My Pencil & My chronicle

My Pencil & My chronicle

ሳሚDire
ታህሳስ 5, 2012 ዓ.ም. ጠዋት 12:30 : ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል። የሰንሴት ሃይኪንግ (hiking) አስተባባሪዎች እና ተሳታፊዎች ለ ጉዞ እየተዘጋጁ

ክፍል ፩

ከተለያዩ የአ.አ ሰፈሮች/አካባቢዎች የመጣን ለዘመናዊ ሆቴል ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ከሆነው #ጣይቱ ሆቴል ፊት ለፊት ተሰባስበናል። ኧረ እንደውም እዛው ያደረ አይጠፋ... 

የጉዞው አዘጋጆች ከላይ ታች የማስተባበር ስራውን ተያይዘውታል። የማርፈድ ልምድ ያለብን አንዳንድ የአ.አ ነዋሪዎችንም ከነብርድ ልብሳችን ጭምር አስተባብረው ከመኪናው ከተቱን።

ከመኪናው ውስጥም እንደምንም የተጫጫነንን ስሜት አላቀን ጉሮሯችንን በእስክሪብቶ ጎርጉረን 'እንዴት አደራችሁ' እያልን ከባላጋራችን ሰላምታ መለዋወጥ ጀመርን። እንዲህ ባለው ስሜት አ.አ ለቀን ለመውጣት ከሹፌሩ ጋር ሞተሩንም ወሬውንም አሙቀን ተንቀሳቀስን። በመንገዳችንም አውቶቡሷ አንዳንድ የአ.አ አካባቢ ነዋሪዎችን እየለቀመች ነጎደች። አ.አ ለቀን አየወጣን ነው ወሬውን ቡና ሳናፈላ ሞቅ አርገነዋል። ይህን የተገነዘበው የፊት አጋፋሪው አቶ ዲጄ ሆዬ የበለጠ ዘና ለማድረግ ቅን ልቦና ተያይዞ መሰለኝ ሙዚቃውን ሊያንቆረቁሩት ተነሱ። ሙዚቃውንም ለቀቁት የመጀመሪያ ምርጫቸውም 'ሱሴ' የሚል ርዕሰ ዜማ ያለው ነበር። እኔን ጨምሮ ተጓዦች ያዛጉ ጀመር ትተነው የመጣነውን ቀሰቀሱብን ይመስላል። የዲጄው ነገር ይቆየንና ተጓዡ ግን ምን አስቦ ነው ሱሴ ሲባል የሚያዛጋው ቆይ ይሄም ይቆየን።

ጉዞውም ቀጥሏል አሌልቱን ቀጥሎ ሸኖን አለፍንና ጥንታዊቷ ደ.ብርሃን ደረስን መሰለኝ። አውቶቡሳችንም ለቁርስ ይሁን ለረፍት ይሁን የደ.ብርሃን እርጎ ለመሸመት ይሁን ቆማለች።

 ከደ.ብርሃን አልፈን የደብረሲናን መንገድ ተያያዝነው... ተያያዝነው ስል በአውቶቡስ ነው ታድያ ቅዝቃዜውም አየጨመረ መጣ። አንደርስ የለ ቦታው ደረስን መሰለኝ... ቆይ ይሄ ምኒሊክ የሚሉት ጉድ ምን አይነት መስኮት ሰርቶ ነው እዚህ ድረስ የጠራን እያልኩ ከራሴ ማውራት ጀመርኩ.... ኧረ ጉድ ይሄን የሚያህል ከፍታ ላይ ይሄን የሚያህል ክፍተት ነው ግን መስኮት ያሉት ለማለት ፈለግኩ። ትንሽ ቆይቼ ሳስበው ሳየው ሳልመው ግን እውነትም መስኮት: አሻግረው ሲመለከቱት የአዋሽ ተፋሰስ: የአፋር በርሃማ አካባቢዎች: የይፋት ቆላማ መንደሮችን በትኩሩት ላያቸው መስኮትነቱን ማረጋገጫ ሰጥቶ ያልፋል።

ድንባሮ: የምኒልክ መስኮት


ተራሮችንም መውጣት መውረዱን ቀጠልን በየመሃሉ እልፍ የሚሉ ሽኮኮ መሳይ ፍጥረቶችን እንዲሁም በሰሜን ተራሮችብቻ የሚገኘው ጭላዳ ዝንጀሮን የመመልከት እድሉን አግኝተናል። ኧረ እንዲሁም ዘመን አመጣሹን ድሮን የምትመስል ወፍ ዝርያም አይተናል: መብረር የለ ሰማይ ላይ መቆም ብቻ... ጉዞው እየተፋፋመ ሲመጣ እኔም መፃፌን አቆምኩ... ቀሪውን ሳርፍ እነግራችኋለው እስከዛው ግን በዚህች አጭር ግጥም ልሰናበታችሁ...

   ምኒሊክ ተጉዞ የምትጠይቀኝ

   ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ

ድንባሮ


ክፍል ፪

....... ቀሪውን ሳርፍ እነግራችኋለው ነበር ያልኩት:ይኸው እስካሁን እንዳላረፍኩ ብነግራችሁስ። እንደ ድሮ ስፖርት አስተማሪያችን ሲያረገኝ ደረቴን ወድሬ ሁለት እንስቶችን ይዤ እየመራው ትንሽ እንደተጓዝን ብቻ ካጠገቤ እያራቁኝ ይሁን እየራቅኳቸው በማላውቀው መንፈስ ከፊቴ ተሰወሩብኝ። ያቺ የወንድነት ስሜቴን አሰባስቤ ደግሞስ የምኒሊክ ሃገርም አይደል ብቻ ማላውቀው መንፈስ እየተፈራረቀብኝ እከተላቸው ጀመር። መንፈስ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ ምንም ትዝ አላለኝም ተውኩት። እንደምንም ብዬ አጠገባቸው ስደርስ ቅድም ያልኳችሁን የደ.ብርሃን እርጎ እንደ ፀበል ፀዲቅ እየተቀባበሉ ይሏታል አልኳችሁ። አቤት ፍቅራችው ደስ ሲል: በሞቴ እየተባባሉ ግማሿን ሊትር ምጥጥ አረጓት። 'ለካስ ብቻችሁን አይደላችሁም እንዲ ልቤን እስክተፋ የምሮጠው በዜሮ ዜሮ መስላችሁኝ' ለማለት ፈልጌ በድጋሚ ተውኩት። ግን ወንዱ ምን ሆኖ ነው ሃሞቱ ፍስስ ያለው ማለቴ ሃሞታችን ፍስስ ያለው ? የኛ ጊዜ ወንድ ቢሆን በአንድ እጁ ሃሳቡን በጀርባው ሚስቱን አዝሎ ነበር ይቺን ተራራ እየወጣ እየወረደ ሚፎክር... 

ብቻ ጉዟችን እንደቀጠለ ነው አንዳንዱ ደግሞ ልቡን ሊተፋት ሲደርስ 'እዚህ ጋር ኔቸሩ አያምርም ፎቶ ላንሳችሁ' በሚል ሰበብ ረፍት ይወስዳል። መቼስ ሴቶቻችን ፎቶ ከተባለ ዜብራ ላይም ቆመው ሳይነሱ አይቀርም። አንዳንዱ ደግሞ 'ጎበዝ በዚህ ጋር ያስኬዳል እንዴ' በሚል ሰበብ ነፍሱን ይመልሳል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወጣን ወረድን ወጣን ወረድን ለዛሬ ይኽን ተራራ ነክቶ መመለስ ነው መሰለኝ ሃሳቡ ነክተን እየተመለስን ነው።

 አቤት መውረድ ግን ሲያስጠላ ማለትም ተራራ መውረድ: አስፋልት ለማየት ያለን ጉጉት እናቱ እንደጠፋችበት ልጅ ያለ ነው። ኡፍፍፍፍፍ አገኘነው አስፋልቱን: እንደው ላገሬ መሬት ያበቃኸኝ ብዬ አስፋልቱን ብስመው ደስ ይለኝ ነበር። ቆይ አንዴ ተንበርክኬ ልሳመውና ቀሪውን እነግራችኋለው..... ይቆየን

ክፍል ፫

ሁላችንም አውቶቡሱን ከበን ተቀምጠናል ግማሹ ስለጉዞው ያወጋል ገሚሱ የወጣውን ተራራ በተመስጦ እያየ ይቆዝማል። ድካሙ የበረታበትም አውቶቡሷን እንደ ቤርጎ ተጠቅሞ ወገቡን ያሳረፈም አለ። ከዚህ በኋላ እንኳን ተመልሰን እኚህን ተራሮች ስለማንወጣቸው ፈገግታዬ ጨምሯል። ሰላም ሲሉኝ ራሱ ተነስቼ ለማቀፍም ይዳዳኛል። ልክ ዘመቻ ሄዶ ከሞት አምልጦ እንደመጣ ወታደር ደስታዬ ወደር አልነበረውም።

ራሃባችንንም ለጊዜው ለማስታገስ አካባቢው ያፈራውን ሸንኮራ አገዳና ቆሎ መቀማመስም ተያያዝነው። በጣም የሚጣፍጥ ምግብ ማለት ርቦህ ምትበላው ምግብ ነው ይል ነበር አንድ ወዳጄ። ህዝቡ ግን ቸር ነው ኤልሳ ቆሎ ተሰልፈን ግማሹን ከ70-80 ብር አውጥተን የምንገዛውን እዚህ በ25 ብር ብቻ በውሃ ጆግ ሙሉ ያሸክሙሃል። ሂሳብም ሲቀበሉ እንኳን እንደማፈርም ያረጋቸዋል በቦታው ያሉትን ጌጣጌጦችም እንደፍላጎቶቻችን ገዝተን ወደ አውቶቡሱ ለመግባት ተነሳን። ግና ለመመለስ ስንሰናዳ አንዳች ነገር ተሰማኝ ቅርም አለኝ ሰው እንዴት ጨክኖ ይህን የመሰለ መልከዓምድር ትቶ ወደ ሁካታው አለም ይመለሳል። ብቻ ተዉት 'ወዳጅ ያዝናል እንጂ አብሮ አይሞትም' ይባላልና።

ጉዞ ወደ ደ.ብርሃን መልስ ጀመረናል ሹፌሩ እንዴት ያለ ጎበዝ ቢጤ ነው። አውቶቡሷን የሚሾፍራት ሳይሆን የሚያባራት ነው ሚመስል እንደውም ቄራ አካባቢ ሞተረኛ ሆኖ ማቀውም መሰለኝ። ለዚህም ይመስላል ከተሳፋሪ አንዷ እንስት ወራጅ አለ ብላ ወርዳ የተመለሰችው።

 ደ.ብርሃን ደረስን ከከተሜ ጋር ተቀላቀልን ለምሳም ተሰናዳን። አ.አ ጥሩ የሚባል ቦታ ተመግበናል ግና እንዲህ ያለ ንፁህ ምግብ እውነቱን ለመናገር እናታችን ጋር የበላን ነን። ለዚህ ምስክራችን አበላላችን መመገቢያ ሳሕኑን ካላጠብን ብለን ሙግትም ገጥመን ነበር። አ.አ እንደለመደብን ሁለት ሊትር ውሃ ለማዘዝ ስንሰናዳ አንድ ወዳጄ እጄን ጎትቶ እስቲ የተፈጥሮውን እየው አለኝ። እግዜር ውሃን ሲፈጥር እዚህ አካባቢ ነበር እንዴ ያስብላል። የጀበና ቡና እዛው ጋር ወጣ ብለን ጠጣን። ልጅቷም ጥሩ ቡና ከጥሩ ፈገግታ ጋር ቸረችን። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወደ አ.አ የመልስ ጉዞውን ጀመርን። ለጥቂት ደቂቃ ዝምታ ሰፈነ ብዙም ሳይቆይ የኋላው ደጀን ለቤት ይዞት የመጣውን እርጎ ጎንጨት አለ መሰል አለኝ የሚለውን ሙዚቃ ያንቆረቁር ጀመር። ያው የድምፅ ነገር እንዳለ ነው። እኛ የ90ዎቹ ነን መሰል ወደ ልጅነትም መለስ ቀለስ ይባላል። ቆይ እኛ የስንተኞቹ እንደሆንን የማናውቀውስ ምን ብለን እንዝፈን ብቻ ይቺ የደ.ብርሃን እርጎ ስንሄድም ስንመለስም ለውጥ አላት ልዩነት ፈጣሪ ነች።

ጉዞውንም መጨረሳችንን ለማብሰር ይመስላል 'እዚህ ጋር ወራጅ' አለ የሚል ድምፅ ሹፌሩን አስቆመው ያው ለደ.ብርሃን ቀረብ ያለ አካባቢ መሰለኝ።።።

እኔም መውረጃዬ ስለሆነ በሌላ ጉዳይ እስክንገናኝ ደህና ቆዩልኝ ሹፌሩንም በሰላም ያሳድርህ በሉልኝ።              በዚህ አጭር የበውቀቱ ስዩም ግጥም ልሰናበት .....

ተፈጥሮን ደጅ ልጥና

ባዲስ መንገድ ትስራኝ፣ባዲስ የፍጥረት ውል

መስኮትሽ ላይ ሆና

ስትዘምር የምትውል

ድንቢጥ ወፍ ታድርገኝ

ብኖር አንቺን አየሁ፣ ከመሞት ምን ሊገኝ?

......>...... ተፈፀመ.....

by @sa_mee

@sunsethiking

Report Page