Oromo Liberation Front/ABO

Oromo Liberation Front/ABO

DW

ኦነግ በምርጫ 2013 ይሳተፋል ?

ትላንት በተጠናቀቀው የመጀመሪያው ዙር የእጩዎች ምዝገባ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አንድም እጩ አላስመዘገበም።

የኦነግ ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ ፥ ኦነግ ምንም የእጩ ምዝገባ አለማድረጉ ኦነግ በምርጫው ላለመሳተፉ ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።

አቶ በቴ ፥ "...በእኛ በኩል በተደጋጋሚ ስንገልፅ እንደነበረው ቢሮዎቻችን ዋና ፅ/ቤቶቻችን ጨምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆኑ፣ ነፃ እንቅስቃሴ እንደድርጅት መታገዱ፣ አመራር እና አባሎቻችን ያለህግ አግባብ መታሰራቸው ምርጫ ላይ በምናደርገው ተሳትፎ ላይ ትልቅ ተፅእኖ አላቸውና እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ መሳተፍ እንደማንችል ስንገልፅ ነበር፤ በዚህ ሁኔታ እጩ ማስመዝገብ አልቻልንም ስለዚህ በምርጫ ሂደቱ ተሳታፊ አይደለንም" ብለዋል።

ኦነግ ከምርጫው ተገፍቷል ያሉት አቶ በቴ በኣመራሮቹ ላይ አፈና በማድረግ እና ነፃ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አውድ አለመፈጠሩን ገልፀዋል።

ፓርቲው በምርጫ አለመሳተፉን ውሳኔ በተመለከተ አስፈላጊ ሆኖ ከየገኘ ለምርጫ ቦርድ እንደሚያሳውቅ አቶ በቴ ተናግረዋል።

ነገር ግን ከዚህ ቀደም ለምርጫ ቦርድ ይደርስብናል ያልናቸውን ችግሮች በተለያዩ መድረኮች ላይ ፣በደብዳቤም በተለያየ መንገድ ስናሳውቃቸው ነበር ምላሽ አልሰጡንም ሲሉ ወቅሰዋል።

በኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እስከ ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባኤ ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ ከዚህ ቀደም የተነገረላቸው አቶ ቀጄላ መርዳሳ (የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ) በበኩላቸው ፓርቲውን በምርጫው ለማሳተፍ ሲያደርጉት የነበረው ጥረት መጨናገፉን ገልፀዋል።

አቶ ቀጄላ፥ "...ኦነግ ባለፉት 7 እና 8 ወራት ችግር ውስጥ ነበር። የአመራር ቀውስ ነው ያለው። ወጥ የሆነ ውሳኔ ሰጪ አካል ጠፍቶ በድርጅቱ ውስጥ ያሉት ህጋዊ አካላት ውሳኔ መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ እጩ ማቅረብ አስቸጋሪ ነው ፤ በተቻለ መጠን ይህ ችግር ተፈቶ ወደ ምርጫ ለመግባት ጥረት ስናደርግ ነበር ፤ ተጓቶ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል" ብለዋል።

ይሁን እና ፓርቲው በጠቅላላ ጉባኤ የውስጥ ችግሮቹን ፈቶ በወጥ አመራር በምርጫው ለመሳተፍ እጬዎችን ለማስመዝገብ በተለየ ሁኔታ ጊዜ እንዲራዘምለት ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑ አቶ ቀጄላ መርዳሳ አሳውቀዋል።

ምንጭ፦ ጋዜጠኛ ስዩም ጌቱ - ጀርመን ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ

Report Page