MoE

MoE


ትምህርት ሚኒስቴር ፤ በአዲሱ ረቂቅ የትምህርት እና ጥናት ፖሊሲ ከቅድመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ከፍል የሚሰጥ ትምህርት #ነፃ እና #አስገዳጅ እንደሚሆን አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የስርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሸዋረገድ ለኢቢሲ በሰጡት ቃል " በአዲሱ የትምህርት ፍኖታ ካርታ ግኝት መሰረት ዜጎች ከቅድመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በግዴታ እንዲማሩ ለማስቻልና የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን የተሳለጠ ለማድረግ አጠቃላይ የትምህርት ረቂቅ አዋጅ ተግባራዊ ይደረጋል " ብለዋል።

ፍኖተ ካርታውን ለማዘጋጀት ሲሞከር የትምህርት ዘርፉ ያለበትን ሁኔታ ሊያሳይ የሚያስችል ጥናት መደረጉን ገልፀው መንግስት ለትምህርት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአዲስ መልክ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ገብቷል ሲሉ አስረድተዋል።

በጥናቱ ሂደት ላይ ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር በተለየ ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች ጥናቱን ከማሰራት ይልቅ በሀገር ውስጥ ባሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናቱ እንዲከናወን መደረጉን ገልፀዋል።

በስድስት ዘርፎች ተከፋፍሎ በተካሄደው በዚህ ሰፊ ጥናት በመሰረታዊነት ቅድመ መደበኛና የአንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ፣ የመምህራን ስልጠና፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት፣ የከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያካትተው የትምህርት ስርዓት በተለያየ ቡድን እንዲጠና መደረጉን ኃላፊው ገልፀዋል።

በጥናቱ መሰረት በነባሩ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ የጥራት ችግር፣ የሰው ሀብት ስብዕና ግንባታ ጉድለቶች፣ ከገበያው ፍላጎት ጋር አለመጣጣም፣ የመምህራን ብቃት ማነስ፣ በቴክኖሎጂ አለመደገፍ እና ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት የዘርፉ ቁልፍ ችግሮች ሆነው መለየታቸውን ገልፀዋል።

 

በአዲሱ የትምህርት ፍኖታ ካርታ አንድ አካል በሆነው ስርዓተ ትምህርት ውስጥ የተዘጋጀውን የአሰራር ማዕቀፍ መሰረት በማድረግ ከ2014 ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴርና በክልል የትምህርት ቢሮዎች ትብብር የመማሪያ ማስተማሪያ መፀሃፍት በማዘጋጀት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የሙከራ ትግበራ መካሄዱን ኃላፊው ተናግረዋል።

በዚህ መነሻነት የሙከራ ተግባሩን መሰረት በማድረግ በ2015 ወደ ሙሉ ትግበራ ለመሻገር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶ/ር ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።

(ኢቢሲ)

Report Page