LifeEx. PROGRAM ON KALTUBE
KALTUBE💐ናይት ክለብ አድሬ በማግስቱ መድረክ ላይ እቆማለሁ!!
........
ለራሴ ያለኝ እይታ ሲበዛ የተጋነነ ነው። ራሴን በጣም ቆንጆ ፣ የፈለገችውን ነገር በፈለገችው ጊዜ ማግኘት የምትችል እና አሁን የተረዳሁት አዲሱ ማንነቴ ድንቅ የማስመሰል ወይም የትወና ሰው ነኝ። ቤተሰቦቼ ገና ድሮ የአሁኑን ዘመን ውጥንቅጥ የሌለበት ክርስትና የኖሩ የቀደሙ አገልጋዮች ነበሩ። ከአያቶቼ ጀምሮ የወንጌል አገልጋዮች ምናልባትም ስማቸውን ብጠቅስላችሁ የምታውቋቸውን ታላላቅ አገልጋዮች በቅርበት የሚያውቁ ነበሩ። እኔም የጥሩ አገልጋይ ባልና ሚስት ልጅ ነኝ። ጌታን በዚ ጊዜ እንደዚ ሁኔታ ላይ ተቀበልኩ የምልበት ወቅት አልነበረም ቤተክርስቲያን ውስጥ ስላደግኩ እዚም እዚያም ስል ቆይቼ መጨረሻ ላይ ወደ ወጣቶች ህብረት ተቀላቀልኩ። በዚያን ጊዜ ያን ያህል በህይወቴ አስከፊ ነገር ላይ አልነበርኩም የቤተሰብም ቁጥጥር ስላለ ማለት ነው።
ነገር ግን አንዱ የህይወቴ ምዕራፍ በእኔ ውስጥ የመሸገውን ክፉ ማንነት ገልጦ አወጣው። ከአራት አመታት በፊት ነበር የሀይስኩል ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ ዩኒቨርስቲ የገባሁበት ለኔም አዲስ የሆነ ህይወት። ዘመድ የሚባል የሌለበት ማንም የማያውቀኝ ስፍራ። ጊቢ የተመደብኩበት ዶርም ስገባ ሶስት ሴቶች ከኔ ቀድመው ገብተው አልጋቸውን አንጥፈው አገኘሁ። ስማቸውንም ሜሮን ፤ ማህሌት ፤ ማህደር እያሉ ተዋወቁኝ የኔም ስም ሜሮን ነበር። በስማችን ቅደም ተከተል ስለተመደብን። አይቼው የማላውቀው ህይወት የተጀመረው አርብ ምሽት ላይ ነበር ሴቶቹ ከምሽቱ 1ሰአት ላይ መለባበስ ጀመሩ የት ልትሄዱ ነው ብዬ ስጠይቅ ኦቨር ልንወጣ ነው አሉኝ። በወቅቱ ምን ማለት እንደሆነ ስላላወቅኩ ጠየቅኳቸው ናይት ክለብ ከጓደኞቻቸው ጋር ሊዝናኑ መሆኑን ነገሩኝ። ክርስቲያን መሆኔን ስላልነገርኳቸው አንቺም ልበሺና አብረን እንሂድ አሉኝ።
አይ ዛሬ ይለፈኝ አልኳቸው። ሁሉም ተሰብስበው ሲወጡ ብቸኝነቱ አስጨነቀኝ። ወትሮም ቤትም የትም ቦታ ብቻዬን ሆኜ ስለማላውቅ ለሊቱን ሙሉ በጭንቀት እና በፍርሀት... ከአሁን አሁን ሰው በመስኮት መጣ ፤ በበር ገባ ፤ አንድ ነገር ሆንኩ እያልኩ ስፈራ አደርኩ። ጠዋት 12ሰአት ላይ ሴቶቹ መጡ አይናቸውን የተቀቡት ኩል ወደታች ወርዶ ፊታቸው ከእንቅልፍ ማጣት ገርጥቶ። ወዛቸው ጠፍቶ ፤ ተዳክመው .....እንደገቡ ወዲያው ተኙ። እኔም ለሊት ስላልተኛሁ ቀን ሁላችንም ተኛን።
አመሻሹን ራት በልተን ድጋሚ ዛሬም እንደሚወጡ ነገሩኝ። ምክንያታቸውም "ቅዳሜ ነዋ!" የሚል ነበር። ብቻዬን ማደሩ በጣም አስጨነቀኝ። በቃ አብሬያችሁ እመጣለሁ አልኳቸው። ምንም አልተደነቁም። እሺ አሉ። ወደ ዶርማችን ገብተን ከነርሱ ልብስ በነርሱ ምርጫ ሰጥተውኝ ለብሼ ብርዱ እያንቀጠቀጠኝ ከጊቢ ወጥተን ታክሲ ተራ ሄድን።
. . . የክለቡ ደማቅ ቀይና ወይንጠጅ መብራቶች አይኔ ላይ የተለየ ስሜት ፈጥረውብኝ ነበር። እነርሱ እየተሳሳቁ ወደ አንዱ ጥግ ወዳለ ሶፋ ሄደን ተቀመጥን መጠጥ አዘዙ እኔ ጨጓራዬን ያመኛል ለስላሳ ይሁንልኝ ስል ሳቃቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። ወይን አይጎዳሽም ብለው አዘዙልኝ።
...ብዙ እንደጠጣሁ አላስታውስም ግን ለምን ያህል ደቂቃዎች ራሴን ሳላውቅ እንደቆየሁ ባላውቅም ድንገት አጠገቤ አንድ ነገር ሲቀመጥ ሲሰማኝ ባነንኩ። እድሜው በ60ዎቹ መሀል የሆነ ሰውዬ ነበር። ሴቶቹ አጠገቤ አልነበሩም። በድንጋጤ ተነስቼ ከሱ ሸሽቼ ስመለከት መሀል ሆነው ከብዙ ሰዎች ጋር ሲጨፍሩ አየኋቸው። ቀምሼው የማላውቀው መጠጥ ፤ የሙዚቃው ጩኸት ፤ የሰው ጩኸት ....ብቻ ምሽቱ ለኔ አድካሚ ምንም ስሜት ሊሰጠኝ ያልቻለ ቢሆንም ለነርሱ ግን ደስታ ነበር። እንደ ትናንቱ ቀኑን ሙሉ ተኛን።
ትምህርታችን ለሳምንታት እንደማይጀመር ስናውቅ በየቀኑ መውጣት ይባስም ብሎ ወደነርሱ አካሄድ መቀላቀል ጀመርኩ። ሲጨፍሩ ማደር ፤ ከእድሜ እኩዮቻችን ወንዶች ጋር ጓደኝነት መፍጠር ተቀጣጥሮ መሄድ ጀመርን። ወንዶቹ ደግሞ የተለያዩ ነገሮችን ማጨስ አስለመዱን። ታድያ በነዚህ ቀናት መሀል ጊቢ ያሉ ሶስት የክርስቲያን ህብረቶች መሪዎች ዶርም ለዶርም ሲዞሩ እኛ ጋር አንድ ቀን መጥተው ስልኬን ወሰዱ። ያን ቀን ፕሮቴስታንት መሆኔን ጓደኞቼ አወቁ ግን ምንም አልመሰላቸውም። ምንም አላሉኝም።
ከፌሎ ተደውሎልኝ ህብረቱን መካፈልም ጀመርኩ የኳየር አገልግሎት እና የቻሪቲ ቡድን ውስጥ ገባሁ። ጥሩ ድምፅ ስለነበረኝ በቅርብ መድረክ ላይ እንደምቆም ሁለቱም ሴት መሪዎች ይነግሩኝ ነበር።
ትምህርት ጀምረንም እንኳ ከሰኞ እስከ እሁድ ገንዘብ ባለን ጊዜ ሁሉ እንወጣ ነበር። የፌሎ ህብረት ፕሮግራም ቀኖችን ብዙ ጊዜ እዘላቸው ነበር። ግን የኳየር ጥናት አልቀርም ነበር ፤ ይሄኔ ነበር የከፋው ነገር የመጣው ከኔ ጋር የተሻለ መቀራረብ ከነበረው ልጅ ጋር በጣም ማጨስ ጀመርኩ ፤ ነገርየው ሳይታወቀኝ ሱስ ሆነብኝ። ሴት በመሆኔ በቀላሉ እይታና ጥርጣሬ ውስጥ ባልገባም ጊቢ ውስጥ ያለበት ድረስ እየሄድኩ አብረን ማጨስ ጀመርን። ማታ 11ሰአት ኳየር ከመግባቴ በፊት ከሱ ጋር አጭሼ ዶርም ተመልሼ ልብስ ቀይሬ ፤ ማስቲካ ገዝቼ ነበር የምሄደው።
አንድ ቀን ለመጀመርያ ጊዜ ለአምልኮ መሪነት መድረክ ተሰጠኝ። ፌሎ ዝግጅት ቅዳሜ ከሰአት ስለነበር እኔና ጓደኞቼ አርብ ለሊቱን ሙሉ የተለመደው ኑሮአችን ላይ ነበርን። ቅዳሜ የደነዘዘ አካሌን ቀድቼ ባመጣሁት ውሀ አጥቤ ሄድኩ። መድረክ ላይ ቆሜ ስዘምር ከአፌ የሚወጡት ቃላቶች ሁሉ ይቀፉኝ ነበር። አልረሳውም የዘመርኩት ዝማሬ "..ለፍቅሬ መግለጫ ላድርግ የቻልኩትን.... ጥሜን ባይቆርጥልኝ ባያረካም ውስጤን... ትናንትም ብያለሁ ዛሬም እደግመዋለሁ....መተኪያ የለህም እኔ እወድሀለሁ...." የሚለውን ነበር። ራሴን የዛን ቀን እንደጠላሁት የጠላሁበት ቀን ኖሮ አያውቅም። በእርግጥ ምንም የሚያይ ሰው አልነበረም ህብረቱ ውስጥ ያሉት ግማሽ ልጆች እንደኔው ክለብ ውስጥ አይቼያቸው ገጥመውኝ ሁላ ያውቃል። የቀሩት ደግሞ ለሰው ግድ የማይሰጣቸው ምንም ስሜት የሌላቸው ፤ ግዴለሽ ነበሩ።
ህይወቴ በዚህ መልክ ግማሽ አመት ከሆነው በኋላ አንድ ነገር እንድለወጥ ምክንያት ሆነኝ። በቀጣይ ሴሚስተር ዶርም እንደ አዲስ እንደምንመደብ እና በየትምህርት ዘርፋችን እንደሚሆን ተነገረን። ጓደኞቼ አብረን ዶርም እንይዛለን አንለያይም ቢሉም እኔ ግን አማራጩን እየተመለከትኩ ነበር። ከቀናት በኋላም ወደ አዲሱ ዶርም ጎራ ብዬ ተመለከትኩ.... ሁለት ጥግና ጥግ የተቀመጡ ሴቶች ነበሩ። ፀጥታው ፥ እርጋታው እና ሰላሙ ደስ ስላለኝ ብቻ ትንሽ ቀን ልሞክረው ብዬ ከጓደኞቼ ተለይቼ እዛ ገባሁ። ለሊት ወደ 6ሰአት ላይ ድምፅ የሰማሁ መስሎኝ ስነቃ አንዷ ተንበርክካ ስትፀልይ ተመለከትኳት። ገርሞኝ ተኛሁ.....ገና በጠዋት ደግሞ ሁለቱም አብረው ሲፀልዩ ከእንቅልፌ ቀሰቀሱኝ። ክርስቲያን መሆናቸውን ነገሩኝ። እኔም ነገርኳቸው። ህብረት ላይ እንደማይሳተፉ ራሳቸውን በራሳቸው እንደሚበረታቱ ነገሩኝ። ለመለወጥ አዕምሮዬ ፈቃደኛ ባይሆንም በልቤ "ደስ ይላሉ" አልኩ። በየቀኑ መፀለይ ብቻ ሳይሆን እኔንም እየቀሰቀሱ አብረን እንድንፀልይ ማድረግ ጀመሩ። መጀመርያ አካባቢ በመሰላቸት በንዴት የጀመርኩት ነገራቸው በኋላ በጣም የምናፍቀው ነገር ሆነብኝ። ውስጤ ሲታደስ ይታወቀኝ ነበር። ጓደኞቼን ሰበባ ሰበብ እየፈጠርኩ መራቅ ጀመርኩ። አዲሶቹ ጓደኞቼ ውስጤ የማላውቀውን ያልተለማመድኩት ከዚህ አለም ላቅ ወዳለ ነገር ከተቱኝ። በኛ ፍሎር የሚገኙ ሌሎች ክርስቲያኖችም ተቀላቀሉን።
በኋላ ላይም ብዛታችን ከመጠን በላይ ሲሆን ወንድ ክርስቲያኖችም እንዲካፈሉ ቸርች ውስጥ ህብረት ማድረግ ጀመርን። ሁላችንም እርስ በርስ ግልፅ ነበርን። አንድ ቀን እኔም ታሪኬን ነገርኳቸው ሌሎችም ብዙ የነበሩበትን ነገር አወሩን። አብረን እግዚአብሔርን ስላስመለጠን አመሰገንን። የማይረሳ 2አመታትን ከዛን በኋላ አሳለፍን።
በኋላ ላይ በህይወቴ እጅግ ደስተኛ የሆንኩት ለነዛ ጓደኞቼ ለሴቶቹም ለወንዶቹም ሳልታክት ሳልሰለች መገፋቴን እየቻልኩ ስለ ጌታ ኢየሱስ ማዳን ፤ ስለ ዘልአለም ህይወት ....ለመዳን. ምንም የሚጠበቅባቸው ነገር እንደሌለ ኢየሱስ ዋጋውን ሁሉ መክፈሉን። በርሱ በማመን ብቻ እንደሚድኑ ፤ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን እንደሚችሉ። ንፁህ ፣ ጳድቅ ፣ አዲስ ፍጥረት መሆን እንደሚችሉ እነግራቸው ነበር። በጣም ደስ የሚለው ከግማሽ በላዮቹ ጌታን በአመቱ ተቀብለው ህብረታችንን ተቀላቀሉ። የቀሩት ደግሞ የመጨረሻው የጊቢ አመቴ ላይ ጌታን መቀበል እንደሚፈልጉ ነገሩኝ።
አሁን ላይ እኔ ተመርቄ ስራ ይዣለሁ። ጌታ ኢየሱስን በስራዬ በኑሮዬ እና በቤቴ የበለጠ እየገለጥኩት ነው። ያኔ በነዛ ሁለት ንቁ ወጣቶች የተጀመረችው የጊቢያችን ህብረት አድጋ ጊቢው ሙሉ አማኝ ያልሆኑ ሁሉ የሚመጡባት ትልቅ ህብረት ሆና አድጋለች። እግዚአብሔር ለቃሉ ታማኝ ነው። በኔ አይነት ህይወት ያሉ ወጣቶችን አስሶ የሚፈልግ ፤ የሚለውጥ ራሱን የቻለ "ኤልሮኢ" የሚባል ቡድን መስርተው እያገለገሉ ይገኛሉ። እግዚአብሔር ስለ ሁሉም ነገር ይመስገን።
------------------------------------------------------------
▪LifeEx. ( By Kaltube )
የቀደሙ ታሪኮች
Story Two :- የእግዚአብሔርን ክብር ከልቡ የሚራብ ትውልድ እየጠፋ እንዳለ ይሰማኛል ልቤ በራሴም በሰዎችም ያዝናል ( ይሄን_ይጫኑ )
Story One :- ቁጣዬን መቆጣጠር ከሰው ጋር ሳልጣላ መኖር አቃተኝ ( ይሄን_ይጫኑ )