Reporter
Journalist Dawit Tayeኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከወቅታዊ የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የዋስትና ሽፋን ለሚሰጧቸው ንብረቶች የሚያስከፍሉትን የዓረቦን መጠን እየጨመሩ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ በተለይ በሞተር ኢንሹራንስ ዘርፍ ለተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ይጠይቁ የነበረውን የዓረቦን መጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመራቸው ታውቋል፡፡
ኩባንያዎቹ ለሚሰጡት የመድን ሽፋን ይጠይቁ ከነበረው ዋጋ እስከ እጥፍ ጭማሪ እየጠየቁ መሆኑን የኩባንያዎቹ ደንበኞች እየገለጹም ነው፡፡ ደንበኞቹ የተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ሲያሳድሱ በወቅቱ የተሽከርካሪዎች ዋጋ መሠረት ዓመታዊ የዓረቦን ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ እየተደረገ ነው፡፡
የኩባንያዎቹ ደንበኞች እንደሚገልጹት፣ የተሽከርካሪዎቻቸውን የኢንሹራንስ ሽፋን ለማሳደስ ሲቀርቡ ከዚህ ቀደም ሲከፍሉ ከነበረው የዓረቦን ዋጋ በላይ እየተጠየቁ ነው፡፡ ከኩባንያዎቹ የተገኘው መረጃም፣ ጭማሪ ሳይሆን ወቅቱን ያገናዘበ ማስተካከያ እየተገረገ ነው፡፡ ይህ የተለመደ አሠራር ሲሆን፣ የአሁኑን የሚለየው ከሌላው ጊዜ በተለየ የተሽከርካሪዎች ዓረቦን ዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡
አንዳንድ ደንበኞችም አደጋ ደርሶባቸው የጉዳት ካሳ በሚጠይቁበት ወቅት የኢንሹራንስ ሽፋናቸው በወቅታዊው ተሽከርካሪዎች ዋጋ መሠረት ገቢ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውንም እያመለከቱ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ በተለይ ዘንድሮ የተሽከርካሪዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ኩባንያዎቹም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተወሰነ ማስተካከያ ማድረጋቸው አግባብ ነው፡፡
የሚጠየቀው የዓረቦን መጠን ከዚህ ቀደም በተለየ ከፍተኛ የሆነው የተሽከርካሪዎች ዋጋ ከ80 በመቶ እስከ 100 በመቶ በመጨመሩ ነወ፡፡ የዓረቦን ክፍያውም በዚያው መጠን እየተስተካከለ ነው፡፡ ይህ የዓረቦን ጭማሪ ገበያው የፈጠረው እንጂ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ጭማሪ በማድረጋቸው አይደለም ይላሉ፡፡
በዚህ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎችም፣ የዓረቦን ክፍያ ማስተካከያ ቢያደርጉም ከወቅቱ የገበያ ዋጋ ጋር የሚመጣጠን የዓረቦን ዋጋ እየጠየቁ አለመሆኑን ያክላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ለተሽከርካሪዎች የሚጠየቀው የመድን ሸፋን ዋጋ ኢንዱስትሪውን አደጋ ላይ እየጣለ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
የኢንሹራንስ ባለሙያና የአልፋ ሰርተፊኬሽን ኮንሰልት ሰርቪስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢብሳ መሐመድ በበኩላቸው፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ወቅታዊውን የተሽከርካሪዎች ዋጋ ከግምት በማስገባት እየወሰዱ ነው የተባለው ዕርምጃ ትክልል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን የዓረቦን ክፍያ ላይ ተደረገ የሚባለው ጭማሪ ሳይሆን፣ የተሽከርካሪዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ኩባንያዎቹ ወቅቱን ባገናዘበ ማስተካከያ ማድረጋቸውን የሚያሳይ እንጂ የዋጋ ጭማሪ የሚለው ሁኔታውን የማይገልጽ በመሆኑ ነውም ብለው አክለዋል፡፡
‹‹የወቅቱ የገበያ ሁኔታ፣ የዶላር ምንዛሪ ከፍ ማለት፣ የመኪና ዋጋ ያላግባብ መጨመርና የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ እያሻቀቡ መምጣታቸው ኩባንያዎቹ ዓረቦን እንዲጨምሩ ያስገድዳቸዋል፤›› ያሉት አቶ ኢብሳ፣ የተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ዓረቦን ክፍያ ከፍ ለማለቱ ዋናው ምክንያት የገበያው ዋጋ አለመረጋጋትና የተሽከርካሪዎች ዋጋ በእጅጉ መጨመር ነው፡፡ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሲያስከፍሉ ከነበረው የዓረቦን መጠን በላይ እንዲጠይቁ ያስገደዳቸውም ወቅታዊው የዋጋ ንረትና በብዙ እጥፍ እየታየ ያለው ጭማሪ ነው፡፡
ኩባንያዎቹ ገበያ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥማቸው ማስተካከያ ማድረጋቸው ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ደንበኞችም ይህንን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት 400 ሺሕ እና 500 ሺሕ ብር ይሸጥ የነበረ አንድ መኪና 800 ሺሕ እና 900 ሺሕ ብር ሲገባ፣ በዚህ ዋጋ መሠረት ለመድን ሽፋኑ የሚጠየቀው ወይም ሲከፈል የነበረው የዓረቦን መጠን መስተካከል አለበት፡፡ ማስተካከያውም የሚጠቅመው ለደንበኛውም ጭምር ነው፡፡
በገበያ ዋጋ መሠረት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማስተካከያውን ካላደረጉ የሚከስሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኢብሳ፣ በደንበኛውም በኩል ለተሽከርካሪ ዋስትና የከፈለው የዓረቦን መጠን ከገበያ ዋጋ በታች ከሆነ ተጎጂ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ የመድን ሽፋን አሰጣጥ በተለይ ከተሽከርካሪዎቸ አንፃር በርካታ ችግር ያለበት በመሆኑ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ማስተካከያዎች እንዲደረጉ መጣር እንደሚያስፈልግ አቶ ኢብሳ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በተለይ በተሽከርከሪዎች የዓረቦን ምጣኔ ላይ ከፍተኛ ችግር ያለ በመሆኑ፣ እንዲሁም ያልተገባ ዋጋ የሚሰጥበት ዘርፍ ሆኖ ለኢንዱስትሪው አደጋ ጭምር ከሚሆንበት ደረጃ ላይ በመድረሱ በዚህ የዓረቦን ምጣኔ ላይ አንድ አስገዳጅ ሕግ ሊኖር የሚገባ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማኅበር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ተስማምቶ ዝቅተኛ የዓረቦን ዋጋ መወሰን አለበት ይላሉ፡፡ ይህ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ መልስ ቢያገኝ ገበያውን ጤናማ ማድረግ ያስችላል፡፡
የመኪኖቹ የመሸጫ ዋጋ መታየትም አለበት፡፡ በአብዛኛው ገበያ ላይ ያሉት ተሽከርካሪዎች አሮጌ መሆናቸውን በመጠቆምም፣ እነዚህ መኪኖች ለመበላሸት ቅርብ መሆናቸውና የመለዋወጫ ዕቃዎች በአራትና በአምስት እጥፍ መጨመሩም ሌላ ፈተና ነው፡፡ በመሆኑም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን ለመቋቋምና የደንበኞቻቸውን የመድን ዋስትና ለመጠበቅ የግድ ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ ማስከፈል አለባቸው፡፡
የመኪና ዋጋ በጣም እያሻቀበ የሚሄድ ከሆነ ደግሞ የዚያን ዋጋ ለመተመን ወይም ለመሸፈን የዓረቦን ዋጋ ከፍ ማለት እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሞተር ኢንሹራንስ ደግሞ አክሳሪ ነው፡፡ አዋጭ የሚባል አይደለምና ነገሩ በጥንቃቄ መታየት ያለበትም ነው፡፡
ሌላው ከተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ጋር የሚታየው ችግር የመኪና ሽያጭ በሠለጠነ ባለሙያ የሚመራ አለመሆኑ ነው፡፡ አዲስ መኪና ከመግዛት ይልቅ ገበያውን ያጥለቀለቁት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ደላሎች ገበያውን እየናጡት ነው፡፡ በሰዎች ዘንድ አዲስ መኪና የመግዛት ልምድም አልተለመደም፡፡ በአሮጌና በአዲሱ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት እየታወቀ እንኳን ሰዎች አሮጌ መኪና ለመግዛት የሚመርጡት የደላሎች ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡
አሮጌ መኪና በ900,000 ብር ይሸጣል፡፡ አዲስ መኪና በ1.3 ሚሊዮን ብር መግዛት እየተቻለ ብዙዎቹ አሮጌ መኪና መግዛት ይመርጣሉ፡፡ እንዲህ ያሉ በገበያው ውስጥ የሚታዩ አሠራሮችን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ አዲስ መኪና መግዛትም የኢንሹራንስ ኩባንያዎችንም ሆነ የደንበኛውን ጫና ያቃልላል፡፡
ዘንድሮ ከመኪና ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለው የዓረቦን ዋጋ ጭማሪ በኢንዱስትሪው በብዛት ከሚሰጠው ከተሸከርካሪ መድን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰበሰበውን የዓረቦን መጠን ይጨምረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የመድን ሽፋን ከ60 በመቶ እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ዓረቦን የሚሰበሰበው ከተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ የዚያኑ ያህል ከጠቅላላው ለጉዳት ከሚከፈለው ካሳ ብዙውን እጅ የሚወሰደውም ይኼው የተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ነው፡፡
(ሪፖርተር ጋዜጣ)