Mushe Semu

Mushe Semu


የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው

በኢኮኖሚ ባለሙያው ሙሴ ሸሙ የተጻፈ ፦

" ሰሞኑን የታወጀው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ ተግባራዊ የሆነው አቅምና አማራጭ በማጣት እንጂ የኢትዮጵያን እድገትና የልማት ፍላጎቶች የሚያሟላ በመሆኑ ብቻ አይደለም።

ለዚህ ደግሞ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ለአንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየው " ዲቫሊው አድርግ አላደርግም " አስጨናቄ ድርድር፣ ተጽእኖ፣ ውጣ ውረድና ዲፕሎማሲ ምስክር ናቸው።

በተጽእኖ የተተገበረ ፓሊሲ መሆኑ የሚፈጥረው ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚያስከትለው ለውጥ ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት የአጭር ጊዜ ተጽእኖውን መገምገም ግንዛቤ የሚሰጥ ይመስለኛል። 

IMF ' Choosing an Exchange Rate Regime' በሚል ርዕስ ' Financial Development ' መጽሔት ቮሊዮም 46 ቀጥር 4 ላይ ካቀረበው ጥቅስ ልነሳ። 

' Compared with pegged (Fixed exchage rate) regimes, floating exchange rates are at less risk for overvaluation, but they also fail to deliver low inflation, reduced volatility, or better trade integration '

' ከቋሚ የውጭ ምንዛሪ ተመን ጋር ሲነፃፀሩ ተንሳፋፊ/ ነጻ የምንዛሪ ተመን ስርዓቶች ለከፍተኛ ዋጋ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው፣ ነገር ግን የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር፣ በመቀነስና የተሻለ የንግድ ውህድ ስርዓትን ከማምጣት አኳያ ተግዳሮቶቹን ከማረምና ከማረቅ አኳያ ከሽፈዋል። ' ይላል።

መንግስት ሰለ ፓሊሲው ጠቀሜታና ጠንካራ ጎን መጠነ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል። ፓሊሲው ጠንካራ ጎኖች አሉት። ነገር ግን ፓሊሲው ሊደቅን ስለሚችለው ተግዳሮት ምንም የተባለ ነገር የለም። 

በዚህ ጽሁፍ ለንጽጽር እንዲጠቅም ተግዳሮቶቹ ላይ አተኩራለሁ።

ጠንካራ ጎኑን በሚመለከት በስፋት ከብሔራዊ ባንክ ሰነድ ላይ መረዳት ትችላላችሁ።

- ገበያ መር ( Free Floating) የውጭ ምንዛሪ ስርዓት በተረጋጋ፣ በቂ አቅርቦትና ምርታማነት እውን በሆነበት ኢኮኖሚ ላይ ተመስርቶ ካልተተገበረ በስተቀር ውጤታማነቱ አስተማማኝ አይደለም። ለምን ?!

- እጅግ የናረ ፍላጎትና የአቅርቦት እጥረት ያለበት ኢኮኖሚ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ላይ ሲተገበር የውጭ ምንዛሪው ዋጋ የሚዋዠቅና በከፍተኝ ደረጃ የሚለዋወጥ ባህርይ ስለሚኖረው የምንዛሬ ተመኑ ከየት ተነስቶ የት ሊያደርስ እንደሚችል መገመት ያዳግታል። 

- እንደሚታወቀው ኢኮኖሚያችን የሚያመነጨው የውጭ ምንዛሪ መጠን ዝቅተኛና ፍላጎታችን የሚያጠረቃ ስላልሆነ የውጭ ምንዛሪውን ተመን ለገበያ ውድድር ብቻ መተዉ፣ የማያቋርጥ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ንረትና ጡዘት ሊያስከትል ይችላል። 

- የብር የመግዛት አቅም መዳከምን ተከትሎ አገልግሎት፣ የጉልበት ዋጋን ጨምሮ፣ አቅርቦት/ ፍጆታ ነዳጅና ማዳበርያ... ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ስለሚያሳዩ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ሊንር ይችላል። 

- በሰላም እጦት ምክንያት ኢኮኖሚው በምርታማነት፣ በኤክስፓርት፣ በነጻ ግበይትና እንቅስቃሴ ስለማይደገፍ አቅርቦት ተዳክሞ የዋጋ ንረቱ ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል።

- እንደመነሻ በሚቀመጠው ቅድመ ገበያ ተመን ምክንያት ተቀማጭ ገንዘብ በባንክም ሆነ ቤቱ ወይም በኪሱ ያለው በቅድመ ገበያ ተመኑ ልክ የመግዛት አቅሙ ያሽቆለቁላል/ይደህያል (30% ከትናንት ጀምሮ)።

- መጠነ ሰፊ ድጎማን ለማስተናገድ የሚያስችል በጀት ቀድሞውኑም በእቅድ ስላልተበጀተለት ለድጎማ የተለየ በጀት መበጀት ግድ ይላል። የዘንድሮ በጀት የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።

- በውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት እስካልጠበበ ድረስ ኮንትራባንድ አንዱና ዋነኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሆኖ ይቀጥላል። የኮንትራባንድ ፍላጎትን ለማሟላት የጥቁር ገበያው ከሚያሳድረው ተጽእኖ የተነሳ ሕጋዊ የውጭ ምንዛሪ ተመንን እየመራ ይቀጥላል።

- ብድር በተገኘ የውጭ ምንዛሪ ምክንያት ተቀማም (Reserve) ስለሚያድግ እድገቱን ተከትሎ የሚፈጠረውን የብር ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ ብር ሊታተም ይችላል።  

- በዚህ ምክንያት ብዙ ብር በጥቂት ምርት ላይ መረባረቡን ስለሚቀጥል ግሽበት ተጠናክሮ ይቀጥላል። የዋጋ ንረትና ግሽበት አብዛኛውን ተጠቃሚ ከጫወታ ውጭ ያደርጋሉ። ፍላጎት ሲዳከም ምርታማነት ሊቀንስ ይችላል። ድህነት ሊበረታና ማህበራዊ ቀውስ ሊስፋፋ ይችላል።

- የውጭ ምንዛሪ የመግዛት አቅም መጎልበትና የብር የመግዛት አቅም መዳከም ለኤክስፓርት አንድ መስፈርት እንጂ ብቸኛ መስፈርት ስላልሆነ የምርት ጥራት፣ አስተማማኝ የምርት አቅርቦት፣ ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎትና ከሙስና የጸዳ የጉምሩክ አሰራር ካልተስተካከለ ኤክስፓርት አያድግም። 

- የጉልበት ዋጋ መናገር፣ የጥራት ጉድለት፣ የመብራትና የወኃ ደካማ አቅርቦት፣ ሙስና መስፋፋት፣ ቀልጣፋ የጉምሩክና የባንክ አሰራር አለመኖር ውድ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ላይ ሲታከል አምርቶም ሆነ አርሶ ኤክስፓርት የማድረግ ተግባርን ወጭ ስለሚያንሩት የኤክስፓርተር አዋጭነት ጥያቄ ላይ እንደወደቀ ሊቀጥል ይችላል። 

- ሰላም እስካልተረጋገጠ ድረስ የኤክስፓርት ምርቶችና አቅርቦቶች በመጠንም፣ በጥራትም ሆነ በቅልጥፍና ወደ ገበያ ስለማይቀርብ ኤክስፓርት እንደተዳከመና አክሳሪ እንደሆነ ሊቀጥል ይችላል። 

- ኤክስፓርት አክሳሪ ሲሆን ኪሳራውን ለማካካስ ሲባል ኪሳራውን የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ላይ ስለሚጫን የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ያለተቆጣጣሪ አሁኑ ካለው በላይ እጅግ ሊያንረው ይችላል ።

- የሰላም እጦትን ተከትሎ ሀገር በቀልም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች ፍላጎት ማጣት ኃብት ማሸሽ መሰደድና ሌላ አማራጭ ሀገር መፈለግ ይቀጥላል። ዋጋ የማረጋጋት ሚናቸውም እንደተዳከመ ይቀጥላል።

- በብድር የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከተጠበቀው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው (10.7 ቢሊየን ታቅዶ 3.4 ተፈቅዷል፤ ተጓዳኝ አነስተኛና መካከለኛ ብድር ሊኖሩ ይችላሉ) ከዚህም ውስጥ በአጭር ጊዜ 1 ቢለየን ዶላር ብቻ ስለሚለቀቅ እጥረቱ መባባሱ የሚጠበቅ ነው። 

- የተገኘው ብድርም ሆነ እርዳታ እሴት በሚፈጥሩ የእድገትና የልማት ስራዎች ላይ ካልዋለ በእዳ ላይ የዋለ ተጨማሪ እዳ ከመሆን ባሻገር ኢኮኖሚያችንን በማጠናከርም ሆነ በማሳደግ ትርጉም ያለው ሚናው ሊኖረው አይችልም። 

- እዳን በሌላ በእዳ (Good Money after Bad Money) መተካት አቅም የፈጠሩትን ጥቂት እዳ ከፋይ የኢኮኖሚ ዘርፎች በማዳከም ሸክም በመሆን ሊያዳክማቸውና ከገበያ ሊያስወጣቸው ይችላል።

- ቃል የተገባው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የሚለቀቀው በገደብ ትንሽ በትንሽ ስለሆነ እዳው በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ተጠናቆ ከመግባቱ በፊት በየትኛውም ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ ሊቋረጥ ይችላል። (ፓለቲካዊ እጅ ጥመዘዛ)

- የአብዛኛዎቹ ባንኮች (Open Position) ኤል ሲ ተክፍቶ ክፍያ ባልተከፈለበት የተከማቸ ተንጠልጣይ የውጭ ምንዛሪ ምክንያት በቢሊየን ብር ይከስራሉ። ይህንን ኪሳራ ለማካካስም ወለድና ቻርጆችን በመጨመር የዋጋ ንረቱን ሊያባብሱ ይችላል።

በጥቅሉ በተረጋጋ ማይክሮና ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ያልተመሰረተ በነጻ ገበያ ብቻ የሚተመን የውጭ ምንዛሪ አሰራር በተሞከረባቸው ሀገራት በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ከሽፏል። የስፔይን፣ የግሪክ፣ የአይስላንድና የፓላንድ ልምድን መገምገም ይቻላል። 

በመጨረሻም ተሳካላቸው የተባሉ ሀገራት የውጭ ምንዛሪ ፓሊስያቸው ምን ይመስላል በጥቂቱ እንይ

ሲንጋፓር 27.7 ቢለየን ዶላር የሚደርስ ፓዘቲቭ የንግድ ባላንስ ያላት ሀገር ናት። ሲንጋፓር ዛሬም የምትከተለው floating with the band/Managed floating የምንዛሪ ፓሊሲ ነው። በከፍተኛና በዝቅተኛ ተመን ውስጥ መጫወትን ብቻ የሚፈቅድ ነው። ኢትዮጵያ ግን 14.27 ቢሊየን ዶላር የንግድ ጉደለት ያላባት ሀገር ናት ምርጫዋን ገደብ የሌለው ገበያ መር (Full floating) የውጭ ምንዛሪ ምጣኔን የመረጠች ሀገር ናት። 

- ቻይና የኤክስፓርት ንግዷን ለማስፋፋት ማኔጅድ የውጭ ምንዛሬ ተመን ትጠቀማለች በዮዋን (Yuan /CNH) ኦፍሾር እና በዮዋን Yuan/ CNY) ዶመስቲክ

- ሳዑዲና ዮ.ኤ.ኢ ... ገደብ ከሌለው ዝውውር ጋር ቋሚ የውጭ ምንዛሪ ተመን ይጠቀማሉ። 

- ሩሲያ በተራዘመ ሂደት ቋሚ፣ ማኔጅድ በማለት አሁን ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ስርዓት ተሸጋግትጠቀማለች።

- ብራዚል ሁለቱንም ቋሚ/ ማኔጅድ ተመንና ገበያ መር የምንዛሪ ተመን ትጠቀማለች።

(ሙሼ ሰሙ - የኢኮኖሚ ባለሙያ)

Report Page