Reporter

Reporter


" በታጣቂዎቹ የተወሰዱት ሕፃናት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ የለንም "


ከደቡብ ሱዳን በመነሳት ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ ክልል ገቡ የተባሉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሦስት ሕፃናት አፍነው መውሰዳቸውን የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ፡፡


የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡት ቃል ፦


- ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊትም በሕገወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው በመግባት የሰው ሕይወት አጥፍተዋል፣ ሕፃናትን አፍነው ወስደዋል፣ ከብቶችን ዘርፈዋል፤ አሁንም ቢሆን ድርጊቱ አልቆመም።


- በተለይ በአኮቦ፣ ዋንቲዋና መኮይ ወረዳዎች ሕፃናትን አፍኖ ለመውሰድ፣ ንብረት ለመዝረፍና በሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሙርሌ ታጣቂዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተስፋፍቷል ፤ ታጣቂዎቹ ባለፈው ሳምንት 3 ሕፃናትን አፍነው የወሰዱት በ3ቱ ወረዳዎች በነበራቸው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ነው።


- በታጣቂዎቹ የተወሰዱት ሕፃናት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ የለንም። የሰው ልጅ ካልሞተ ይገኛል ብሎ ማሰብ ቢቻልም፣ እስካሁን በተደረገው ሕፃናትን የማስመለስ ሙከራ አንፃር፣ አሁንም ቢሆን ሰሞኑን የተወሰዱት ሕፃናት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በሚደረግ ውይይት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ የለም።


- እስካሁን ታፍነው የተወሰዱት ሕፃናትና የተዘረፉ ንብረቶች ለማስመለስ ከዚህ ቀደም የክልሉ መንግስት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ቢያደርግም፣ ውይይቱ ውጤታማ ባለመሆኑ በተጨባጭ የተመለሰ ሕፃንም ሆነ ንብረት የለም።


- እስካሁን የተወሰዱት ሕፃናትና ተዘርፈው የተወሰዱ ከብቶች ይመለሳሉ ከሚል ተስፋ ባሻገር፣ የክልሉ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ያስችላሉ ብሎ ያመነባቸው ሁለት ዓበይት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሠራ ይገኛል። በአንዱ ተግባርም ውጤታማ እየሆነ ነው።


ከሁለቱ ጉዳዮች መካከል አንደኛውና የመጀመሪያው የክልሉን ፖሊሶችና ሚሊሻዎች ብቁ አድርጎ በማሠልጠን፣ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃት በሚያደርሱበትና ድንበር ጥሰው በሚገቡበት አካባቢ አሰማርቶ፣ ከዚህ በኋላ ጥቃቱ እንዳይደገም የመከላከል ተግባር ላይ ማተኮር ነው፡፡


በፖሊሶችና ሚሊሻዎች አማካይነት ድንበር ጥሰው የሚገቡ ታጣቂዎችን በተደጋጋሚ ሙከራቸውን ለማክሸፍ ተችሏል፤ ለአብነትም ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት በዲማ ወረዳ ከሦስት ጊዜ በላይ በተከታታይ ባደረጉት ሰው የመግደል፣ ሕፃናትን አፍኖ የመውሰድ፣ እንዲሁም ንብረት የመዝረፍ ሙከራ ከሽፎ ሙሉ ለሙሉ ተደምስሰዋል።


- ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ የጋምቤላ ክልል መንግሥት እየተገበረው ያለው ሁለተኛ ተግባር ነው።


የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ከዚህ በፊት ታፍነው የተወሰዱ ሕፃናት እንዲመለሱ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ይሁንና በመጨረሻ የተገኘ ውጤት የለም፡፡ ይባስ ብሎም ችግሮችና ጥያቄዎች እየጨመሩ ስለመጡ ሕፃናቱ ይመለሳሉ የሚል ተስፋ መሰነቅ አይቻልም።


- ትልቁ ተስፋ የክልሉን ፖሊስና ሚሊሻ እያሠለጠኑ ታጣቂዎቹን መከላከል ነው።

(ሪፖርተር ጋዜጣ)

Report Page