#Mekelle

#Mekelle


የፌደራል ሥርዓት አወቃቀር ለቋንቋዎች እድገት መሠረት ከመጣሉ ባለፈ ኅብረተሰቡም ባደገበት ቋንቋ የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችለው የቋንቋ ምሁሩና ፖለቲከኛው አቶ በቀለ ገርባ ገለጹ፡፡

”ኢትዮ ቋንቋዎችና ጠቀሜታዎች” በሚል ርዕስ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

የኦሮሞ ፌዴሬሊሰት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ እንዳስረዱት አሁን ሕዝቡ በራሱ ቋንቋ እንዲተዳደር፣በራሱ ቋንቋ እንዲማርና የመንግሥት አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አሁን ያለው የፌደራል ሥርዓት አወቃቀርም አልተሰራበትም እንጂ፤ ለቋንቋዎች እድገት ጥሩ መሰረት ጥሏል ያሉት ምሁሩና ፖለቲከኛው አቶ በቀለ፣አወቃቀሩ እንደ መልካም ጅምር በመውሰድ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የራስህን ማንነትና ቋንቋ በሌላ ሰው መጫን ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉ የሌሎች ሰዎች ማንነትና ቋንቋ ማክበር በመቻቻልና በመከባበር የሚያኖረን የተሻለ አማራጭ እንደሆነም አመልክተዋል።

የፌደራል ቋንቋ ከአንድ ቋንቋ በላይ በርከት ያሉ እንዲሆኑ ማድረግ የቋንቋዎች እኩልነት ከማረጋገጥ ባለፈ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉትና በሕንድ የፌደራል መንግሥት ቋንቋዎች 12 ፣በደቡብ አፍሪካ ደግሞ ዘጠኝ መሆናቸወን ለአብነት አቅርበዋል።

በኢትዮጵያም አዋጭነታቸውን በማጥናት በርካታ ቋንቋዎችን የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ  ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

”አንድ ሰው ሁሉም ቋንቋዎች እንዲማር ይገደዳል ማለት ሳይሆን፣ ከቋንቋዎቹ አንዱን ከቻለ እንደሌሎቹ ቋንቋዎች እኩል ተቀባይነት አለውና የመንግሥት አገልግሎት ታገኝበታለህ ማለት ነው” ብለዋል፡፡

በርካታ ቋንቋዎች ማወቅ ከፖለቲካና ከዘር መያያዝ እንደሌለበትም አቶ በቀለ አስረድተዋል፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ የአፋን ኦሮሞ ፊደል ላቲን ከመሆኑ ይልቅ ግእዝ ቢሆን በርካታ የሌላ ብሄር ተወላጆች ለመማር እድል አይሰጥም ነበር ወይ? አንዳ አንድ ፖለቲከኞች ቋንቋ መሠረት ያደረገ የፌደራል ሥርዓት የከሸፈ ነው ይላሉ እርስዎ እንዴት ያዩታል? የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል፡፡

ኦቦ በቀለ በበኩላቸው የአፋን ኦሮሞ ፊደል ቁቤ/ላቲን መደረጉ ህጻናት ሲማሩ በቀላሉና በማያሻማ መንገድ እንዲረዱት ከማሰብ ባለፈ ከፖለቲካ ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌደራል ሥርዓት ከመከተል ውጭ በወንዝና በተራራ ማካለል ተገቢ እንደማይሆን  ተናግረዋል፡፡

ለአገሪቱ የሚበጀው አሁን ባለው የፌደራል ክፍተቶች በማጠናከር ወደፊት መመልከት እንጂ፣ ወደ ኋላ መንሸራተት አይበጀንም ብለዋል፡፡

”ተጨማሪ ቋንቋ መማር ማለት ሙያህን የምትሸጥበት እድል ማስፋት ነው”ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዋነኞቹ አገራዊ  ጉዳዮች መግባባት ለመፍጠር የመነጋገር ባህላችን መዳበር አለበት ነው ያሉት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብደል ቃድር ከድር ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የምሁራን መድረክ እያቀረበ መሆኑንም  ገልጸዋል፡፡

Via #ENA

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page