Reporter
ናታን ዳዊትመንግሥት ሰላም በሌለበት የዋጋ ንረትን ማርገብ እንደማይቻል ይገንዘብ !
ፖለቲካዊ ጉዳዮችንና ተያያዥ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገው የሚከሰቱ ቀውሶች ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ነው፡፡
ለተከታታይ ዓመታት በየምክንያቱ የተፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ እንዲሁም የለየለት ጦርነቶች በሕይወትና በንብረት ላይ ያደረሱት ውድመት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
የማይሻሩ ጠባሳዎችንም አኑረዋል፡፡ ያለመረጋጋቶቹ የፈጠሯቸው አያሌ ጥፋቶች አገራዊ ኢኮኖሚው ላይም ያሳረፈው ተፅዕኖ በቀላሉ ሊጠገን የማይችል ስብራት ከማድረሱም በላይ፣ የአገር ዕድገት ወደኋላ እንዲጎተት አድርጓል፡፡
ከአንደኛው ችግር ወጣን ስንል ሌላው እየተተካ ስናስተናግደው የቆየነው ትርምስ ዛሬም መቋጫ ያልተገኘለት በመሆኑ፣ አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለማቋረጥ የቀጠሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የአገሪቱን ሀብት እየበላ ነው፡፡
ለልማት መዋል የሚችል ገንዘብ እየታጠፈ በየጊዘው የሚፈጠሩ ቀውሶች ማብረጃ ሲሆን ቆይቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት አገራችን ያጋጠማትን ተደራራቢ ችግሮች ለመወጣት የወጣውን ወጪ ቤት ይቁጠረው እንጂ፣ መልሰን ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመግባትም የሚጠይቀን ድካምና ወጪ አገሪቱ መሸከም ከምትችለው በላይ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡
በተከታታይ የተከሰቱና እየተፈጠሩ ያሉት ቀውሶች መነሻቸው ምንም ይሁን ምን፣ እንደ አገር እያስከፈለ ያለው ዋጋ ነገም ላለመቀጠሉ እርግጠኞች አይደለንም፡፡
ማንኛውም ግጭትና ቀውስ ከሚያስከትላቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ በግብይት ሥርዓት ውስጥ እያስከተለ ያለውን ችግር ብቻ ነጥለን እንኳን ብናይ ጉዳቱ እያንዳንዱን ዜጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡
በአንድ አካባቢ ግጭት ተከሰተ ሲባል ወዲያው የግብይት ሥርዓቱ የበለጠ ይበለሻሻል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የዋጋ ንረት ቦታውን በመያዝ የኑሮ ውድነቱን ሲያባብሰው ዓይተናል፣ እየተመለከትንም ነን፡፡
ወትሮም ውስብስብ ጤንነት የሚጎድለው የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት በየአካባቢው የሚፈጠሩት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሲታከሉበት ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡
ከዚህ ቀደም በእጅጉ የአገር ፈተና የሆኑትን ጦርነቶችና ግጭቶች ትተን ከጥቂት ወራት ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ምሳሌ አድርገን ብንወስድ ያለመረጋጋቶቹ ገበያው ላይ እየፈጠሩ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች በቀላሉ ለመረዳት ያስችላል፡፡
ችግሩ በክልሉ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ወጪ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖው እንዲታይ አድርጓል፡፡ ግጭቱ በተለይ በክልሉ ውስጥ አሁንም ድረስ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን አውኮታል፡፡
ግጭቱ ጎልቶ በወጣባቸው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ አጠቃላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴው እንዲታጎል ከማደረጉም በላይ የምርትና ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ እንዲንሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
እንደ ባህር ዳር ያሉ ከተሞች አንድ ሌትር እሽግ ውኃ እስከ 40 ብር እንዲሸጥ አድርጓል፡፡ የጤፍ ዋጋ በኩንታል ከ10 ሺሕ ብር በላይ እንዲያሻቅብ ሆኗል፡፡ ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችም እስከ እጥፍ ዋጋ ወጥቶላቸው ሲሸጡ እንደነበርም ለመታዘብ ተችሏል፡፡ አጋጣሚው ሠርግና ምላሽ የሆነላቸው ስግብግብ የሚባሉ ነጋዴዎች ኅብረተሰቡ የገባበትን ችግር እንኳን ተረድተው ሊራሩ ያለመቻላቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
መንገዶች በመዘጋጋታቸውም ወደ ክልሉ የሚገቡና የሚወጡ ምርቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ በመቋረጣቸው የተፈጠረው እጥረት ችግሩን አባብሶታል፡፡
ከክልሉ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ እንደ ጤፍ ያሉ ምርቶች ዋጋቸው ከሚገመተው በላይ ጨምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ እንኳን የአንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 2,000 ብር ዋጋ መጨመሩ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡
ከ150 እስከ 180 ብር የሚሸጥ ከሰል ከሰሞኑ ከ350 ብር በላይ ዋጋ እንዲያወጣ የሆነበት ምክንያቱ ይኼው በተፈጠረው አለመረጋጋት የግብይት ሥርዓቱ በመታወኩ ነው፡፡
እነዚህ በቀጥታ ሸማቹን ከሚመለከቱ ተፅዕኖዎች ባሻገር የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲቋረጥ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲስተጓጎልና አጠቃላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴው ተጎድቷል፡፡
ዕለታዊ ጉርሳቸውን በየዕለቱ ጉልበታቸውን ሸጠው ሕይወታቸውን የሚገፉ ዜጎች በእጅጉ ተፈትነውበታል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችም መንገድ አጥተው ለማዕከላዊ ገበያ ሊቀርቡ ያለመቻላቸው በራሱ በአንድ አካባቢ የሚከሰት ቀውስ ፍዳው እዚያው የሚያበቃ አለመሆኑን ነው፡፡
ጥቂት የማይባሉ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ፆም ማሳደራቸው የሚፈጥረው የምርት አቅርቦት ካሰብን ግጭቶችና ያለመረጋጋቶች ለረሃብ መቀስቀስ ጭምር ምክንያት ስለመሆናቸው መገንዘበ አያዳግትም፡፡
እንዲህ ያሉትን ድርብርብ ችግሮች ባለፉት ዓመታት ቀውስ በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተመለከትናቸው ናቸው፣ ተመሳሳይ ችግሮች ተስተናግደዋል፡፡ ጉዳዩን ከሸማቹ አንፃር ሲታይ ጉዳቱን የበለጠ ከፍ የሚያደርገው እውነት ደግሞ በተከሰቱት ግጭቶች ምክንያት የተፈጠሩ የዋጋ ማሻቀቦች ሲመለሱ ያለመታየታቸው ነው፡፡ በዚያው ዋጋቸው ተሰቅሎ መቀጠሉ ያለመረጋጋትና ግጭቶች ጉዳት የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆኑ የነገም ፍዳዎች ሆነው የሚቀጥሉ መሆኑን በቀላሉ የምንረዳው ነው፡፡
በአንድ ተፈጠረ በተባለ ችግር ዋጋው የጨመረ ምርት ችግሩ ከተፈታ በኋላም በዚያው ሲቀጥል ለምን ብሎ የሚጠይቅ ስለሌለ ወይም ከቀውስ በኋላ የግብይቱን ሥርዓት ጤናማ ለማድረግ የሚያስችል አሠራርና ልምድ ባለመኖሩ በእጅጉ ያሳስባል፡፡
አሁንም በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ምክንያት አድርገው በክልሉም ሆኑ ከክልሉ ውጪ የታዩ የዋጋ ለውጦች ወደ ትክክለኛ የገበያ ዋጋቸው ይመለሳሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የሚገኝበት መንገድ ካልተፈጠረ የዋጋ ንረቱን ማባባሱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ችግር የሚሆን መፍትሔ አልተበጀም፡፡ የግብይት ሥርዓታችን የበለጠ እየታመመ ለዋጋ ንረቱም መባባስ ምክንያት እየሆነ ሊቀጥል ይችላል፡፡
አገርንና ዜጎቿን ዋጋ እያስከፈለ ያለውን ተደጋጋሚና ተከታታይ ቀውሶች የፈጠሩትን ሁለንተናዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ማሳለፍ ካልተቻለ የነገው ችግሮቻችን አሁን ከምናየው በላይ ይሆናል፡፡
ስለዚህ ሥር እየሰደደ ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብ፣ ቢያንስ አሁን ካለንበት እንዳይብስ ከተፈለገ ሰላም የግድ ይላል፡፡ የዋጋ ንረትን ለማርገብ መንግሥት እከተላቸዋለሁ ብሎ ይፋ ያደረጋቸው የፖሊሲ ውሳኔዎችም ቢሆኑ መሬት ላይ ሊወርዱ የሚችሉበት፣ እየታዩ ያሉ ችግሮችን በመፍታትና ሰላም እንዲወርድ በማድረግ ብቻ ነው፡፡
(ሪፖርተር ጋዜጣ - ናታን ዳዊት)