#Maji

#Maji


በደቡብ ክልል ማጂ ወረዳ ቱም ከተማ በዛሬው ዕለት በተደረገ ተቃውሞ ላይ የጸጥታ ኃይሎች በተኮሱት ጥይት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የሕክምና ተቋም ኃላፊ ለጀርመን ድምፅ ሬድዮ ተናገሩ። የዞኑ ባለሥልጣናት እና የዐይን እማኞችም ጸጥታ ኃይሎች በተኮሱት ጥይት ከተገደሉት በተጨማሪ ሌሎች ከአስር በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል። 

ሰልፉ የተደረገዉ አዲስ በተዋቀረው በምዕራብ ኦሞ ዞን የምትገኘው የማጂ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ መታሰራቸውን በመቃወም ነበር። «አስራ አንድ ሰው [በጥይት] ተመቷል። ሶስቱ ሴቶች ናቸው። ትልልቅ ሰዎች እና ሕፃናትም አሉበት» የሚሉት የዐይን እማኙ «ሰልፍ ሲደረግ መንገድ ይዘጋል። መንገድ ሲዘጋ መከላከያ እና ልዩ ኃይል መጣ። ከዚያ በአካባቢው በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ምንም ነገር ሳያማክር ተኩስ ጀመረ» ሲሉ መነሾውን አብራርተዋል። 

የማጂ ወረዳ ጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ አኩ እንደሚሉት ቱም በተባለችው ከተማ በተደረገው ሰልፍ ስድስት ሰዎች በጸጥታ አስከባሪዎች ተገድለዋል። 

አቶ ከበደ "ዛሬ ጠዋት በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የነበሩ አራት ሰዎች በልዩ ኃይል እና በመከላከያ ሠራዊት በተተኮሰ ጥይት ተመተው እኛ ጋ ተኝተዋል። የሞቱት ሬሳቸው ሳይነሳ እዚያው ነው ያለው። የሞቱት ወደ ስድስት የሚሆኑ ሰዎች ናቸው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በአራት ጥይት የቆሰሉ አንድ ሰው ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ማጂ መላካቸውን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል። 

የምዕራብ ኦሞ ዞን የሚሊሺያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን እንደሚሉት ግን በቱም ከተማ የተገደሉት ሰዎች ሁለት ብቻ ናቸው። «ችግሮችን ለማረጋጋት ዛሬ ቱም ማዕከል ላይ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማው ከገባ በኋላ በፈነዳው ጥይት አንድ ሴት፤ አንድ ወንድ ሞተዋል የሚል መረጃ አለን። አስር ወንዶች፤ ሁለት ሴቶች ቆስለዋል የሚል መረጃ ነው በስልክ እየደረሰን ያለው» ብለዋል። 

በቱም ከተማ የሚገኙት የዐይን እማኝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት «የሚመቱትን መተው ወዲያው ወደ ካምፓቸው ሔዱ» ሲሉ አክለዋል። 

አቶ ሰለሞን በምዕራብ ኦሞ ዞን በምዔኒት እና በማጂ፤ በቤሮ እና በሱርማ የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት አራት ወረዳዎች የተሳተፉበት ውይይት በክልሉ ጸጥታ [መዋቅር] አማካኝነት በቤንች ሼኮ መደረጉን ገልጸዋል። «እነዚህን ችግሮች በውይይት ለመፍታት ለሁለት ቀን ያህል ውይይት ከተደረገ በኋላ የማጂ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ በቁጥጥር ሥር ውለዋል በሚል ነው ማጂ ወጣቱ ነውጥ እያነሳ ያለው» ብለዋል።  

ታሰሩ የተባሉት የማጂ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ «ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ አመራር ናቸው» የሚሉት በቱም ከተማ የሚኖሩ የዐይን እማኝ «ሰውየውን ዞን ላይ በኮማንድ ፖስት አስረውታል። ሕዝቡ ደግሞ ለምን ታሰረ ብሎ ነው ዛሬ ጠዋት ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው» ብለዋል።

የምዕራብ ኦሞ ዞን የሚሊሺያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን «ይኸን ችግር ለማርገብ ከመከላከያም ከልዩ ኃይልም ኅብረተሰቡ ወዳልተፈለገ ሁኔታ እንዳይገባ ሌላ ችግሮችም እንዳይፈጠሩ ዞኑ ርብርብ እያደረገ ነው» ሲሉ ለጀርመን ድምፅ ሬድዮ ተናግረዋል።

[የጀርመን ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ]

Report Page