Profile
Tikvah Ethiopiaዛሬ በዚህ በታላቁ የእውቀት መዘክር በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ታሪካቸውን በጥቂቱ የምናነሳሳላቸው አንዲት ብርቱ ኢትዮጵያዊት ናቸው። እኚህ ኢትዮጵያዊት አንድ ሆነው ለብዙ ሺ የሰው ልጆች ደህንነት፣ በሕይወት ለመቆየት እና ለወግ ለማድረግ መብቃት ትልቅ አስተዋዕጾ አድርገዋል። የኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊት ታሪክ በአንድ ገጠመኝ እንዲህ ማውጋት እንጀምራለን።
እንዲህ ሆነላችሁ ….
አንዲት ወጣት ከሐገረ አሜሪካን ወደ ትውልድ አገሯ ኢትዮጵያ መጣች፡፡ በአንዱ ጎዶሎ ቀን ከፍተኛ የሆነ የመኪና ደጋ ደረሰባት፡፡ አደጋው ከፍተኛ ነበርና ሁኔታው ለቤተሰብና ለዘመድ አዝማድ አስጨናቂ ነበር። የልጅቷን ሕይወት ለመታደግ የዘመኑን ሳይንስ የታጠቀ የኒውሮሰርጀን ሐኪም ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ ሙያ ላይ የበቃ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው የአገራችንን ሐኪሞች ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ ዕድል ቀንቶ ኒውሮሰርጅኑ ተገኘ። የተጨነቀው ቤተሰብ “እባክህ የልጃችንን ሕይወት ታደግልን ሲል ተማጸነው”
ዶክተሩም “እማማ እኔ እኮ የእርሶ ልጅ ነኝ! እርስዎ በሰሩት ትምህርት ቤት ተምሬ፣ ተመግቤ ነው ያደግሁት” አላቸው። እማማ ማርታ የዘሩትን መልካም ዘር ፍሬ ሲያገኙ ፈጣሪን አመሰገኑ።
ኒውሮሰርጅኑ ዶ/ር አብዲ ኤርሞሌ በብቃት ሥራውን አከናውኖ የእማማ ማርታ የቅርብ ዘመድ የሆነችውን የወጣቷን ሕይወት አተረፈ። ለመሆኑ የብዙዎች እናት፣ ደግ፣ ቅንና መልካም ሴት እማማ ማን ናቸው?
ልደት ተስፋ እና ጥረት
1920ዎቹ ዓ.ም. ውስጥ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጊዜው አጠራር ከሸዋ ክ/ሀገር የሄዱ ቤተሰቦች ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህ ቤተሰቦች በነቀምት ከተማ ውስጥ በልዩ ልዩ የኃያማኖታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሰማርተው ለነበሩ ሚሶዮናውያን ተቀጥረው የሚሰሩ ነበሩ፡፡
ሚያዝያ 02 ቀን 1924 ዓ.ም ለእነዚህ ታታሪ ቤተሰቦች ልዩ ቀን ነበረች፡፡ በነበራቸው ሁለት ወንድ ልጆች ላይ ሌላ አንዲት ሴት ልጅ ወለዱ፡፡ አቶ ገ/ፃዲቅ አሊዬ እና ወ/ሮ ወለተመስቀል ገነነ ይህችን ልጃቸውን ‹‹ማርታ›› ሲሉ ሰየሟት፡፡ በርግጥ የማርታ ወላጆች ከእነዚህ በሥጋ ከሚወለዷቸው ልጆቸቸው በተጨማሪ ሌሎች የልጅነት ማዕረግ የተሰጣቸውና ተንከባክበው የሚያሳድጓቸው በርካታ ልጆች ነበሯቸው፡፡
ሕጻኗ ማርታ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ የቀለም ትምህርትዋን በአከባቢዋ በሚገኘው ትምህርት ቤት ተምራ አጠናቃለች፡፡ በኋላም፣ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት የእጅ ስራ የዕደ ጥበብ ትምህርት እና የነርስነት ትምህርት ለመማር በቅታለች፡፡
ወጣትዋ ማርታ አንደበተ ርቱዕ፣ ደፋር እና ብልህ ከመሆኗ ጋር ተዳምሮ በዕውቀትና በማስተዋል የምትራመድ በመሆኗ ግርማ ሞገስ የተላበሰች ሴት ሆነች፡፡
ዘመኑ እነዲህ እንዳሁኑ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ሁኔታው በፍጥነት የሚቀያየርበት አለመሆኑ፣ የአገራችን የባህልና የኢኮኖሚ እድገት ውስን መሆን፣ ለበርካታ አታካች ችግሮች የሚጋላጥ ከመሆኑም በላይ፤ በአገር ልማድና ወግ መሰረት እንደ ማርታ ያለች ሴት ለብዙዎች ሚስት እንድትሆን የሚመኟት ነበረች፡፡
በ1950ዎቹ ዓመታት ሴቶች ከማጀት እና ከቤት እመቤትነት ውጭ በአደባባይ ወጥተው እና በኢኮኖሚው መስክ ራሳቸውን ችለው ለመገኘት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ የታዩ እንኳን ቢኖሩ፤ እጅግ ሲበዛ ጥቂቶች በተፈጥሮአቸው ጠንካራና በራስ መተማመን ባህሪይን የተላበሱ አልፎ አልፎ ብቅ ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ሴት ወይዛዝርት ነበሩ፡፡
እንዲህ ያለውን ከባድና ፈታኝ የሕይወት ጋሬጣ ለማለፍ በዘመኑ የነበረው ዕድል ከልዑላን፣ ወይም ከሌሎች በሥልጣን እርከን ከነበሩ ቤተሰቦች መካከል መወለድ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለወጣትዋ ማርታ ገብረጻዲቅ የተሰጠ አልነበረም፡፡
ወጣትዋ ማርታ ገብረጻዲቅ ግን ረጅም ለምታየው የነገው ሕይትዋ የተጠራች ነበረችና ትግሉን ከልጅነት እድሜዋ መሰረት ጥላ ጀመረችው፡፡
በልጅነት ያውም በለጋ እድሜ ከጥበብና ማስተዋል ሊያርቃት የሚችል፣ ከእኩያ ጓደኞችዋ ግንኙነት ነጥሎ የሚያስቀር፣ ከጥበብና ማስተዋል ከነገው ሕይወትዋና ጥሪዋ የሚያደናቅፋት፣ ከትምህርት ቤት ደጃፍ ሮጠው ላልጠገቡት እግሮችዋ መሰናክል የሆነ የጋብቻ ጥያቄ መጣ፡፡ ጥያቄውን የተቀበሉት ቤተሰቦችዋ ልጃቸውን ሊድሯት ወስነዋል፡፡ ይህን ለ,ያስቀር የሚችል ኃይል ደግሞ የለም፡ ስለዚህም ጋብቻው ከኖርዌጂያኑ ተወላጅ ከፒተር ጋር ተጣመረች፡፡ አሁን ወይዘሮ ተብላለች፡፡ ወይዘሮ ማርታ ገብረጻዲቅ፡፡
ትዳር እና ትምህርት
ሂደቱ ግን ለግላጋዋን ማርታን እንደሌሎች የአገሯ ሴቶች ሁሉ ቅስሟን የሚሰብርና ከቤት የሚያስቀራትና ከጥሪዋ የሚያቆማት ሆኖ አልተገኘም፡፡ መማር እንደሚጠቅማት የተረዳችው ማርታ በትምህርትዋ ያለመታከት ገፋች፡፡ በውጤትዋም ብልጫ ያት ሴት በመሆኗ ለሽልማት ከንጉሥ ፊት ለመገኘት ታጨች፡፡ ነገር ግን ይህንን የሽልማት ሥነ ስርዓት መካፈል እንደማትችል ተነገራት።
ማርታ፤ “እንዴት ተደርጎ አለች” ይህ ሽልማትና ማዕረግ በጥረትና በልፋት የተገኘ በመሆኑ፤ እንዲህ በቀላሉ ሊቀር የሚችል አልነበረም፡፡ ጠየቀች፡፡ ከልካይዎችዋ ግን ከጥቂት ወራት በፊት ባደረገችው ጋብቻ ሳቢያ የተፈጠረውን እርግዝና ምክንያት አድርገው ፤ ከንጉስ ፊት ለመገኘት ብቁ አይደለሽም አሏት፡፡ እርሷ ግን ይህ ምክንያታቸውን አልተቀበለችም፡፡ ‹‹በየትኛውም ምክንያት ቢሆን ከሽልማቴ ልቀር አይገባኝም፡፡›› ስትል ተሟገተች፡፡
የጊዜው የትምህርት አስተዳደሮች ደግሞ በእርግዝና ውስጥ ሆነሽ ለሚመለከቱ ሰዎች ሁኔታውን ባልተገባ መንገድ ይረዱታልና ልንፈቅድ አንችልም፤ ለሐሜት ያጋልጣል ሲሉ ሞገቷት፡፡
የእርሷ ምላሽ በቂና ሃቅ ነበር፡፡ ‹‹ካገባሁ 10 ወራት አልፎኛል፡፡ ይህም ጋብቻ ህጋዊና የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ምኑ ነው ለሃሜት የሚያጋልጠው … በዚህ ምክንያት ልቀር አይገባኝም፡፡›› አለች፡፡ ከዚህ በላይ ሊከራከሯት የሚችሉበት ሰበብ አጡ፡፡ ብርቱዋ ሴት ማርታ ትግሉን በድል አሸነፈች፡፡ ይህ የማርታ ድል በጭለማ ውስጥ ለነበረው የማህበራዊ ጥሪ የማንቂያ ደወል ሆኖ ተሰማ፡፡ ያገባች ሴትም ብትሆን በትምህርትዋ መቀጠል ትችላለች የሚል ጮኽ ያለ የሚሊዮኖችን ብሶት አሰማ፡፡ ንጉሡ ቀ.ኃ.ሥ እና ንግሥቲቱ ለወጣትዋ ወ/ሮ ማርታ ገብረጻዲቅ ሽልማታቸውን በአድናቆት አበረከቱላት፡፡
ይህ ሽልማት ለማርታ እንደ አብሪ ኮከብ ሆኖ የሚታይ የሕይወት ትግል የድል ብስራት ደወል ሆነ፡፡ በጥረትዋ የገፋችው ማርታ፤ በነሐሴ 1947 ዓ.ም. የሁለትና የአንድ ኣመት ልጆቻቸውን ለወላጅ እናትዋ ክብካቤ ሰጥታ፣ ለከፍተኛ ትምህርት ዕድል ወደ አገረ አሜሪካ አቀናች፡፡ የረዥም ጎዳና ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል እንዲሉ፤ ለዓመታት ከቤተሰብዋ የሚለያት የትምህርት ዕድል ዘላቂ ለሆነው የሕይወት ጥሪና ዓላማ ጠቃሚ በመሆኑ እንባዋን ዋጥ አድርጋ ጉዞዋን ቀጠለች፡፡
ከዚህ ከትዳር አገሯ ከፒተር በሚደረግላት ድጋፍ እና በአገረ አሜሪካን በምታደርገው ጥረትና ብርታት እራስዋን ያበረታቸው ትጉህና ታታሪዋ ማርታ አድካሚ የነበሩትን አምስት ዓመታት በሰው አገር ላይ በብቸኝነት ቆይታ በAdams State University ትምህርቷን በማጠናነቅ በB.A. ዲግሪ ተመርቃ ወደ አገሯ ተመለሰች፡፡
ኑሮ፣ ሕይወት፣ ሥራ እና ኃላፊነት
በርካቶች እንደሚያስቡት ከአሜሪካ መልስ ሕይወት ለማርታ ቀላልና አስደሳች ሆኖ አልጠበቃትም፡፡ እዚህ በትውልድ አገሯ ላይ ሆና ሕይትዋን ለመምራትና ለህብረተሰቧ የበኩሏን አስተዋጽዎ ለማበርከት ለምትመኘው ሴት፤ ሕይወት ፈተና ነበር፡፡
ከዚህ ከባድ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሊጠቀስ የሚገባው፤ የውድ ባለቤትዋ የሚስተር ፒተር ከእርሷ፣ ከልጆቻቸው፣ ከገነቡት ቤተሰባቸውና ለ32 ዓመታት ሲያገለግሉት ከነበረው ሕብረተሰብና ሕይወት በድካም ማረፍ ነበር፡፡ ያኔ ለማርታ፣ ሁለት ልጆችዋን ጨምሮ በዙሪያዋ ያሉትን ሰዎች ሁሉ መከባከብና መርዳት፣ እንዲሁም፤ ለዘላቂው ሕይወት ጅማሬ የብቸኝነቱን ጎዳና መላመድና መዘጋጀት ይጠበቅባት ነበር፡፡
እናም ይኽን ክፉ ጊዜ መሻገር ወይም ለችግሮቹ መሸነፍና እጅ መስጠት ምርጫ ሆነው ቀርበዋል፡፡ …. መሸነፍ በማርታ ሕይወት ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ግን ደግሞ ለማሸነፍና ለድል የሚያበቃ ምን መላ መዘየድ እናዳለባት፤ በእጅዋ ያሉት የሥራ ዕድሎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በቅጡ ማጤን ያስፈልጋት ነበር፡፡
ሐዘኗን ዋጥ አድርጋ፤ ነቃ ባለ ሕሊና፣ ኮስትር ባለ ሐሞትና ትጉህ በሆነ ልቦና ከፊት ለፊትዋ ያለውን የእርሷን የልጆችዋን እንዲሁም የአገሯን መልካም ዕድል ለመገንባት ጥረት ማድረጓን ጀመረች፡፡ በተማረችው ትምህርትም ሆነ በሌላ በማናቸውም የሙያ መስክ አገልግሎት ለማስጠት እንድትችል ዕድል እንዲሰጣት ለቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የማመልከቻ ደብዳቤዋን ጻፈች፡፡
‹‹የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቴን በሚገባ አጠናቅቄ ወደ አገሬ ተመልሼያለሁ፡፡ አገሬ የእኔ ሙያና ክህሎት በሚገባ ያስፈልጋታል፡፡ ስለሆነም፤ ግርማዊነትዎ የሥራ ዕድል ይሰጠኝ ዘንድ አመለክታለሁ፡፡›› ስትል አሳሰበች፡፡ ቀድሞም ቢሆን በትጋትና በታታሪነትዋ አውቀው ከሌሎች ይልቅ በአብላጫ ውጤትዋ የሸለሟት ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳሚ ኃይለ ሥላሴ ለጥያቄዋ ቀና ምላሽ ሰጧትና በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ A Point Four Educational Program Liaison Officer ሆና ሥራ እንድትጀመር ተደረገ፡፡
ይህን የሥራ እድል ያገኘችው ማርታ በዚህ በተሰጣት ሙያ ከአንድ ወር በላይ አልቆየችበትም፡፡ ሙያውን ጠልታው፣ ወይም በሥራ ምክንያት ተጋጭታ አልያም በሌላ አንዳች መጥፎ ምክንያት ሳይሆን፤ የምትወዳት ሀገሯ ለበለጠው ግዳጅና ኃላፊነት ገና በለጋነት አጭታ ስለሾመቻት እንጂ፡፡
ወቅቱ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም የተለየ ትኩረትን የሳበችበት ጊዜ ነበር፡፡ ከወራሪው ግፈኛ ፋሽስት ጣሊያን የአምስት አመት ጭንቅ ጊዜ በድል ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንገስት፤ ፊቱን ወደ አገራዊ ልማትና እድገት ያዞረበት ነው ሲሉ በርካቶች የጊዜውን ታሪክ የሰነዱ ምሁራን ያወሳሉ፡፡ በጊዜው ያሉ እንደ ማርታ ያሉ ወጣቶችም አገራቸውን በልዩ ፍቅር የሚወድዱ ከመሆናቸውም በላይ፤ በጥንታዊ ሥልጣኔ፣ በታሪክና በዘመን ቀደምት የሆነችው አገራቸው በዘመናዊው ዓለም ስልጣኔና ዕውቀት ከኋላ ከቀሩ የመጨረሻዎቹ የኣለም አገራት መካከል የምትጠቀስ መሆኗን በማወቃቸው በኃይለኛ ቁጭትና እልህ የሚተጉበት መሆኑን ብዙዎች ይመስክራሉ፡፡
ይህን እና ሌሎችንም ምክንያቶች ተከትሎ፣ በውስጥ እና በውጭ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ እመርታ በአገሪቱ በመታየቱ፤ የንጉሠ ነገሥቱ መንግስት የዓለምን መገናኛ ብዙኃን አትኩሮት ከመሳባቸውም በላይ፤ አያሌ የአውሮፓና አሜሪካ አገራት መሪዎችን አክብሮት የተቀዳጁበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር አገሪቱ በልዩ ልዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ስሟ በተደጋጋሚ የሚጠራ በመሆኑ፤ ይህን የሚመጥን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ስልት መከተልና ማዘመን ያስፈልግ እንደነበር ገፊ ምክንያች እየበዙ መጡ፡፡ ስለሆነም፣ በውጭ ያለውን አገራዊ ትኩረትና ዲፕማሲያዊ ጫናዎችን የሚቋቋሙና በድል የሚወጡ፣ በትምህርት፣ በትጋት፣ በአገር ፍቅርና በሥራ ወዳድነታቸው የተመረጡ ተከባሪ የአገር ልጆች በባትሪ የሚፈለጉበት ሆነ፡፡
ከእነዚህ ታሪክን ሰርተውና ቀርጸው የአገራቸውን ክብርና ጥቅም ከማናቸውም ጥቅምና ክብር አስበልጠው የወደዱት የማርታ ገብረጻዲቅ ትውልድ ታሪክ ተጋሪዎች፣ በሰሩት አኩሪ ተግባርና በተወጡት ከባድ ኃለፊነት ያተሙት ዘላለማዊ ተግባር ለዛሬውም የአገራችን የውጭ ፖሊሲና አቅጣጫ ፈር ቀዳጅ ከመሆን ያለፈ አስተዋጽዎ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ክብርና ሞገስ ለእኝህ ኩሩና ብልህ የአገራችን ዜጎች ሁሉ እንዲሆን እንመኛለን፡፡
ወ/ሮ ማርታ ገብረጻዲቅ፤ በዚህ ልዩና በታሪክ ፊት ከፍተኛውን ሞገስ በተላበሰ አገራዊ ጥሪ ወቅት፤ ከንጉሰ ነግስት ቀዳማዊ ኃለ ሥላሴ ዘንድ፤ ወቅቱንና ዘመኑን የሚዋጅ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀረበላቸው፡፡ ጥሪው አስደሳችም፤ ፈተና የበዛበትና ግዳጁም የዋዛ እንዳልሆነና የበረታ አደራና እልህ ያለው መሆኑ ግን ይታወቃል፡፡
“ሴት ነኝ፣ የቤተሰብና የሙት ልጆች እናት ነኝ” በሚሉ ደካማ በሚመስሉ የፍርሃት ውሳኔዎች ወደ ኃቻው ሳያፈገፍጉ ለታጩበት ከፍተኛ የኃላፊነትና የሹመት ተግባር እራሳቸውን አበቁ፡፡ ጥሪውንም በአክብሮት ተቀበሉ።
በዚህ ዝግጅታቸው የተደነቁት የቅርብና የሩቅ የሥራ ኃላፊዎቻቸው በወ/ሮ ማርታ ላይ ያላውን እምነትና ተስፋ አፀኑ፡፡ በሙያቸውና በዕውቀታቸው የተከበሩት ወይዘሮ ማርታ በያዙት ኃላፊነት ላይ ሌሎች ተጨማሪ የሥራ ክፍሎችንና ኃላፊነቶችን እየጨመሩ፣ በሥራ ላይ ሥራ እያበዙ፣ ከነበሩበተረ ደረጃ ባልተገመተ ብስለትና ፍጥነት እጅግ ሩቅ ሆኖ ይታዩ የነበሩትን የሥራ ድርሻዎችን በከፍተኛ ኃላፊነት ይመሩ ጀመር፡፡
ጊዜውና ወቅቱ ይጠይቅ የነበረውን ብስለት የተቀዳጁት ብርቱዋና ታታሪዋ ሴት ወይዘሮ ማርታ ግብረ ጻድቅ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊነታቸው ወቅት፤ እጅግ ከፍተኛ የሆኑ የመንግስት የሥራ ድርሻዎችን ያከናውኑ የነበር ሲሆን፤ በዚህም አገልግሎታቸው ከውስጥ ከውጭ አገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በቅርብ የመገናኘት ዕድል አግኝተዋል።
አገልግሎታቸው ልባቸውን ያረካውና የተደሰቱባቸው የሥራ አለቆቻቸውም ከባድና ከፍተኛ ትርጉም ያላውን የስራ ድርሻዎች ለወ/ሮ ማርታ መስጠትና በእርሳቸው በኩል እንዲከናወኑ ማስቻልን ይመርጡ ጀመር፡፡
በዚህም ምክንያት አያሌ ዓለም አቀፍ ታዋቂ ሰዎች፣ የአገራት መሪዎች፣ መንግስታት ወኪሎች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ የፕሮቶኮል ሹሞችና ኃላፊዎችን መገናኘት የዕለት ከለት ስራቸው ሆነ፡፡ ይህም ወቅት ለአገራቸው ሊሰጡት ከሚችሉት አገልግሎትና ተግባር ውስጥ የሕይወታቸው ከፍተኛው ቢሆንም ፤ ገና ጅማሬው እንጂ ማብቂያው እንዳልሆነ ልባቸው ይነገራቸው ነበር፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በሥራ ቆይታቸው ፤ በእርሳቸው አገለግሎትን ያገኙና በቅርብ ይገኛኗቸው ከነበሩ ዓለም አቀፍ ሰዎች መካከል በታሪክና በዘመን በልዩ ልዩ ምክንያት ተጠቃሽ ከሆኑት መካል ጥቂቶቹ፦
- የዩጐዝላቪያ ኘሬዚደንት ማርሻል ብሮዝ ቲቶን፣
- የእንግሊዟን ልዕልት ኤልሳቤጥን ልጅ ልዕልት አንን፣
- የዛምቢያ ኘሬዚደንት ኬነት ካውንዳን ባለቤት፣
- የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢንድራ ጋንዲ፣
- የፓኪስታን ኘሬዚደንት አሊ ቡቶ እና ባለቤታቸውን፣
- የአሜሪካውን ኘሬዚደንት ጆን ኦፍ ኬኔዲን ባለቤት ጃኩሊን ኬነዲ በቀድሞው አጠራር የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው አጠራር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተብሎ የሚጠራው እና ስድስት ኪሎ የሚገኘውን ኬኔዲ ላይብረሪ ለመመረቅ በመጡበት ወቅት ተቀብለው አስተናግደዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ልዩ ልዩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ኢትዮጵያን በመወከል ከፍተኛ ልዑካንን ይዘው የአገራቸውን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ ለዚሁም ጉዳይ ሲባል አብዝተው ወደ ውጭ የሚጓዙ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ በጉዟቸው ወቅት የሚያገጥማቸውን ዕድሎች ሁሉ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው እንዲያውል ከፍ ያለ አስቷጽዎ አበርክተዋል፡፡ ጣሊያን፣ እስራኤል፣ ራሺያ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ሌሎችም የአውሮፓና የአሜሪካ እንዲሁም የእስያ አገራት የጉዟቸው መዳረሻዎች ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ማርታ ለሰሪ ለሴቶች ከሚሰጡት ቦታ የተነሣ ራሽያ በሄዱበት ጊዜ የመጀመሪያዋ የሩሲያ ሴት ጠፈርተኛ (Valintin Tereshooven) ቫለንቲን ትረስሆቭን አግኝተው አነጋግረዋል።
በዚህ መሐል ከአሁኑ ባለቤታቸው ከአቶ ደመቀ ተክለወልድ ጋር ጋብቻን መሰረቱ፡፡ አቶ ደመቀ ተክለወልድና ወ/ሮ ማርታ ገብረጻዲቅ እውቀታቸውና ግንኙነታቸው፣ ገና በለጋው ዕድሜያኧቸው በሰው አገር በተማሪነት እያሉ ነበር፡፡ ያኔ በአገረ አሜሪካ በተማሪነት ጊዜ፣ የአገር ልጅ ፊቱና ድምጹ ከእህል ውሃ በላይ በሚናፍቅበት ጊዜ፣ አይዘህ በርታ - አይዞሽ በርቺ ተባብለው የተደጋገፉና ለውጤት የበቁ ከመሆቸውም በላይ፤ ወደ ሚወዷት የትውልድ አገራቸውም አብረው ተመልሰዋል፡፡
በኋላም ወ/ሮ ማርታ የመጀመሪያ ባለቤታቸውን በሞት ሲነጠቁ፤ አቶ ደመቀ ተክለወልድ የቅርብ አጽናኚያቸው ብቻ ሳይሆኑ፤ የልጆቹም የቅርብ ቤተሰብና ተመልካች ነበሩ፡፡ በሕይወታቸው ሲደጋገፉ የኖሩት እነኚህ የአንድ ልብ ቀለም ባለቤቶችና እድለኞች ኑሮኧቸውንም በአንድ ጣሪያ ስር መስርተው ኃይላቸውን አጠናከሩ፡፡ አቶ ደመቀ እንደ ወ/ሮ ማርታ ሁሉ በትምህርታቸው ከፍተኘውን ደረጃ የጨበጡ ብቻ ሳይሆን፤ በአገራቸው ልዩ ልዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡
እ.አ.አ. በ1967 ዓ.ም. በካናዳ ሞንትሪያል ለተዘጋጀው የዓለም አቀፍ ኤክስፖ ኢትዮጵያ ላደረገችው ታላቅ ተሳትፎ ወ/ሮ ማርታ እና ባለቤታቸው አቶ ደመቀ በንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ትዕዛዝ የኢትዮጽያ ፓቪሊዮን ያገራችንን ገጽታ በሚያሳይ መልኩ አስገንብተውና የኤክስፖው ተሳታፊ ሆነው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል፡፡ ለዚህም ከፍ ያለ ምስጋናና ክብር አግኝተውበታል፡፡
በሕይወት ዓላማ ከፍታ ውስጥ ….
ወይዘሮ ማርታ ገብረጻዲቅ ከባለቤታቸው ከአቶ ደመቀ ተክለወልድ ጋር በትዳር ከተጣመሩ በኋላ ፤ በሁለቱም ላይ ከፍ ያለ የሕይወትና የኑሮ ዓላማ ታይቷል፡፡ ሁለቱ የረዥም ጊዜ ወዳጆች በአንድ ጣሪያ ስር በፍቅርና በልዩ መተሳሰብ መኖር ከጀመሩ በኋላ ያለው ሕይወታቸው የትዳር አጋራቸው የአቶ ደመቀ ተክለወልድ ድጋፍና በርቺ ባይነት ሳይለያቸው፤ በታላቅ ትህትና ‹‹እመቤቴ›› ብለው እየጠሩ ያሞካሽተዋቸዋል፡፡ “ልባምን ሴት ማን ያገኛታል? ቢባል አቶ ደመቀ ማለት ማጋነን አይሆንም። በእውነት! በትዳር ሕይወታቸው መልካም ምሳሌዎቻችን ናቸው።
ወይዘሮ ማርታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሥራ ኃላፊነታቸው በነበሩበት ጊዜ ያላቸውን የስራ ግንኙነትና ፍቃድ በመጠቀም ለአገራቸው ሴቶች አንጸባራቂ የለውጥ ኃይል ለመሆን የቻሉ ሲሆን፤ በጠቅላላው ለአገራቸው የማህበራዊና የኢኮኖሚ ከዚያም አለፍ ሲል በፖሊቲካዊ እይታ ሊገነባ የሚችል የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣና በፆታ ላይ ያለውን ግምት ከስሩ ሊነቅል የሚችል መድኃኒት ለማበርከት ችለዋል፡፡
ወይዘሮ ማርታ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት የፓርላማ ዘመን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትን የተቀላቀሉ የመጀመሪያዋና ብቸኛዋ ሴት ሴናተር ለመሆን የበቁ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ለመሆን ችለዋል፡፡ ይኸው ሥልጣን በዘመኑ አጠራር ግልጽ ለማድረግ ‹‹የሴናተርንት›› ሥልጣንና ኃላፊነት ሲሆን፤ በዚህም የሥራ ዘመናቸው እስከአሁን ድረስ በታሪክ የተጠቀሰ ብቸኛ ሴት ተመራጭ ለመሆን አስችሏቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፓርላማ ታሪክ መዝገብ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል (ሴናተር) የነበሩት ወይዘሮ ማርታ ገብረ ጻዲቅ፤ በምክር ቤት ቆይታቸው ሊሰሯቸው ያቀዱት አራት ዋና ዋና ተግባራት መኖራቸውን እርሳቸው እራሳቸው ዛሬም ድረስ ያስታውሳሉ፡፡
ይህን ታሪካዊ ኃላፊነትና ይሁንታን ያገኙት ሴት ወይዘሮ ታታሪዋና የሕይወታቸውን ገጽ እራሳቸው በትግላቸው የጻፉት ወይዘሮ ማርታ፤ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ይታዩ የነበሩትን የማህበራዊ ድህነትና ጉስቁልና መቅረፍ ላይ ያተኮሩ ሁለት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በሕግ ለማጽደቅና ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሌሎች ሁለት ልዩና አስፈላጊ የነበሩትን ኢኮኖሚያዊና ማህበረ-ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድም አቅጣጫና ፖሊሲ እንዲሰራላቸው አስቀድሞ በምክር ቤቱ ይሁንታን ማግኘት ነበረባቸውና ለእነዚህም ተግባራዊነት አጥብቀው ይተጉ ጀመር፡፡
ወይዘሮ ማርታ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላነት ዘመናቸው (ሴናተርነት ሹመታቸው) ወቅት ሊሰሩት የፈለጉት አራት መሰረታዊ የአገራችን ማህበረ-ኢኮኖሚያዎና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ኃይልና ስልጣን የሚሰጡ አዋጆችን ለማፀደቅ ከተጉባቸው ተግባራት መካከል ፡-
- የአልኮል መጠጥን ዋጋና መጠንን መወሰን
- የማደጎ ልጆችን የገቢ ማሰባሰብ ተግባራት
- በጎዳና ላይ በልመና ተግባራት የተሰማሩና የሚተዳደሩ ሰዎችን ዘላቂ የሥራ ዕድል ለማስገኘት የሚችሉ ሕግጋትን ማጸደቅ
- የግብር ሕግ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ወይዘሮ ማርታ በአብዛኛው ጊዜ ወደ ውጭ አገራት ለሥራ በሚዘዋወሩበት በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስተናጋጆች የስራ እድል የነበራቸውና በሥራው ላይ የተሰማሩት ሴቶች በሙሉ የውጭ አገራት ሴቶች መሆናቸው በእጅጉ ያስቆጫቸው ነበር፡፡ የአገራቸው ሎጋና ቆነጃጅት ቅምጥል ሴቶች እያሉ፣ ታይተውና የማይጠገቡት የአገራቸው ሴቶች ልጆች በምድራቸው ላይ በታላቅ ነጻነትና ውበት እየተፍለቀለቁ ሲሄዱ ማማራቸውን እያሰቡ፣ …. ስለምን የአገር ሃብትና ገንዘብ ከሁሉም በላይ የሆነው የማንነትና የአደርገዋለሁ ይቻላል አስተሳሰብ ኃላ ቀርነት ይገዛናል ሲሉ ይቆጩና ያሳስባቸው የነበሩ ሴት ናቸው፡፡
በዚህም ምክንያት፤ በሄዱበት ሁሉ ያይዋቸውን ቆነጃጅት ሎጋና መልከ መልካም ሴቶች ሁሉ እያግባቡና እያስተማሩ / እያስረዱ ወደ አውሮፕላን የበረራ አስተናጋጃነት ስራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ችለዋል፡፡ ይህ በመሆኑ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ የሆኑትን ኢትዮጵየሰውያን ሴት የበረራ አስተናጋጆችን ለማፍራት የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፤ በጊዜው ብቻ ሳይሆን አሁን ድረስ ከበዛ የአገር ሃብት ብክነትና ወጪ ሊታደግ የተቻለውን ታላቅ ስራ ሊጎናጸፍ በቅትዋል፡፡፡
ወይዘሮ ማርታ ፤ ይህ በጉዞአቸው ላይ የውጭ አገራትን ዜጎች የበራራ ማስተናገድ ሥራ በአገራቸው አውሮፕላን ላይ ማየታቸው ያመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ ፤ ቀጥሎ ወዳለው ከፍተኛ ሕይወትና የዓላማ ፅናት የተንፀባረቀበት የከፍተኛ መንግስት ሥራ አስፈጻሚነት ሚና እንዲኖራቸውና የተሻለ አበርክቶ ሊወጡ እንደሚችሉ አንድ አቅጣጫ ጠቋሚ ሊሆን የሚችል ብርሃን የሆናቸው መሆኑን አንዳንዶች ይነገራሉ፡፡
በዚህ አታካችና ያላሰለሰ ጥረት በሚጠይቅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትግልን ትኩረት ባደረገ ማህራበራዊ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ የታቀደ ከፍ ያለ ስራና ኃለፊነት ውስጥ እያሉ፤ ታሪካዊው የኢትዮጵያ አብዮት መጣሁ ደረስኩ ሲል ቆይቶ ፤ ነገሩ ሁሉ የሕልም ዓለም፤ የቁም ቅዠት መሳይ ሆነ፡፡
ይህ ሌላኛው የወይዘሮ ማርታ የሕይወት ፈተና የሚጀምርበት፤ ሕይወታቸው በሌላ ገጽና መልክ የሚጻፍበትን ቀለም የሚያበጅበት፤ ፈተናው እና የአልሸነፍም ባይነት ትግሉ ከራስ አልፎ ለበርካታ ሺህ ዜጎችና ተከታታይ ትውልዶች የሚተርፍ ጸጋን የሚታደሉበት ምዕራፈ ሊሆን አሃዱ አለ፡፡
በርግጥ ሲያወሱ፤ እንዲህ ሲጽፉት ሊቀል ይችል ይሆን …. ወይስ፣ ያለፉት ዳገትና ቁልቁለት ለመተረክ ሲበቁ ለአፍ ዳገት የለውም የሚለው ተረት ይረሳ ይሆን …. ስደት … የታላቅ ራዕይ ጥንስስ …. እኔም አገር አለኝ … ናፍቆትና ሥጋት ….
በ1960ዎቹ እንደ ወይዘሮ ማርታ እና እንደ አቶ ደመቀ ያሉት ምሁራን ጎልማሶች፤ ባካበቱት እውቀትና ልምድ አገራቸው ለተሻለ ዓላማና ግዳጅ ልትፈቅዳቸው ሲገባ፤ ለሕይወታቸው አስጊ የሆኑ ክስተቶች መኖራቸውን ለማወቅ ተቻለ፡፡
በንጉሡ ዘመን ከከፍተኛ ባለሥልጣኖች ጋር በነበራቸው የሥራ ግንኙነት እና የሥራ ድርሻ ምክንያት የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) በ1967 ዓ.ም. ወ/ሮ ማርታንና ባለቤታቸው አቶ ደመቀ ተ/ወልድን ለእስር ሊዳርጋቸው እንደሆነ መረጃው በሚቀርቡዋቸው ወዳጆች አማካይነት ተነገራቸው፡፡ ይህን መርዶ የሰሙት ባለትዳሮች ሁለት ጊዜ ማሰብ አልፈለጉም፡፡ ምክንያም ሌሎች በርካታ ሰዎች በዚህ ዓይነቱ ውሳኔ ምን ዓይነት በደል እንደደረሰባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉና እለቱን ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ በሌሊት ያላቸውን ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት ጥለው ከአዲስ አበባ ተነስተው የሰባት ቀን አድካሚ ጉዞ በማድረግ ወደኬንያ ተሰደዱ፡፡ በልጅነት ዕድሜ ትተውት ከመጡት ስደት ፤ በጉልምሳና ዕድሜ ላይ ማረፊያቸውን በሚያዘጋጁበት ወቅት ፤ አስከፊ የስደትን ሕይወት ለመጀመር ተዳርጉ።
ኬንያ በቆዩበት ወቅት የደርግ ወታደራዊ አገዛዝን ለማምለጥ በጠረፍ በኩል በእግር ጉዞ የሄዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት እና ችግር ሲመለከቱ፤ የራሳቸውን ችግር እንዲረሱና ስለወገኖቻቸው ሥቃይ እንዲያስቡ አደረጋቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ወገኖች በቻሉት ሁሉ ለመርዳት ወስነው ይህን ሃሳባቸውን ከግቡ ለማድረስ ለረዥም ጊዜ እንዲያስቡበት ያደረጋቸው ሲሆን፤ በሚቻላቸው ሁሉ ስደተኛ ወገናቸውን ከመደገፍና ከማገዝ ቦዝነው አያውቁም ነበር፡፡
ከኬንያ የስደት ቆይታ ወደ ግሪክ ሌላ የስደት ሕይወት አመሩ፡፡ በግሪክ ቆይታቸው ላይ ዘላቂ የሆኑና እስከአሁንም ድረስ የተተገበሩ እና በመተግበር ላይ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ሰብዓዊ ተግባራትና ስራዎችን ለመጀመር ቻሉ፡፡ ቀደም ሲል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃለፊነታቸው ወቅት በሥራ ከተዋወቋቸውና ወዳጅ ከሆኗቸው ወገኖች ጋር በመገናኘት፤ ተቋማዊ ቅርጽ ያለውና ለበርካታ አፍሪካውያን ስደተኛ ምንዱባኖች መድሕን ሊሆን የሚችል የድጋፍ ሰጪ የተራድዖ ድርጅትንና አላማን ለመፀነስ የበቁ ሲሆን፤ ይኸው ዛሬም ድረስ ይህ ፅንሰት ተወልዶ አድጎና ጎልምሶ ለበርካታ ሺህ ሰዎች ድጋፍ ሊቆም የቻለ ሊሆን በቃ፡፡
ፕሮጀክት ሜርሲ … ምስረታና እድገት …
በዚህ ቁንጽል የሆነ የታሪክ ዘጋቢ ሰነድ መግቢያ ጽሁፍ ላይ የተጠቀሰው ኒውሮሎጂስቱ ደክተር አብዲ ኤርመሎ የፕሮጀክት ሜርሲ ውጤት ነው፡፡ ፕሮጀከት ሜርሲ በአሜሪካን አገር የተወለደ፣ ፅንሰትና ሂደቱ ግን በስደት ሕይወት ከኬንያ በጀመረ ግንዛቤና አትኩሮት በግሪክ የታለመ ታላቅ ራዕይና ዓላማ ነው፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካት ወይዘሮ ማርታ እና አቶ ደመቀ ቀን ከሌት ያለ ድካምና መሰለቸት የታተሩ ሲሆን፤ የደግ ኃሳብ ምንጭ የሆነው ጌታ መድኃኒዓለም ለዘላለማዊ ክብር እንዲበቃ ባርኮታል ሲሉ ብዙዎች ቅዱስ ኣላማውን ቅድስና ይደግፉታል፡፡
ስደተኞቹ ባለትዳሮች ወይዘሮ ማርታ እና አቶ ደመቀ ከግሪክ ቆይታቸው በኋላ ሕይወታቸውን ወደ አሜሪካ በማቅናት መሰረቱ፡፡ ይህ ስደት ግን የመጨረሻው ስደት ሊሆ እንደሚገባ በልባቸው ወስነዋል፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ኑሮና ሕይወቱ በምርጫው የሚወሰን በመሆኑ እንጂ፤ አሜሪካ የመጨረሻው የመኖሪያ ፍላጎታቸው በመሆኗ ሕይታቸውን አሳልፈው የሚሰጧት አገር አልነበረችም፡፡
በአሜሪካ የዳግም የጉልምስና ዘመን ስደታቸው ወቅት ሁለቱ ታታሪዎች በልዩ ልዩ ሙያዎች ተሰማርተው ያገለገሉና ኑሮን ለለማሸነፍ የጣሩ ከመሆቸው በላይ፤ ሕይወታቸው ለሌሎች የተሰጠ ነውና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የተቸገሩትን ለመርዳትና ለመደገፍ፤ ተስፋ እና ብርታት ለመሆን፤ የተበላሸውን ለመጠገን ምክነያትና ሰበብ ለመሆን በፀሎታቸውም ሆነ በሕይወታቸው ከመጣር በቀር ሰንፈው አያውቁም ነበር፡፡
እንዲህ ለመሆን የዘወትር ሥራቸውን ለመስራት ባሻገር ለሌሎች ሊኖራቸው የሚችለውን አስተዋጽዎ በምን መልኩ ሊያደርጉት እንደሚገባ በተለይ የወይዘሮ ማርታ ልብና ነብስ ቀን ከሌት ሲሟገቱ ውለው ያድሩ ጀመር፡፡ እነርሱ ሕይወትን ለማሸነፍ በምድረ አሜሪካ ፡-
As President, ITG, Inc.
Vice President, Hel-Mar. Inc
Board of Trustees, Taylor University, Indiana
Board of Director, Refugees Int’l, Washington, DC
በእነዚህ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በልዩ ልዩ ሃላፊነቶች ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ፕሮጀክት ሜርሲ ከኃሳብ ወደ ዕውን ሕይወት ተሸጋገረ፡፡ የቤታቸውን ሕይወት በአብዛኛው አቶ ደመቀ በሚሸፍኑት የገቢ ምንጭ የሚተዳደረው ቤተሰብ፤ በወይዘሮ ማርታ ሌሎችን ሰዎች የጉስቁልና ሕይወት ለመታደግ እረrፍት ማጣት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት ሙሉ ቃል ኪዳን ሰጥቶ አጋር ወዳጆችን በማሰባሰብ ወደ ተግባዊ እንቅስቃሴ ተዘዋወረ፡፡ ወይም ሕይወታዊ ሥራ ተጀመረ፡፡ ፕሮጀከትሜርሲ በ1977 ዓ.ም. እ.ኤአ. በይፋ ተመሰረተ፡፡
የፕሮጀክት ሜርሲ ዓላማ ስደተኞች በሚበዙባቸውና በተለይም የትምህርት ዕድል ያልነበራቸውን ትምህርት እንዲያገኙ በሱዳን፣ ጁቡቲ፣ ጊኒ፣ ኬንያ፣ አይቮሪኮስት እና ማላዊ በመሳሰሉ አገሮች ላይ አልሚ ምግብ በመላክና አንዳንድ ቦታ ላይም ት/ቤት በማቋቋም የበጎ አድራጎት ሥራዎችን መሥራት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ረሀብ በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ያንዣብብ ስለነበር ኢትዮጵያም በእጅጉ በድርቅ የተመታችበት ወቅት ስለነበረ ሕፃናትን ለመታደግ ወ/ሮ ማርታ "አጥሚት" የሚባለውን አልሚ ምግብ አስተዋወቁ፡፡ በአሜሪካን አገር የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ድርጅት ታይቶ ዕውቅና እንዲሰጠው ለማድረግ በመቻሉ በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የ1977 ድርቅ ወቅት አጥሚት በመላክ የብዙ ሰው ህይወትን ማዳን ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደተለያዩ 30 አገራት አጥሚት በመላክ የህፃናትን ሕይወት በመታደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ተደርጓል፡፡ በዚሁ የድርቅ ወቅት የታረዙትን ለማልበስም በአሜሪካን ሀገር ማረሚያ ቤት ያሉ ታራሚዎች የኢትዮጵያውያንን ባህል በሚመጥን መልኩና ገጽታችንን ባስጠበቀ ሁኔታ ልብስ በማሰፋት እርዳታ አድርገዋል።
በኋላም የደርግ መንግሥት ሲወድቅ በታላቅ ጉጉት ሲናፍቁት ወደነበረው አገራቸው መጥተው በውጭ ቆይታቸው ሕይወትን ለመታደግ ሲያደርጉ የቆዩትን የሕይወት አድን ዕርዳታ ሥራን (relief work) በኢትዮጵያ በማሸጋገር ዘላቂነት የሚኖረውንና ህብረተሰቡ ራሱን ለመርዳት የሚያስችለውን ስልት በመቀየስ ለመስራት ሲንቀሳቀሱ ወደተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ለመዘዋወር ጥናት እያካሄዱ ሳለ ቀድሞ ከሚያውቋቸው ሰዎች መካከል በተለይም ከጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ያሉ ሽማግሌዎች መሬት እናቅርብና የትምህርት ቤትና የጤና አገልግሎት እንድናገኝ እርዱን ብለው ወ/ሮ ማርታንና አቶ ደመቀን በተደጋጋሚ በመቅረብ ለማሳመን ሞከሩ፡፡
በመሆኑም በመስቃን ወረዳ የተቦን ቀበሌ ከ1ኛ - 2ኛ ክፍል ባሰሩት ዘመናዊ ት/ቤት 355 ተማሪዎችን ተቀብለው የአካባቢው ህብረተሰብ ልጆች ትምህርት እንዲያገኙ አደረጉ፡፡ ትምህርት ቤት ለአካባቢው የመጀመሪያው ስለነበር የህዝቡ ደስታ ከፍተኛ ሆኖ መሬት ከመስጠታቸውም ሌላ ሽማግሌዎቹ እየተመላለሱ በተጨማሪም የጤና አገልገሎት ለማግኘት ስለሚቻልበት ሁኔታ መጠየቁን ተያያዙት፡፡
ይህንኑ መነሻ በማድረግ ወ/ሮ ማርታ ገ/ፃዲቅና ባለቤታቸው አቶ ደመቀ ተክለወልድ ከት/ቤቱ ጐን ለጐን የጤና ክሊኒክ አቋቁመው ተማሪዎች እንዲጠቀሙበት አደረጉ፡፡ ይህ በእንዲህ ላይ እያለ ተማሪዎች ከክፍል መቅረት አንዳንዱ ደግሞ ክፍል ውስጥ ትምህርት የመቀበል ፍላጎቱ የቀነሰ ሆኖ ስለተገኘ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት ችግሩን ለመቅረፍ ለተማሪዎች ምግብ አዘጋጅቶ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለተማሪዎች የምገባ ኘሮግራም ተጀምሮ ላለፉት በርካታ ዓመታት ድርጅቱ ተማሪዎቹን እየመገበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በተማሪዎች የምገባ ኘሮግራም ከKG-8ኛ ክፍል የሚማሩ 1500 ሕፃናት እና ተማሪዎች የተመጣጠነ የቁርስና ምሣ ምገባ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
በዚህ ሁኔታ በኘሮጀክት ሜርሲ ከተመሠረተው ትምህርት ቤት ጥሩ እውቀትን ገብይተው ለቁም ነገር የበቁ በርካታ ምሁራን አገራቸውን በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 28 ኢንጅነሮች (የሲቪል፣ ኤልክትሪካል፣ መካኒካል) ከ30 በላይ የጤና ባለሙያዎች (ኒዮሮሰርጂን፣ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ የጤና አፊሰሮች፣ የላቦራቶሪ ቴክኒሻኖች፣ ፋርማሲስቶች) ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በድርጅቱ ከሚሠሩ ከ300 በላይ ቋሚ ሠራተኞች አንድ አራተኛው ገደማ በኘሮጀክት ሜርሲ ኘሮግራሞች በማስተማር፣ በሆስፒታል ባለሙያነትና ተቀጣሪነት፣ በአስተዳደር፣ በግብርናው ዘርፍና በመሳሰሉት ላይ እየሰሩ የተወለዱበትን ህብረተሰብ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ኘሮጀክት ሜርሲ የአካባቢውን ህብረተሰብ ሕይወት ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ለመቀየር እና ራሱን በራሱ እንዲረዳ ለማስቻል በአምስት ዘርፎች ማለትም በትምህርት፣ ጤና፣ መሠረተ-ልማት፣ የምግብ ዋስትና፣ የሙያ ክህሎት ወይም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚሉ እርስ በርስ ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ በሆኑ የተቀናጀ የልማት ሥራዎች በመሰማራት ላለፉት 30 ዓመታት በሺ የሚቆጠሩ የህብረተሰቡ አባላትን በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ሥራውን በጀመረበት በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በትምህርት ዘርፍ ከKG- 12ኛ ክፍል በማቋቋም፣ በጤናው ዘርፍ የተማሪዎች ክሊኒክ እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመክፈት፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በማቋቋም፣ በመሠረተ-ልማት ረገድ ድልድይና መንገድ በመስራት፣ እንዲሁም 15 ኪ/ሜ ርዝመት ባለው መንገድ ላይ ላለው 30,000 የሚገመት ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ውኃ በማቅረብ የአካባቢውን ህብረተሰብ ህይወት እንዲሻሻል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማስፋት እና በማጠናከር እየሠራ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረ-ብርሃን 17 ኪ/ሜ ወዲህ ባለው ጫጫ ከተማ የወተት ላም ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል አቋቁሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የወተት ምርታቸውን በማሳደግ ለራሳቸው እና ልጆቻቸው ወተት እንዲያገኙና ከዚያ የሚተርፈውን ለገበያ አውጥተው ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ በመቀየስ ገበሬውን ተጠቃሚ በሚያደርግ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡
ኘሮጀክት ሜርሲ ከመንግሥት ጋር ውል ገብቶ የሕብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል ከሚያደርጋቸው የልማት እና የበጎ አድራጎት ሥራዎች በተጨማሪ ሁኔታዎችን እያየና ወይም በህብረተሰቡ ሲጠየቅ፣ ለትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ፣ ለጤና ማሻሻያ እንዲሁም ሌሎች የመሠረተ-ልማት ፍላጎቶችን አስተናግዷል፡፡ ቀደም ባለውም ጊዜ በአፋር፣ በትግራይ እና በሰሜን ሸዋ አሳግርት ላይ ትምህርት ቤቶችን አስገንበቶ አስረክቧል፡፡
ሰብዓዊ ድርጊቶች
ወ/ሮ ማርታ ገ/ፃዲቅ በተፈጥሮአቸው ሩህሩህ እና ለሰው አዛኝ ከመሆናቸው የተነሳ ይህን የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት ከማቋቋማቸው በፊት ጀምሮ የአቅመ-ደካማ ዘመዶቻቸውና የዕውቅ ቤተሰብ ልጆችን አስተምረው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል፡፡ ውጭ አገር አሜሪካ ድረስ በመላክም ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት እንዲበቁ አስችለዋል፡፡
ወ/ሮ ማርታና ባለቤታቸው አቶ ደመቀ በአገራችን በመንግሥት ሥራ በነበሩባቸው ወቅት ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ በበርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ በገንዘብ ማሰባሰብ፣ የውጭ ድጋፍ በማፈላለግና በማማከር የተሳተፉ ሲሆን በዚህ ረገድ ከተሳተፉባቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል የወጣት ሴቶች ክርስቲያን ማህበር (YWCA) ቀይ መስቀል ማህበር፣ ቼሻየር ሆም ይገኙበታል፡፡
ወ/ሮ ማርታ በሄዱበት ሁሉ የሚያጋጥማቸውን አሳዛኝ ክስተቶች ችላ ብለው ማለፍ አይሆንላቸውም፡፡ ለአብነት ያህል አንዲት ልጅ ሕፃን ወንድሟ በእግር መሄድ ስላልቻለ በጀርባዋ አዝላው በየቀኑ ስትመላለስ መንገድ ላይ ሲያገኟት ልጁን ወደ ድርጅቱ ግቢ እንድትወስደውና በየቀኑ ወተት እንዲጠጣና ትምህርቱን እንዲማር ምግብም እንዲመገብ በማድረግ ጤናው እንዲሻሻልና ልጁም ቆሞ እንዲሄድ አስችለውታል፡፡
ዛሬ ይኸ ልጅ ትምህርቱን በዲግሪ ደረጃ ጨርሶ በድርጅቱ ሆስፒታል ተቀጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ አባቱም ከድርጅቱ ምስረታ ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት በላይ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌላ አንድ ልጅ ወደ ሆስፒታል ዘመድ ለመጠየቅ ሄደው ከጐን ተኝቶ ሲያገኙት ምን እንደሆነ ጠየቁትና ከምሰሶ ላይ የወደቀ የኤሌክትሪክ ኬብል ነክቶ ሰውነቱን የጐዳውና በዚሁ ምክንያት ሁለቱም እግሮቹን ለማንቀሳቀስ እንደማይችል ሲነግራቸው ወደ ድርጅታቸው በማምጣት ዊልቸር ተሰጥቶት ትምህርት እንዲማር ተደርጎ ይኸው ዛሬ ትምህርቱን ከ12ኛ ክፍል ሊያጠናቅቅ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ሌሎችም በእሳት ቃጠሎ፣ በልብ ሕመም፣ በቲውመር እንዲሁም በሌላ ቤተሰቦቻቸው ለህክምና መክፈል ሳይችሉ ወይም በአገር ውስጥ የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ውጭ አገር ድረስ እንዲሄዱና እንዲታከሙ በማድረግ በሕይወት የተረፉ የቀድሞ ታማሚዎች አሁን ጤነኛ ሆነው ሕይወታቸውን በደስታ እየመሩ ያሉ ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባል ተረጂዎች አሉ፡፡
ወ/ሮ ማርታ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኢንተርቪው ላይ ችግሮች ሲገጥማቸው በምን ሁኔታ እንደሚፈቱት ተጠይቀው ሲመልሱ "እኔ ችግሮችን አልፈራቸውም እንዲያውም የመፍትሔ ሃሳብ አማራጮች እየበዙ ያስቸግረኛል እንጂ" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በአገራችን በተለያየ ወቅት በተከሰቱ የድርቅና ረሃብ ወቅቶች በወረዳዎች፣ በዞኖች እና በክልል ደረጃ አልፎም በአገር አቀፍ ደረጃ ከውጭ ዕርዳታ እንዲገባ በማመቻቸት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በአንድ ወቅት በተከሰተ ከፍተኛ ድርቅ ከወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር በኘሮጀክት ሜርሲ ቅጥር ግቢ፣ በማረቆ፣ በስልጤ፣ በሶዶ ኬላ የማገገሚያ ጣቢያዎችን (Therapeutic Centers) በማቋቋም አጥሚት እና ሌሎች አልሚ ምግቦችን ለህፃናት በማደል ህይወት አድን ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡
ማርታና ደሜ
ማርታና ደሜ የሚለው አነጋገር ብዙውን ጊዜ በውጭ አገር ኑሮአቸው ዘመን ፈረንጆቹ ጥንዶቹን ለማቆላመጥ በሚመስል መልኩ ማርታና ደሜ (ማርታና ደመቀ ለማለት ነው) ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ ይህም የሁለቱን ባልና ሚስት ቅርርቦሽና ፍቅር በይበልጥ ሊገልጥልን ስለሚችል ማርታና ደሜ ብለን የሁለቱን የፍቅር ህይወት ባጭሩ እንድንቃኝ ይረዳናል፡፡
ማርታና ደሜ ከተለመደው የባልና ሚስት ግንኙነት ለየት ባለ ሁኔታ የሚገለጽ ነው፡፡ ወ/ሮ ማርታ ባለቤታቸውን "ጌታዬ" ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ደመቀ ባለቤታቸውን "እመቤቴ" ይሏቸዋል፡፡ ይህ አጠራር ቦታ እና ወቅት አይለይም፡፡ ወደ ገበያ ቢሄዱ፣ በእንግዶች መሐል ቢሆኑ፣ ብቻቸውን ቢወያዩ፣ ጓደኞቻቸውና አብሮ አደጋቸው ጋር ሲሆኑ ወይም የውጭ አገር እንግዶች ቢገኙ ይህ "ጌታዬ" እና "እመቤቴ" የሚለው አነጋገር ከሁለቱም ተለይቶ አያውቅም፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ሲታይ አንዱ ያለ ሌላው መኖር የሚችሉ አይመስልም፡፡ በሚበላ፣ በሚጠጣ፣ በሚወደስ፣ በሚነገር ሁሉ አንዱ ሌላውን በማስቀደም ክብር ይሰጣጣሉ፡፡ ለሚያጋጥማቸው ጥሩ ነገር ሁሉ "አንቺ ትብሽ" "አንተ ትብስ" እየተባባሉ ፍቅራቸውን ሲለዋወጡ ማየቱ ለተመልካች አዲስ ፍቅረኛሞች እንጂ ከዓመታት በላይ አንድ ላይ የቆዩ አይመስሉም፡፡
ማጠቃለያ
ወ/ሮ ማርታ ገ/ፃዲቅ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በአሜሪካን ለከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የደረሱ በአገር ውስጥ ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር የፓስፖርትና ዜግነት የኃላፊነት ቦታ እስከ የሕዝብ መወሰኛ ም/ቤት አባልነት እንዲሁም በአሜካን አገር ከባለቤታቸው አቶ ደመቀ ተ/ወልድ ጋር ከአንድም ሁለት የኩባንያ ለዚያውም ለአሜሪካ መንግሥት ፔንታጐን የሬዲዮ መገናኛ መሣሪያዎችንና የአየር ፓራሹትን ሠርቶ በማቅረብ ዕውቅና ከማግኘታቸው ጐን ለጐን በኢንዲያና ስቴት የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከባለቤታቸው አቶ ደመቀ ጋር የመሠረቱት ኘሮጀክት ሜርሲ ከመነሻው ጀምሮ በዝቅተኛ ኑሮ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ላደረጉት ከፍተኛ የበጎ አድራጎት ሥራ በአሜሪካን አገር "የዓመቱ እናት" ከመባላቸው በላይ ከTaylor University ሁለቱም ወ/ሮ ማርታ ገ/ፃዲቅ እና አቶ ደመቀ ተ/ወልድ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ተሰጥተዋል፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ ኘሮጀክታቸው ድረስ በመሄድ ከጐበኙ ትላልቅ ሰዎች መካከል ከአሜሪካ የኮንግረስ አባል ሴናተር ሆፍማን እንዲሁም የአሜሪካን የFAO ተወካይ ቶኒ ሆል የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከአገራችን ደግሞ የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስቴሮች ባለቤቶች፣ የክልል መስተዳደር ኘሬዚደንቶች፣ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም ታዋቂው በኢትዮጵያ ጉዳይ የፖለቲካ ተንታኝና የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሽን ይገኙበታል፡፡
ለዚህ ሁሉ አበርክቷቸው እናት ባንክ በአዲስ አበባ በወሎ ሰፈር ያለው ቅርንጫፍ ወ/ሮ ማርታ ገ/ጻድቅ ቅርንጫፍ ብሎ በስማቸው ሰይሞላቸዋል። እናት ባንክን እጅግ እናመሰግናለን።
ወ/ሮ ማርታ ገ/ፃዲቅ ልጆችን በጣም አብዝተው የሚያቀርቡና የሚወዱ ከመሆናቸው የተነሳ ከሚሰጡት የበጎ አድራጎት ሥራ ውጭ በግል ሕይወታቸውም ከ50 በላይ ወጣቶችን አሜሪካ በሚገኘው ቤታቸው በማስጠጋት እያኖሩ ምግብና መኝታ አሟልተውና ለውጭ ትምህርት አብቅተው ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን አጠናቀው ዛሬ በአገር ውስጥና በአሜሪካ በሥራ ዓለም ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
በባለቤታቸው አፍ እመቤቴ፣ በልጆቻቸውና በቅርብ ዘመዶቻቸው እቴሜቴ በብዙዎች ደግሞ እማማ፣ እማማዬ የሚባሉት እኚህ ብርቱ ሴት ወ/ሮ ማርታ፣ እማማዬ ለ91 ዓመትዎ በሰላም አደረስዎ! ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ያለፈ የተረፈና ያማረ አሻራቸው እነሆ የብዙዎቻችን ሆኖ ዛሬም ለመዘከር በቅቷል።
እንኳን ለ91ኛው የልደት በዓልዎ በሰላም አደረስዎ!
እንኳን ተወለዱልን!
እጅግ እንወዶታለን፣ ስላበረከቱልን ሁሉ፣ ስለ መልካም ተጽዕኖ ከልብ እናመሰግናለን።
ፈጣሪ ዘመንዎችን እንደባረከ ሁሉ አሁንም እርሶንና ባለቤትዎን መላ ቤተሰቦን ለበረከት ያድርግልን። ክብረት ይስጥልን!