MoA

MoA


#ግብርና_ሚኒስቴር #EPHO

" ዶሮና እንቁላል ያለስጋት መመገብ ይችላል " ግብርና ሚኒስቴር

ግብርና ሚኒስቴር ፤ በቅርቡ የተከሰተው የዶሮ በሽታ በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ሕብረተሰቡ ያለምንም ስጋት ዶሮና እንቁላል መመገብ እንደሚችል አሳውቋል።

ሚኒስቴሩ ይህን ያሳወቀው ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ለኢዜአ በሰጠው መግለጫ ነው።

ባሳለፍነው ሰኔ ወር መባቻ በቢሾፍቱና በምዕራብ አዲስ አበባ የተከሰተው የዶሮ በሽታ ወረርሽኝ በዶሮ እርባታ ቦታዎች ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ያለው ግብርና ሚኒስቴር በሽታው እንደተከሰተ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል ተሰማርቶ የበሽታውን ሥርጭት የመግታት አፋጣኝ ምላሽ መውሰዱን አሳውቋል።

በወቅቱ ለዶሮ እርባታ አገልግሎት ከውጭ የሚገባው የለማ እንቁላልና ዶሮና የዶሮ ውጤቶች ዝውውር ባለበት እንዲገታ የጥንቃቄ መመሪያዎች ለሚመለከታቸው አካላት መተላለፉንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውሷል።

በተጨማሪም ዶሮና እንቁላል አመጋገብ ላይ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ መተላለፉን ገልጾ በሂደትም የጥንቃቄ መመሪያዎች እየተሻሻሉ መሄዳቸውን አሳውቋል።

በሽታውን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ምክንያት በሽታውን በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል ያለው ግብርና ሚኒስቴር አሁን ላይ ምንም አይነት የበሽታ ስጋት ባለመኖሩ ሕብረተሰቡ ዶሮና እንቁላል ያለስጋት በማብሰል እንዲጠቀም፤ ዶሮ አርቢዎችም በሙሉ አቅማቸው ዶሮ በማርባት ለገበያ እንዲያቀርቡ መወሰኑን ገልጿል።

በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ዜጎች ግን በማንኛውም ጊዜ የሚያደርጉትን ‘ባዮ-ሴኪዩሪቲ’ የተሰኘውን የዶሮ እርባታ ጥንቃቄ ሥርዓትን ባጠናከረ አግባብ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በበኩሉ በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ በሰው ጤና ላይ ጉዳት ያስከተለው ጉዳት ካለ ለመለየት ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ጥናት ማከናወኑን ገልጿል።

በጥናቱ ውጤት መሰረትም እስካሁን በሽታው በአንድም ሰው ላይ የጤና ችግር አለማድረሱ አረጋግጧል።

በወረርሽኙ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎች መሞታቸውን የጠቀሰው ኢንስቲትዩቱ በዶሮና የዶሮ ውጤቶች እንቅስቃሴ ላይ እገዳ መጣሉ ደግሞ ዘርፉ ላይ ጉዳት ማድረሱን አንስቷል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት የዶሮ እርባታ ሥርዓትን ማሻሻልና የአርቢዎችን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ትምህርት መሰጠቱናበተለይ በዶሮ እርባታ የሚሳተፉ ዜጎች ዘወትር ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መተግበር እንዳለባቸው አሳስቧል።

(ኢዜአ)

@tikvahethiopia


Report Page