#Reporter
በከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር በአቶ ደሳለኝ ተረፈ ፊርማ ሰሞኑን ለአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ዕጣ የወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተያዘው ወር ዕጣ ለወጣላቸው ሰዎች ይተላለፋሉ፡፡
ነገር ግን በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሰን ላይ የተገነቡ ቤቶች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ተነጋግሮና መፍትሔ አስቀምጦ ስምምነት ላይ ሳይደረስ፣ ቤቶቹን ለዕድለኞቹ ለማስተላለፍ ውል መፈጸም በቀጣዩ ሒደት ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ቤቶቹ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት ውል ተፈጽሞባቸው ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ፣ ወደፊት የሚያስተዳድራቸው የኦሮሚያ ክልል በመሆኑ እንዴት እንደሚሆን በተለይ ጥናቱን አጥንቶ ያቀረበው ኮሚቴ ሊያብራራ ይገባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ከወጣባቸው በኋላ የዕድለኞች ስም ዝርዝርና ሙሉ መግለጫ የከተማ አስተዳደርሩ ልሳን በሆነው ‹‹አዲስ ልሳን ጋዜጣ›› ይታተም እንደነበር ለ12 ዙሮች የወጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ያስታወሱት ኃላፊዎቹ፣ ባለፈው ዓመት በ13ኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ዝርዝሩ እንዲታተም ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ የተላከ ቢሆንም፣ በወቅቱ በተፈጠረው ችግር ምክንያት እንዳይታተም መታገዱን አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን አሁን እንዲተላለፍ ከተወሰነ ዝርዝሩ ታትሞ መውጣት እንዳለበት፣ ዋና ጥቅሙም የዕጣው ባለቤቶች ችግር ቢገጥማቸው ማስረጃ ሊሆናቸው እንደሚችልም አክለዋል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ
@tikvahethiopiaBot @tikvahethiopia