፈፀሙ ግድያዎችን መንግስት "ኦነግ ሸኔ" የሚል ስም በመጠቀም ተጠያቂ ሲያደርግ ነበር።

አሁን ግን 'ሸኔ' የሚል ብቻ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የውሳኔ ሀሳብ መተላለፉ አነጋጋሪ ሆኗል። በዚህ ስም የሚታወቅ ድርጅት በሌለበት እንዴት በአሸባሪነት ይፈረጃል ሲሉም በርካቶች ይጠይቃሉ።

ያም ሆነ ይህ አሁንም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ዙሪያ አስተያየቶች መሰጠታቸውን ቀጥሏል።

የጀርመን ድምፅ በዛሬ ምሽት የሬድዮ ስርጭቱ ላይ ሁለት የህግ ምሁራንን አነጋግሮ አስተያየታቸውን አሰራጭቷል።

አንደኛው የህግ ጠበቃ እና አማካሪው አቶ አመሃ መኮንንን ሲሆኑ ድርጅቶቹ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የመወሰኑን ውሳኔ በተመለከተ ተከታዩን ብለዋል ፥

"አንዴ ኦነግ ሸኔ ይባላል፣ አሁን ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተባለው ሸኔ የሚል ቋንቋ ነው፤ ከኦነግ ጋር የሚገናኝ ሆኖ አይታይም፤ የራሱ ምክንያት ይኖራል። ሸኔ አለ ? የለም ? ሸኔ የኦነግ ስራ አስፈፃሚ ማለት ነው የሚል ነገርም ሰምተን ነበር ፤ ዞሮ ዞሮ ግን በዚህ ቡድን ስም እጅግ አሰቃቂ የሚባሉ ግድያዎች ፣ ንብረት ማውደምው ፣ ሰዎችን የመጥለፍ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል። ዓላማውን በኃይል ለማስፈፀም ሲንቀሳሰቅ ነው የምናውቀው። ስለዚህ በአሸባሪነት መፈረጁ ተገቢነት አለው ብሎ መውሰድ ይቻላል። 

ህወሓትን በሚመለከት ይህ ድርጅት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በህግ ተመዝግቦ፣ ሀገርም ጭምር ሲመራ የነበረ ድርጅት ነው። ከለውጡ በኃላ አመራሮቹ ከፌዴራሉ መንግስት ጋር አለመግባባት ፣ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣ አለመግባባት ፣ የለውጡን ሂደት ያለመቀበል ነገር አይተናል። መጨረሻ ላይ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ኃይል የቀላቀለ ግጭት ውስጥ የገባበትን ሁኔታ እናውቃለን። ከዛ በኃላ ምርጫ ቦርድ ድርጅቱ ህልውናው እንዲከስም አድርጓል፤ አመራሮቹ ተበትነው በመንግስት ሀብት ፣ በመንግስት መሳሪያ ከፌዴራል መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ የገባ ይመስለኛል የሽብርተኝነት ትርጓሜ ማዕቀፍ ውስጥ ከዛ በኃላ ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች።"


ባለፈው አመት የተሻሻለው የሽብር ወንጀልን ለመከላከልእና ለመቆጣጠእ የወጣው አዋጅ ቁጥር 11/76 ማንኛውም ሰው የፖለቲካ ፣ የሀይማኖት ወይም የርዮተ አለም አላማውን ለማራመድ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን በማሸበር መንግስትን ለማስገደድ መሞከርን ይከለክላል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ውሳኔ ሀሳብ መሰረት ከተሰየሙ የሽብረተኛ ድርጅቶች ጋር ፦ ትብብር / ትስስር፣ የሀሳብ እና የተግባር ዝምድና ያላቸው ግለሰቦች ድርጅቶች ላይ ውሳኔው ተፈፃሚ ይሆናል ብሏል።


የዚህ ውሳኔ ተፈፃሚነት ከፀና የሚያመጣውን ውጤት በተመለከተም አቶ አመሃ ይህን ብለዋል ፦

"እነዚህ ድርጅቶች በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ ስጋት፣ ለህዝቡ ፀጥታ ስጋት ፣ለሀገር ሰላም ስጋት የሚሆኑበት መንገድ በእጅጉ ይቀንሳል ብዬ ገምታለሁ።

በሽብረትኝነት የመሰየሙ ውጤት ፦

- እነዚህን ድርጅቶች መምራት የሚያስጠይቅ ይሆናል።

- የድርጅቶቹ አባል መሆን ያስጠይቃል።

- ድርጅቶቹን ባማቸውም ሁኔታ መደገፍ እና መተባበር የሚያስጠይቅ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ በእጅጉ አቅም የሚያሳጣቸው ነው የሚሆነው።


በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ሚኪያስ በቀለ የውሳኔው ውጤት በተመለከተ ውጤቱን እንደሚከተለው አስረድተዋል ፦

"በመጀመሪያ ደረጃ ህጋዊ ሰውነታቸውን ያጣሉ። ህጋዊ ሰውነት ከነበራቸው ጠ/አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤት አቅርቦ ፍርድ ቤቶች ናቸው እነዚህን ድርጅቶች የሚያፈርሷቸው።

ከዛ በኃላ እነዚህ ሽብርተኛ የተባሉ ድርጅቶች ከሌላ ማንኛውም ሶስተኛ ወገን ጋር ግንኙት መፈፀም አይችሉም፤ ከነሱ ጋር የሚደረግ ግንኙነትም ከመጀመሪያው ውጤት የሌለው ህገወጥ ይሆናል።

ንብረትን በተመለከተ በቀጥታ ለመንግስት እንዲወረስ ይሆናል።

አሁን አጠያያቂ የሆነው አንዱ ጉዳይ ፥ ሸኔ የሚባል ድርጅት አለ ወይ ? የሚለው ነገር ነው። እራሱን "ሸኔ" ብሎ የሚጠራ ቡድን አይታወቅም። ስለዚህ መንግስት ማለት የፈለገው የኦነግ የወታደራዊ ክንፉን ለማለት ይመስለኛል። 

ምክር ቤቱ በደንብ አድርጎ መርምሮ እነዚህን ድርጅቶች እራሳቸውን እንዲከላከሉ እድል ሰጥቶ ሽብርተኛ ድርጅት ነው የሚለውን ስያሜ ሊሰጥ ይችላል።

ውሳኔው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቅ ከሆነ በተለይ ህወሓት በትግራይ ፣ ሸኔ በኦሮሚያ መሰረታቸውን ያደረጉበት ህዝብ ላይ እንግልት እንዳይኖር ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።


አቶ አማሃ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎችም ይህን ብለዋል ፦

"እነዚህ ድርጅቶች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የሚሰየሙ ከሆነ ብዙ ሰዎች የነዚህ ድርጅቶች አመራር፣ አባላት ወይም ድጋፍ ሲሰጡ ተገኙ፣ ተባበሩ በሚል ሊከሰሱ ይችላሉ። ስለዚህ ፍርድ ቤቶች በጥንቃቄ በእያንዳዱ ጉዳይ ላይ በእርግጥም አባል ነው ወይ/አባል ነች ወይ፣ አመራር ነው ወይ፣ ነች ወይ / ድጋፍ ሰጥቷል የሚለውን በህግ እና በማስረጃ ብቻ አይተው መመዘን አለባቸው ያለበለዚያ ቀደም ሲል የተሻረው የፀረ ሽብር ህግ ውጤት የመከሰት እድል ሊኖር ይችላል። ከፍተኛ ኃላፊነት ሊኖር ይገባል"


በሌላ በኩል አል ዐይን አማርኛ የውሳኔ ሃሳቡን በማስመልከት ተገቢነቱን፣ አንድምታውን እና ምን ያህል ችግሮች ሊፈታ እንደሚችል ምሁራን አነጋግሮ በድረገፁ ይዞ የወጣ ሲሆን አስተያየታቸውን ካካፈሉት መካከል አንድ ስማቸው እንዲነገር ያልፈለጉ ምሁር ይገኙበታል።

ስማቸውን ያልተገለፀው ግለሰብ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ሲሆኑ ተከታዩን ብለዋል ፦

“በሽብርተኝነት ሊፈረጅ የሚችል አካል ለቁጥጥር ያስቸገረ ጠንካራ መዋቅር ያለው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያው ጭምር ህወሓት ስጋት ሊሆን በማይችልበት ደረጃ “መመታቱን እና መዳከሙን ደጋግመው በአደባባይ በተናገሩ” ማግስት እንዲህ መባሉ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

‘አጥፍተነዋል’ በሚል ሲነገር የነበረው “ፕሮፓጋንዳ እንደነበርና ህወሓት አሁንም ስጋት እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

የመንግስትን ተዓማኒነት “ይበልጥኑ የሚጎዳ” ነው።

በትግራይ ከተካሄደው “ህግ የማስከበር ዘመቻ” ጋር በተያያዘ አስከፊ ሰብዓዊ ጥሰቶች መፈጸማቸውን በመግለጽ ችግሩ “በሰላማዊ መንገድ በድርድር” እንዲፈታ ከተለያዩ የውጭ አካላት ጥያቄዎች እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡

‘ሁኔታው አሳስቦናል’ በሚሉ የውጭ አካላት የሚቀርቡት እነዚህ ጥያቄዎች አሁን አሁን የጫና መልክም እየያዙ ነው፡፡

በሽብርተኝነት የመፈረጁ የውሳኔ ሃሳብ በዚሁ ሰበብ የመጣም ነው።

በአሸባሪነት ከተፈረጀ አካል ጋር አንደራደርም በሚል ተጽዕኖውን ለመቋቋም በማሰብ የተደረገ ሊሆን ይችላል።

ሆኖም ከድርጅቶቹ ጋር “ግንኙነት አላቸው በሚል የሚጠረጠሩ አካላት ለተለያዩ በደሎች እንዳይዳረጉ፤ ለጭቆና በር እንዳይከፍት ስጋት አለኝ።

መንግስት “ሸኔ” ሲል ስለጠቀሰው ምንነቱና ማንነቱ የማይታወቅ አካል ሊጠየቅና ሊያብራራ ይገባል።

“ታጥቆ ዜጎችን የሚገድለው ኦነግ ሸኔ ‘የመንግስት ድጋፍ አለው፤ የኦነግ እና የመንግስት ጥምር ጦር ነው’ እየተባለ ባለበት ሁኔታ ነጥሎ ‘ሸኔ’ ማለቱ ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

ቡድኑ በመንግስት ይደገፋል መባሉን የሚያጠናክር እና ከለላ ለመስጠት በማሰብ የተደረገ ሊሆንም ይችላል።


የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና ፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ደግሞ ተከታዩን ብለዋል ፦

“ውሳኔ እንዲያውም ቢዘገይ እንጂ የሚጎዳ አይደለም።

ህወሓትን ሽብርተኛ ብሎ ለመፈረጅ በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰው ጉዳት ብቻ በቂ ነው።

ህወሓት ባለፉት 3 ዓመታት በግልጽ እና በስውር በርካታ ጥፋቶችን አድርሷል። የዘገየ ግን ትክክለኛ የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል።

መንግስት በውሳኔ ሃሳቡ ኦነግ ሸኔ ከማለት ይልቅ ‘ሸኔ’ ማለቱ ምናልባት ለሌላ ትርጉም እንዳይጋለጥ በማሰብ ሊሆን ይችላል እንጂ ‘ሸኔ’ በሚል በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናትን እና ሌሎች በክልሉ የሚኖሩ ማንኛውንም ማህበረሰብ እንደፈለገ እየገደለ ነው ይሄንን የሚያደርገው ደግሞ ኦነግ ሸኔ ነው።

“ሸኔ” እና “ኦነግ” አንድ ለመሆናቸው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ባንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን በትጥቅ መፍታት ጉዳይ ሲጠየቁ “ማን ነው ትጥቅ ፈቺ፤ ማንስ ነው ትጥቅ አስፈቺ” በሚል የሰጡት መግለጫ በቂ ማስረጃ ነው።

መንግስት ትጥቅ እንዲፈቱ ሲጠይቅ ‘ወታደሮቻችን ትጥቅ የሚፈቱት ለመንግስት ሳይሆን ለአባገዳዎች ነው በሚል ነው የተንቀሳቀሱት።

ጉዳዩን በዝርዝር የሚያየው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‘ሸኔ’ በሚል የቀረበለትን ‘ኦነግ ሸኔ’ ብሎ ያስተካክላል የሚል ግምት አለኝ።

ኦነግ ሸኔ በይፋ ሰዎችን የሚገድል የተደራጀ እና የታጠቀ ሀይል ነው፤ በአሸባሪነት መፈረጁ ዘግይቷል እንጂ ትክክል ነው።

የሽብርተኝነት ውሳኔው በተለይም ኢትዮጵያ በህወሓት ጉዳይ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ለሚቀርብባት የተደራደሩ ጥያቄዎች መፍትሄ ሊሆን ይችላል።

የውጭ ሃገራቱ በሽብርተኛ ቡድኖች ላይ ያላቸው አቋም እንደሚታወቅ እና ደፍረው የተደራደሩ ጥያቄዎችን ለኢትዮጵያ ላያነሱ ይችላሉ።

ከዚህ ባለፈም ህወሓት እና ሸኔ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ያላቸው ገንዘብ፣ንብረት እና ሌሎችም ሀብቶች በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ስለሚውሉ ለኢትዮጵያ አንደ አገር ጥቅሙ ብዙ ይሆናል።


[ከላይ ያሉት የምሁራን ሀሳብ እና አስተያየቶችን ቲክቫህ የሰበሰበው ከጀርመን ድምፅ ሬድዮ (በጋዜጠኛ ሰለሞን ሙጬ እና ከአል ዓይን የአማርኛው አገግልግሎት ክፍል ነው]

Compiled By : Tikvah-Ethiopia

@tikvahethiopia

Report Page