Oromia - Wallagga

Oromia - Wallagga

ቢቢሲ፣ ዶቼ ቨለ ፣ ቲህቫህ ኢትዮጵያ

የምሥራቅ ወለጋ ጥቃቶች እና የነዋሪዎች ቃል

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ሰሞኑን በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከነሐሴ ወር መጀመሪያዎች አንስቶ በክልሉ መንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች እንደነበሩ የሚገልፁት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ግጭቶቹ እየቀጠሉ ሲሔዱ ሲቪሎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች መከተላቸውን ተናግረዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም የፋኖ ታጣቂዎች ፈፀሙት በተባለ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች ታፍነው መወሰዳቸውን ተከትሎ የክልሉ ኃይሎች ወሰዱት ባሉት "አፀፋዊ እርምጃ" ብዙዎች መገደላቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ አብራርተዋል።

በሰሞኑ ጥቃቶች በርካታ ንብረት ሲወድም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉም አያሌ ናቸው።

አሁንም ጥቃቶች መቀጠላቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።


" አምቡላንሱ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ተገድለዋል " - እማኝ

የጊዳ አያና ወረዳ ነዋሪ ፦

" ነሐሴ 13 በፋኖ የተፈፀመውን ጥቃት በቦታው ተገኝቼ ተመልክቻለሁ።

ከዚያ ጥቃት በፊት ባሉት ቀናት የፋኖ ታጣቂዎች ከሚሊሻዎች ጋር በተለያዩ ቦታዎች ተኩስ ሲለዋወጡ ነበር።

ሚሊሻዎች መቋቋም ሲያቅታቸው 'ገዳ ኮማንዶ' በመባል የሚታወቀው በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተቋቋመ ልዩ ኮማንዶ ገብቶ ከፋኖ ጋር ፊትለፊት ሲዋጋ ነበር።

በአካባቢው ባለው ስጋት ምክንያት የሕዝብ መገልገያ ተሽከርካሪዎች ተሰባስበው በመከላከያ ሠራዊት እየታጀቡ ነው የሚንቀሳቀሱት።

ረቡዕ ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም የሕዝብ ማመላለሻ፣ የጭነት እና ተሽከርካሪዎች በመከላከያ እጀባ ከጊዳ አያና ወደ ነቀምቴ ሲጓዙ በነበሩበት ወቅት፣ ቱሉ ሌንጫ በምትባል ቀበሌ ውስጥ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ ላይ ደፈጣ አድርገው ሲጠብቁ ይየነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች በተሽከርካሪዎቹ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

በወቅቱ በእጀባ ሲጓዙ የነበሩት ተሽከርካሪዎች በቁጥር እስከ 30 ይደርሳሉ። ከመካከላቸው ታማሚ የጫነ አምቡላንስ እና የሦስት ባንኮችን ገንዘብ ከእነ ኃላፊዎቹ የጫነ ተሽከርካሪ ይገኝበት ነበር።

በጥቃቱ አምቡላንሱ ውስጥ የነበሩ በዕድሜ ጠና ያሉ ታማሚ እና አብራቸው የነበረች የሕክምና ባለሙያ እንዲሁም የሦስቱ ባንኮች ኃላፊዎች ተገድለዋል።

የባንኮቹ ገንዘብ በታጣቂዎቹ ተዘርፏል። አምቡላንሱም ተቃጥሏል። ሌሎች ሲቪሎችም ተገድለዋል። "


" በድንገት ነው መገደሉን የሰማነው " - የሟች ወንድም

የሟች ወንድም ፦

" ወንድማችን የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የጊዳ አያና ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ነበር።

በመከላከያ ሠራዊት እጀባ የባንኩን ገንዘብ ይዞ ወደ ነቀምቴ እየሔደ ነበር።

በመንገድ ላይ እንዳለ በተፈፀመበት ጥቃት መገደሉን በድንገት ሰማን።

የባንክ የቅርንጫፍ ኃላፊ የሆነው ወንድሜ ማሙሽ ማሩ ይባላል። የአራት ልጆች አባት ነበር።

"


በተጨማሪ ፦

- አቶ ካፋሎ ነጋሳ ደያስ የተባሉ የቀርሳ ሀርቡካኔ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደር በዚሁ ጥቃት መገደላቸውን የቤተሰብ አባላት ገልጸዋል።

- ጫላ ናጋሳ የተባለ ባለፈው ዓመት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት ልጅም የጥቃቱ ሰለባ ሆኗል።


" 13 ቤት ለቅሶ ደርሻለሁ " - የአካባቢው ነዋሪ

ነዋሪ ፦

" በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉቴ ከተማ ብቻ 13 ቤት ለቅሶ ደርሻለሁ።

ከተገደሉት በተጨማሪ ብዙ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል።

በተኩስ መሃል ተይዘው የነበሩ ተሳፋሪዎች፣ ራሳቸውን ለማዳን እግራቸው ወደመራቸው አቅጣጫ ሲሯሯጡ የፋኖ ታጣቂዎች ወዳሉበት አቅጣጫ የሄዱት ታፍነው ተወስደዋል።

ቁጥራቸው እስከ 70 ሊደርስ ይችላል።

ታፍነው ከተወሰዱት ውስጥ ሦስቱ ዘመዶቼ ናቸው። ታጋቾቹን ለመልቀቅ ታጣቂዎቹ ገንዘብ እየጠየቁ ነው።

ከታገቱት መካከል አንዷ ትዳር ከመሠረተች ገና አንድ ሳምንቷ ነው።

በጅማ መምህርት የሆነች የ3 ልጆች እናትም ወደ ቤተሰቧ በመመለስ ላይ እንዳለች ታፍና ተወስዳለች።

ከታገቱት መካከል አምልጠው የተመለሱ አሉ ግን አብዛኞቹ የት እንደደረሱ አይታወቅም።

እኔን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተፈናቅለን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነን።ሆኗል።


ከአንገር ጉቴ መላው ቤተሰባቸውን ይዘው የተፈናቀሉ ተፈናቃይ (ለዶቼ ቨለ)፦

" አሁንም ድረስ ባለው የጸጥታ ችግር መንገድ እንደ ተዘጋ ነው። ባለፈው እሁድ ከአንገር ጉቴ ወደ ነቀምቴ በቆሎ ጭኖ ሲጓዝ የነበረን ነጋዴ ታጣቂዎች መንደር 11 ላይ እሱን ገድለው ሹፌሩን አግተው ሄደው ዕጣ ፋንታው አልታወቀም።

ወደ ግዳያ ወይም ዲቾ አቅጣጫ ከፍተኛ ስጋት ስላለ ማንም ሰው አይጓዝም ተቋርጧል።

እኔን ጨምሮ በርካታ ህዝብ ወደ ቄየው ሊመለስ ቀርቶ በርካታ ህዝብ እየተፈናቀለ ነው። "


ይህን ጥቃት ተከትሎ ሁኔታዎች ተባብሰው " አፀፋዊ እርምጃ" በስፋት መፈፀሙን ነዋሪዎች ገልፀዋል።


በጊዳ አያና ወረዳ የክልሉ መንግሥት ኃይሎች እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ከነሐሴ 2/2018 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ከተጎጂዎች መካከል የሆኑ አራት የወረዳው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ይገልፃሉ።

ከነሐሴ 12 ወዲህ ደግሞ " ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ተጀመረ " ብለዋል።

ፋኖ ነሐሴ 13 ከፈፀመው ጥቃት በኋላ ደግሞ ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ "አፀፋዊ" እርምጃ በብዛት መቀጠሉን አመልክተዋል።


" ካኅናት፣ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞች ተገድለዋል " - ነዋሪ

የመንደር 22 ነዋሪ፦

" ግጭቶች ከተጀመሩ አንድ ወር አካባቢ ይሆናል። ንፁሃንን ዒላማ ማደረግ የተጀመረው ግን ከ5 ቀን ወዲህ ነው ከነሐሴ 12 ወዲህ ነው።

የተገደሉትን በቁጥር ለመግለፅ ይከብዳል። በርካታ ናቸው። ካኅናት፣ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞች ተገድለዋል።

ከተገደሉት መካከል የቅርብ ዘመዶቼ የሆኑ ካህን ይገኙበታል።

ካህኑ ዘመዴ ቆሞስ አቡሀይ ታደሰ መኮንን ይባላሉ። የኦሮሚያ ክልል መለዮ የለበሱ ታጣቂዎች ልብሳቸውን አስወልቀው ሲያንገላቷቸው የሚያሳየው በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረው ቪዲዮ የእርሳቸው ነው።

ቆሞስ አቡሀይ ታደሰ፣ በጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ የምትገኘው ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ ነበሩ። ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም. ዓርብ ነው የተገደሉት።

ከቤተክርስቲያን በአገልግሎት ላይ ከነበሩበት ነው ይዘው የወሰዷቸው። ከዚያን ጫካ ወስደው አሰቃይተው ነው የገደሏቸው።

በቀበሌው በምትገኝ 'ፈንደቃ' የምትባል መንደር ቤቶች መቃጠል ሲጀምሩ ሰው በፍራቻ ሸሽቶ ነበር። እሳቸው ግን የሃይማኖት አባት እንደመሆናቸው 'ምንም አያደርጉኝም' ብለው በማሰብ ቤተክርስቲያኑንም ትተው ላለመሔድ ነው የቀሩት።

ዓርብ ተገድለው በአምስተኛው ቀን ማክሰኞ ዕለት ነው የተቀበሩ። የፀጥታ ኃይሎች ቦታውን ለቀው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ አስከሬናቸው ከጫካ ውስጥ ተፈልጎ ነው የተቀበረው። ሌሎች ሟቾችም በተመሳሳይ ቀን ተቀብረዋል።

ሌላ የካህኑ የቅርብ ዘመድ የሆኑ ቄስ አዲስ የሚባሉ የሃይማኖት አባትም አገልግሎት ለመስጠት ወደ ቤተክርስቲያን በሚሄዱበት ሰዓት ተይዘው ተገድለዋል።

በቤተክርስቲያኒቱ ደጅ በልመና ይተዳደሩ የነበሩ እናት ደግሞ ከሕጻን ልጃቸው ጋር እንዳሉ ተገድለዋል። ከአራት ቀናት በላይ አስከሬናቸው ሳይነሳ ቆይቷል።

እናት በልጇ ፊት መገደላቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶግራፎች የነሱ ናቸው። እናቲቱ ነፍሰጡር ነበረች። አብራቸው የነበረችው ሕጻን ሁለተኛ ልጃቸው ናት። በሕይወት ተርፋ ዘመድ ወስዷታል።

በአካባቢው ጥቃቱን እየፈፀሙ ያሉት ገዳ ኮማንዶ፣ በቅርቡ ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የፈፀመ በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቡድን ታጣቂዎች እና የሚሊሻ አባላት ናቸው። በሂደቱ የሚሳተፉ ሌሎች አካላትም አሉ።

በጣም ከባድ ሁኔታ እያሳለፍን ነው። የብዙ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች በእሳት ወድመዋል። አንስሳት እና ሌሎች ንብረቶችም ተዘርፈዋል።

በአሁኑ ወቅት በየአቅጣጫው ከአካባቢው ሸሽተን በጫካ፣ ሰዎች ጋር ተጠግተን እና በቤተክርስቲያናት ተጠልለን ነው ያለነው።

ጥቃት የተፈፀመባቸው መንደሮች በርካታ ናቸው።

በዋናነት በአንዶዴ ዲቾ እና በቱሉ ሌንጫ ቀበሌዎች የሚገኙ ብዙ መንደሮች በአብዛኛው ወድመዋል። ዋና ከተማዋን አንገር ጉቴ (ጉትንን) ጨምሮ በከተሞች ያሉ መጋዘኖች እና የንግድ ቤቶች ዘረፋ እና ቃጠሎ ተፈጽሞባቸዋል። "


" የደረሰልን የጠየቀን የለም " - የአንገር ጉቴ ነዋሪ

ነዋሪ፦

" የእህል ክምችት ያለበት መጋዘኔ ተቃጥሎብኛል።

አሁንም ጥቃቱ እንደቀጠለ ነው።

የደረሰልንም የጠየቀንም አካል የለም። "


ሌላ ነዋሪ " መሔጃም የለንም፤ እርዳታም የለም፤ ሁላችንም ተፈናቃዮች በችግር ላይ ነን " ሲሉ ተናግረዋል።


" በርካታ ሲቪሎች ተገድለዋል ፥ በርካታ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል " - የቱሉ ሌንጫ ቀበሌ ነዋሪ

ነዋሪ፦

"  በገዳ ኮማንዶ የተመራ ኃይል በቀበሌው በሚገኙ መንደሮች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመረው ከነሐሴ 16 ጀምሮ ነው።

መንደር 3፣ መንደር 22 እና በጭበጭ በሚባሉ መንደሮች ውስጥ ሰኞ ነሐሴ 18 እና በቀጣዩ ቀን በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ሲቪሎች ተገድለዋል። በርካታ መኖሪያ ቤቶችም ተቃጥለዋል። ዘረፋም ተፈጽሟል።

ከተገደሉት መካከል በሚካኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው የነበሩ በትንሹ 20 ሰዎች ይገኙበታል።

በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ ጋብ ሲል በ3ኛው ቀን ተደብቀው የሔዱ ሰዎች 20 አስከሬን ቀብረው ተመልሰዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመበት ግንድአንሳ ሚካኤል ቤተክርስቲያንም ተቃጥሏል።

ከተገደሉት ሲቪሎች መካከል ዘመዶቼ ይገኛሉ። አካባቢያቸውን ጥለው ማምለጥ ያልቻሉ አቅመ-ደካማ ሲቪሎች ዋነኛ ሰለባዎች ናቸው። "


" መአት ነው የወረደብን ... ፋኖዎቹ ቀድመው ወጥተው ነበር " - የመንደር 3 ነዋሪ

ነዋሪ፦

" መአት ነው የወረደብን።

ዋናው ጥቃት ከመፈፀሙ ከሁለት ቀን ፊት በ16 ቅዳሜ የመንግሥት ኃይሎች መጥተው መተኮስ ጀመሩ፤ የፋኖ ታጣቂዎች ቀድመው መንደሮቹን ጥለው ሄደዋል።

በወቅቱ 10 ሽማግሌዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የመከላከያ ካምፕ ሔደን እንዲታደጉን አመልክተን ነበር። ከዚያ ስንመለስ ሚሊሻዎች አሰሩን። ከስድስት ሰዓት የእስር ቆይታ በኋላ የመከላከያ ኮሎኔል መጥቶ ሁኔታውን አስረድተነው ተለቀቅን።

'ፋኖን ትደግፋላችሁ፤ እዚህ ነው ሚደበቁት እናንተ ናችሁ ምትመግቧቸው' በሚል ነው ጥቃት የተፈፀመው።

በአካባቢው የፋኖ እንቅስቃሴ አለ። ነገር ግን የመንግሥት ኃይሎች ጥቃት ከመፈፀማቸው በፊት ከስፍራው ለቀው ወጥተው ነበር።

ቦታው የበረሃ ፋኖዎች የሚንቀሳቀሱበት መስመር ነው፤ ይህ ሃቅ ነው! በፊትም ከሩቅ እየመጡ እነዚህን መንደሮች ማረፊያ ያደርጋሉ።

' ሕዝቡ ሂዱልን፤ እኛን እንዳታስገድሉን 'ብሎ ሲማጸናቸው ነበር።

የታጠቁ ናቸው፤ የታጠቀን ኃይል ማን ያግደዋል ? ማን ይከለክለዋል ? የፈለጉትን ነው የሚያደርጉት።

በአሁኑ ወቅት ጥቃቱ የተፈፀመባቸው መንደሮች ሰው አልባ ሆነዋል። "


ይህ የሚከተለው የነዋሪዎች ቃል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የተሰጠ ነው

" 'መሳፈር አትችሉም' ተብለን አሁንም መውጫ የለንም፤ የትም መሄድ አንችልም " - ነዋሪ

ነዋሪ ፦

" በአንገር ጉትንና አካባቢው ከሰሞኑ በተፈጸመው ጥቃት ፀበል ቦታ የነበሩ በርካቶች ጭምር ተገድለዋል። የሟቾቹ ቁጥር በእርግጠኝነት ከ67 በላይ ይሆናሉ። 67 በተጨባጭ ተቆጥሯል።

በመንደር 3፣ 22 እና 14፣ ጉትን ከተማ፣ በ'ቱሉ ጋና' አካባቢዎች ጥቃት ተፈጽሟል።

በተጨባጭ ሀብት ንብረት ሳይቀር ቤትም ተቃጥሏል። የመንግስት የጸጥታ ኃይል በአካባቢው አለ፤ ስንጠይቃቸው ግን 'አያገባንም' ነው ያሉት።

መንደር 3 ላይ 14 ዓመት በሊቀመንበርነት ሲያገለግል የኖረና አቅሙ ሲደክም በቤክርስቲያን ጥበቃ ተመድቦ የነበረን ሰው በስለት አጥቅተው ገድለውታል። 'ባለቤቴን ገደሉት' ብላ የሟች ባለቤትም ወደ ጓሮ ስትሄድ ታጣቂዎቹ በስለት ገደሏት።

ፀበልተኞች ለፀበል በሄዱበት 'የት አባታችሁ ትገባላችሁ፣ መውጫ የላችሁም' እየተባሉ በስለት ተገድለው ነው የቀሩት። ይህ የሆነው 'ግንድ አንሳው' ሚካኤል መንደር ሦስት ነው።

አንዲት እናት ተገድላ አብራት የነበረች ህፃን ልጇ ከጎኗ ተኝታ መገኘቷን የሚያሳይ ምስል ትክክል ነው።

ከሞት የተረፉት ከጥቃት ለማምረጥ ሲሞክሩ ክልከላ እየተደረገ ነው።

'መሳፈር አትችሉም' ተብለን አሁንም መውጫ የለንም፤ የትም መሄድ አንችልም፤ የተረፍነውም ቁጭ ብለናል። የታጣቂዎቹን ማንነት ማወቅ አይቻልም፤ ፊታቸውን ተሸፋፍነዋል፤ ሌሊት ነው የሚገቡት፤ 'ሸኔ' ናቸው ነው የምንለው። "


ሌላ ነዋሪ፦

" የእህቴ ባል ወንድም አደባባይ በጥይት ገደሉት፤ ባለፈው ወር የሞቱት በሙሉ ያለምንም ጥፋት ነበረ የተገደሉት ግን ምን ዋጋ አለው። "


" በርካታ ከብት በታጣቂዎች ተዘርፏል " - ነዋሪ

ነዋሪ ፦

" መጀመሪያ አርሶአደሩ ከ'ሸኔ' ጋር ውጊያ ላይ እንደነበር፣ በኋላ 'የገዳ ኮማንዶ' በአካባቢው ገባ። ከዚያ በኋላ እንደ ቱሉ ሌንጫ ቀበሌ በአንድ ቀን ብቻ ከ40 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

እነዚህ በይፋ የማውቃቸው ብቻ ናቸው ፣ በአጠቃላይ እስከ አንዶዴ ዲቾ ያለውን ሳይሆን እዚሁ ቀበሌ ያለው ነው፤ በአጠቃላይ በጣም ብዙ ነው። እኔ በዓይኔ ያየሁትን ነው የምናገረው።

43 ሟቾች እኛው ጋር የነበሩ ናቸው። በሌላ ቀበሌም የተገደለ አለ፤ ቤተክርስቲያን ተቃጥሏል፤ የተገደሉት በስለት ጭምር ነው፤ ለመሮጥ የሞከረ ብቻ ነው በጥይት የተመታው።

በፈንዲቃ፣ ለሊ ተክለሃይማኖትና ማርያም፣ ዋጃ፣ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ቁጥራቸው በትክክል ባይታወቅም፣ በብዛት ሰዎች የተጎዱበት ነው።

ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት ነው። ከ200 በላይ የጋማ ከብት፣ በርካታ የቀንድ ከብቶች በታጣቂዎች ተወስደዋል። ማህበረሰቡ ከባድ ጥቃት ነው የደረሰበት። "


ከወለጋ ከዚህ ቀደም በነበረ ጥቃት ተፈናቅለው ደቡብ ወሎ ዞን ተጠልለው የሚገኙ ጉዳዩን ጥቃት በደረሰበት አካባቢ ካሉ ቤተሰቦቻቸው ያጣሩ ተፈናቃይ፦

" ሐምሌ 24/2018 ዓ/ም ምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን አካባቢ 17 ሰዎች በማንነታቸው ሳቢያ ተገድለዋል።

የተረፉት፣ ወደ ሌላ ቦታ ወጥተው ሕይወታቸውን ማቆየት አይችሉም፤ 'ይሙቱ' ተብለው እየተሰቃዩ አሉ፤ በጃርደጋ ጃርቴ፣ አጋምሳ፣ አቤደንጎሮ፣ አሙሩ፣ ሀሮ ያሉት በችግር ላይ ነው ያሉት። "


" የሞቱት ሞተዋል ለተረፍነው እንኳ መፍትሄ ይስጠን " - የአንገር ጉትን ነዋሪ

ነዋሪ ፦

" መፍትሄ ባለመገኘቱ ተፈናቃዮች በዱር ናቸው። ታጣቂዎቹ ካለንበት ቦታ ከገቡ መሸሻ የለንም፤ እዚሁ መገደል ነው። የአማራ ክልል መንግስት ትኩረት ያድርግልን፤ የሞቱት ሞተዋል ለተረፍነው እንኳ መፍትሄ ይስጠን።

ተቸግረን ነው ያለነው በቡሬ መስመር ከጉትን ወደ አጋምሳ በኩል ወደ ዓባይ በርሃ ያለው መንገድ ከ2013 ዓ/ም ተዘግቶ ነው እስካሁን ህብረተሰቡ ተቆልፎ ለአደጋ ከመጋለጥ የደረሰው። በነቀምት በኩል ያለው መንገድም ዝግ ነው፤ በየት እንውጣ? ምንም መውጫ የለም ጫካ ነው። "


የመንግሥት አካላት ምላሽ

" በፋኖ ፅንፈኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል " - ዞን ፖሊስ

የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የፋኖ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን የምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ አስታውቋል።

የዞኑ ፖሊስ፣ የፋኖ ጥቃት ከመፈፀሙ አንድ ቀን ቀደም ብሎ " ሕዝቡ በሁለት ታጣቂዎች በሸኔ (የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት) እና በፋኖ ፅንፈኞች በሚፈፀሙበት ጥቃቶች ለተለያዩ ጉዳቶች ተጋልጧል " ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል።

የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች "በፋኖ ፅንፈኞች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን" የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ቦጃ ባልቻ መግለጻቸውም በዚሁ የፌስቡክ ልጥፍ ተጠቅሷል።

እንዲሁም ለዶቼቨሌ በሰጡት ቃል ረዳት ኮሚሽነር ቦጃ ባልቻ፣ " ብዙዎች እንደሚነዙት አሉባልታ ሰላማዊ ህዝብን እንዲህና እንዲያ አድርገዋል እንደሚሉት ሳሆን ትኩረት አድርገን እርምጃ እወሰድን ያለው ህዝቡን በሚያፈናቅል የታጠቀ አካል ላይ ነው " ብለዋል።


የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በሚል ስያሜ የተደራጀው የፋኖ ቡድን በወለጋ የሚንቀሳቀስ የፋኖ አደረጃጀት መመሥረቱን በቅርቡ ገልጿል። የወለጋ ፋኖ ነሐሴ 13 በጊዳ አያና ጥቃት መፈፀሙንም በማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች የገለፁት የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች፣ ዒላማቸው የመንግሥት አካላት እንደሆኑ ነው የተናገሩት። በዕለቱ የተለያዩ መሳሪዎች መማረካቸውን ፤ በርካታ መኪናዎችን መደምሰሳቸውን አሳውቀዋል። 3 ኩንታል ብርም መውሰዳቸውን ገልጿል።


ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ሰሞኑን በወለጋ ደረሰ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ እንደ ቢሮ ምን ምላሽ እንዳላቸው የጠየቃቸው የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ፣ ምላሽ በመስጠት ፋንታ ከኃላፊ የማይጠበቅ የስድብ ኃይለ ቃል ተናግረው አቋርጠው ስልክ ዘግተዋል። 


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና የተፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ክትትል እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል። ይሁን እንጂ በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሳ እስካሁን የተሟላ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቋል።


የነዋሪዎች ስጋት ፦ ግጭት የአብሮ መኖርንና የአርሶ አደሩን ሕይወት እየፈተነ ነው

በጊዳ አያና አካባቢ በቀጠለው ግጭት ምክንያት፣ በአንድነት እየኖሩ የነበሩ ማኅበረሰቦች መካከል መተማመን እየቀነሰ መምጣቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ ግጭቱና በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍርሃትን እያባባሱ ነው። በተለይም ከፖለቲካ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው አርሶ አደሮች በግጭቱ መካከል እየተጎዱ መሆኑን ይናገራሉ።

አንድ ነዋሪ፣ ቀደም ሲል ተዋደው ተጋብተው አብረው ይኖሩ የነበሩ ማኅበረሰቦች አብሮ የመኖር ሁኔታ በፖለቲካ ምክንያት እየተሸረሸረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ የታጠቁ ኃይሎች ግጭት በቀጠለ ቁጥር የሲቪሎች ሕይወት ይበልጥ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፣ ወደ መንደሮቻቸው ተመልሰው ለመኖር የደኅንነት ዋስትና እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ብዙዎቹ ተጎጂዎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ድፍረት እንደሌላቸው ገልጸው፣ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።

ከተፈናቃዮቹ መካከል የሆኑ ግለሰቦች፣ በጫካ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት እንደሌላቸው እና ሰብዓዊ ድጋፍ እየደረሳቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች በዚህ የክረምት ወቅት ወደ እርሻቸው ተመልሰው ለመሥራት የደኅንነት ዋስትና እንደሌላቸው ይናገራሉ። በመሆኑም እርሻቸውን ተንከባክበው ዘር መሰብሰብ ካልቻሉ፣ ከፊት ለፊታቸው ሌላ ከባድ ችግር ሊጠብቃቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ቢመለሱም፣ በግጭቱ ምክንያት ቤቶቻቸውንና ንብረቶቻቸውን ያጡ በርካታ ሰዎች ማረፊያ እንደማይኖራቸው ይገልጻሉ።

በአጠቃላይ፣ የነዋሪዎቹ ስጋት የሚያመለክተው ግጭቱ በሲቪሎች ሕይወት፣ በአብሮ መኖር፣ እና በአርሶ አደሩ የእርሻ ሥራ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ከፍተኛ መሆኑን ነው።


መረጃው የተዘጋጀው ፦

° ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ

° ቲክቫህ ኢትዮጵያ በስልክ ያናገራቸው ነዋሪዎች

° ከዶቼ በለ ሬድዮ

ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ/ም

Report Page