Reporter

Reporter


የመምህራን ጥያቄ ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመምህራን ማኅበር በሥሩ ከሚገኙት አባላት መካከል የ29,500 አባላቱ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዲፈታለት ከንቲባ አዳነች አቤቤን በደብዳቤ ጠይቋል።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ለሪፖርተር ቃለ ምልልስ ሰጥተው ነበር። በዚህ ቃለምልልስ ምን አሉ ?

- ማህበሩ ከሁለት ሳምንት በፊት ለከንቲባዋ በጻፈው ደብዳቤ፣ በአስተዳደሩ ሥር የሚገኙ መምህራን የቤት ጥያቄ እንዲፈታ ጠይቋል፡፡

- የመምህራን ጥያቄ እየበረታ በመምጣቱ ከንቲባዋ ከመምህራን ጋር በ2013 ዓ.ም. በነበራቸው ስብሳሰባ፣ መምህራን በማኅበር ተደራጅተው ቤት እንዲገነቡ እንደሚደረግ ቢገለጽም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ተስፋ ሰጪ ነገር እየታየ አይደለም።

- ለከንቲባዋ በተፃፈው ደብዳቤ ለመምህራን የኑሮ ውድነትን የሚያረግቡ ድጎማዎች እንዲደረጉ፣ ከንቲባዋ በመድረክ ላይ የገቡት ቃል ወደ ታች ወርዶ እንዲፈጸምና በከተማ አስተዳደሩ በተጀመሩ ልማቶች የመምህራን ጥያቄዎች እልባት እንዲያገኙ ተጠይቋል።

- የመምህራን የደመወዝ ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከተቻለ በልዩ ትኩረት በከተማው ደረጃ ውሳኔ ሰጥቶበት እንዲፈታ፣ ካልሆነም ደግሞ የሚመለከተው የፌዴራል ተቋም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እልባት መስጠት እንዲቻል እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።

- የኑሮ ውድነት ማረጋጊያ ድጎማ 3,000 ብር የሚሰጥ ቢሆንም፣ ገንዘቡ ከችግሩ ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ቢያንስ በእጥፍ እንዲያድግ መምህራኑ ይፈልጋሉ።

በተጨማሪ ለከንቲባዋ በተፃፈው ደብዳቤ ....

ለመምህራን ሁለተኛ መ/ ቤታቸው የሆነው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ፣ ግንቦት 2013 ዓ.ም. መምህራንን ባወያዩበት ወቅት መምህራን በማኅበር ተደራጅተው ቤት እንዲገነቡ እንደሚደረግ የተገለጸ ቢሆንም፣ ነገር ግን እስካሁን በተፈለገው ርቀት ወደ ሥራ አለመገባቱን ያትታል፡፡ 

በዚህ የተነሳ ባለፉት ወራት ምንም ዓይነት ለውጥ አለመኖሩ መምህራንን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ፣ ጉዳዩን በተቃራኒ በጥርጣሬ እንዲያዩት አነሳሽ ምክንያት ከመሆኑም በላይ ተስፋ አስቆራጭነቱ እየሰፋ የመጣ ስለመሆኑ ይገልጻል።

ይህ ጉዳይ መምህራን ቃል የገቡልንን አልተገበሩልንም (አላስተገበሩልንም) የሚል ስሜት ፈጥሮ የመምህራንን ሞራል ያላሸቀ ፣ ቤት ባላቸውና በሌላቸው መምህራን መካከል የፍትሐዊነት ጥያቄ ያስነሳ መሆኑም በደብዳቤው ተመላክቷል፡፡

መምህራን የሚያገኙት የደመወዝ መጠንና በአሁኑ ወቅት ያለው ፦ የቤት ኪራይ ዋጋ፣ በተጨማሪም የኑሮ ውድነት መምህራንን ተረጋግተው እንዳያስተምሩ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ ከንቲባዋ ለመምህራኑ በገቡት ቃል መሠረት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ የመምህራን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ " አጥብቀን እንጠይቃለን " ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ያለውን የኑሮ ውድነት መምህራኑ ከሚያገኙት ደመወዝና የኑሮ መደጎሚያ ጋር ተቋቁሞ መኖር ከባድ መሆኑን የሚያስረዳው ደብዳቤው፣ የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም ባደረገው የኑሮ መደጎሚያ ላይ ወቅቱን የሚመጥን ማሻሻያ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

ለከንቲባዋ የተላከው ደብዳቤ በመምህርነት ሙያ ላይ 40 ዓመትና 18 ዓመት ያገለገሉ መምህራን በአንድ ቋት ውስጥ አንድ ዓይነት ደመወዝ ስኬል መካተታቸውን ጠቅሶ፣ ይህም አግባብነት የሌለው በመሆኑ እንደ መንግሥት አስቸኳይ እልባት ያስፈልገዋል ብሏል፡፡

ግንባታው የተጀመረው የመምህራን ሆስፒታልና ሁለገብ ማዕከል ግንባታው እንዲፋጠን፣ መንግሥት በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግና የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ መምህራን የሥራ ላይ ዋስትና የሌላቸው በመሆኑ፣ ከሥራው ባህሪ አንፃር የሥራ ላይ ዋስትና/ኢንሹራንስ እንዲፈቀድላቸው በሚል አክሎ ጠይቋል፡፡

(ሪፖርተር ጋዜጣ)

@tikvahethiopia

Report Page