#OLF

#OLF


የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ-መንበር የሆኑት የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት በፌዴሬል ፖሊስ መከበቡን የፓርቲው ቢሮ ኃላፊ አቶ ገዳ ኦልጅራ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አቶ ገዳ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት አካባቢ የሚገኘው የጸጥታ ኃይል የሊቀመንበሩን ደኅንነት ለመጠበቅ መሰማራቱን ከፖሊስ መስማታቸውንም ተናግረዋል።

የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት መከበብን ለቢቢሲ ያረጋገጡት አቶ ገዳ የታጠቁ ኃይሎች በመኖሪያ ቤቱ ዙሪያ እንደሚገኙ አሳውቀዋል።

ኃላፊው፤ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመኖሪያ ቤታቸው መውጣትና መግባት እንዳልቻሉና ወደ ውጪ የሚወጡ ከሆነም በጸጥታ ኃይሎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ስጋተቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የግንባሩ ለቀ መንበር አቶ ዳውድ ከሦስት ቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ከአንድ ቀን በኋላ መፈታታቸውን አቶ ገዳ ገልጸዋል።

"ዋና ሊቀመንበራችን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት። እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው የዕለተ ዕለት ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም" ሲሉ አቶ ዳውድ ከቤታቸው መውጣት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

አቶ ገዳ እንደሚሉት አቶ ዳውድ ብቻ ሳይሆኑ በቤታቸው ውስጥ ያሉ የቤተሰባቸው አባላትም ከመኖሪያ ግቢው መውጣትናም ሆነ ከውጪ መግባት ተከልክለዋል።

አቶ ገዳ ካሉት የእንቅስቃሴ ገደብ በተጨማሪ የአቶ ዳውድ ኢብሳ ስልክ ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ እየሠራ አይደለም።

የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት ለምን እንደተከበበ የሚያውቁት ነገር አለ ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ገዳ፤ ፖሊስ ይህን ያደረገው ለእሳቸው [አቶ ዳውድ] ደኅንነት ሲባል እንደሆነ ተነግሮኛል ይላሉ።

ይሁን እንጂ "ሰው እንዳይገባና እንዳይወጣ እየከለከሉ ደኅንነት ለመጠበቅ አይመስልም" ይላሉ። "የአቶ ዳውድ ስልክ ስለማይሰራ ከራሳቸው ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻልንም" ሲሉ ከሊቀመንበሩ ጋር መገናኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

ሁኔታውን በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ የተየቁ ሲሆን እሳቸው ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Report Page