LIFE EX. PROGRAM

LIFE EX. PROGRAM

ANOTHER STORY ON KALTUBE

💐የእግዚአብሔርን ክብር ከልቡ የሚራብ ትውልድ እየጠፋ እንዳለ ይሰማኛል ልቤ በራሴም በሰዎችም ያዝናል

.......

ጌታን ያገኘሁበትን 2ተኛ አመት ለብቻዬ በማስብባት ልዩ ቀኔ እንደሌላው ጊዜ ደስተኛ አልነበርኩም። ምክንያቱም በህይወቴ ከአመት አመት እጅግ ደክሜዬለሁ። ጌታን ስቀበል በእውነቱ ወንጌልን ተረድቼ አልነበረም በቅንነት ነበር። ኋላ ላይ ግን መፅሐፍቅዱን የበለጠ ሳነብ ከእግዚአብሔር ጋር በፀሎት ስጣበቅ ወንጌል ምን እንደሆነ። እግዚአብሔር ምን አይነት አምላክ እንደሆነ ለፈጠራቸው ህዝቦች ምን አይነት በጎ ሀሳብ እንዳለው የበለጠ እየተረዳሁ ስሄድ ህይወቴን ለሱ አብልጬ ሰጠሁ ጊዜዬን በፀሎትና በአገልግሎት ከመጣበቡ ብዛት ምግብ ሳልበላ የምውልባቸው ቀናት ብዙ ነበሩ። በህይወቴ ግን ፍፁም እርካታ ነበረኝ። የበለጠ መሻቴ የነበረው ፍጥረት ሁሉ ኢየሱስን እንዲያውቅ ከዘልአለም ሞት እንዲድን በመሆኑ ወንጌል በገባሁበት ቦታ ሁሉ ያልመሰከርኩበት የለም ላብ እስኪያጠምቀኝ ድረስ በአደባባዮች ቆሜ የጌታዬን ማዳን አወራ ነበር። ወደ ቤቴም ስመለስ ለሰአታት በእግዚአብሔር ፊት ተንበርክኬ ትውልዱ እሱን እንዲያውቅ አይኖቹ እንዲበራለት የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥ አጥብቄ በእንባ እፀለይ ነበር። 

አንድ ወቅት ላይ ቤተሰቤ ከተማ ልንቀይር መሆኑን አሳወቁኝ። ወደ አዕምሮዬ የመጣው ግን ያቺ ቀኑን ሙሉ የምውልባት የቤተክርስቲያን ክፍል ፤ እነዛ ለእግዚአብሔር ፈቃድና ሀሳብ የተሰጡ ንፁህ እና ታታሪ ወንድሞቼ እና እህቶቼን መለየቱ ነበር። በቤተሰቤ ስር ኑሮዬ ግዴታ በመሆኑ አማራጭ አልነበረኝም ሞቅ ወዳለው ግርግርና ትርምስ ወደ ሞላው ከተማ አዲስአበባ ከቤተሰቤ ጋር መጣን። ሰፈራችን አካባቢ በግዝፈታቸው ተለቅ ያሉ ብዙ ሰው የሚታደምባቸው ቤተክርስቲያኖች ነበሩ። ከነርሱም በታች አነስተኛ ቁጥር ያለው ሰው የሚይዙ ቤተክርስቲያኖችም ነበሩ። ቤተሰቤ አባል ሆነን እንድንካፈል የመረጡት ትልቅ ወይም Mega Church የሚባለውን ነበር። መጀመርያ አካባቢ ላይ በህይወቴ በፀሎቴ ላይ የህይወት ልዩነት አልነበረኝም በትጋት እፀልይ አገለግል ነበር። ኋላ ላይ ግን የቤተክርስቲያኑን የተለያዩ ህብረቶች መቀላቀል ጀመርኩ በገባሁበት ህብረት ያለነው ወጣቶች እጅግ ብዙ ስንሆን እኛን ለመከታተል ከኛ በእድሜ ከፍ ያለ ሰው ህብረቱን ይመራ ነበር። ህብረቱ ውስጥ ከልቡ አጠገቡ ላለው ሰዉ የሚጨነቅ ፤ ፊቱ ከመፀለይና በእግዚአብሔር ፊት ከመሆን ብዛት የወዛ ሰው ማግኘት ይከብድ ነበር። ሁሉም በሳምንት አንድ ቀን መርሀግብር የሚያደርግበት ስፍራ እንጂ ምንም ለህይወት የሚተርፍ ነገር እንደሌለበት በተደጋጋሚ አየሁ። በህብረታችን የነበሩት እህቶች የሚያስጨንቃቸው አለባበስና ውበት እንጂ ከልብ ለእግዚአብሔር መኖር መላ ህይወትን ለርሱ መስዋዕት አድርጎ መስጠት አልነበረም። በወንድሞች በኩል በመፅሐፍቅዱስ ጥናታችን ሰአት የማይሰማው ድምፃቸው የኳስ ወሬዎችን እና አዲስ የወጣ መዝሙር ቪዲዩ ለማውራት ሲሆን መደማመጥ ያቅታቸዋል። የሆነ ነገር ጎድሏል ብዬ ብዙ ጊዜ አስባለሁ። በነርሱ እይታ ከገጠር የመጣሁ በአለባበሴም ደካማ ስለነበርኩ ብዙዎቹ አይቀርቡኝም ነበር። ልቤ ላይ ያለውን ሸክም የሚጋራኝ ለፀሎት ልቡ ክፍት የሆነ ስለ እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ሲሰማ ሀሴት የሚያደርግ ሰው ማግኘት ከበደኝ። ተንበርክኮ ከመፀለይ ይልቅ እለት እለት የህብረታችንን ጉድለት ማሰላሰል ብቻ አበዛሁ። ቀድሞ ከነበረኝ ህብረት ጋር ነገሮችን በማነፃፀር ራሴን ወደማይገባ ድብርት ከተትኩት። አዎ እዚህ ያለሁበት ስፍራ እልም ያለ ደረቅ ምድረበዳ ነው። መንፈስ የሌለበት የደቂቃዎች ፀሎት ፤ የድምፅ ውበት መፈተኛ እና ጩኸት ብቻ የሆነ አምልኮ።.....አስጨነቀኝ።.... የራሴን ባላንስ ላለማጣት እየተንገዳገድኩም ለመቆም ሞከርኩ ግን አቃተኝ። የክርስትና ህይወቴ ከእግዚአብሔር ፤ ከቃሉ ፤ ከፀሎት በራቀ ቁጥር በፊት የተረዳኋቸው መገለጦች የነበረኝ መሻትና ረሀብ ሁሉ ከልቤ ጠፉ። ይበልጥ ደግሞ ከቤተክርስቲያን ውጪ ወጣት ክርስቲያኖች በህይወታቸው የሚያደርጉትን ያልተገባ ሀጥያት በአይኖቼ ማየት ስጀምር ፤ ሳምንቱን ሙሉ በሀጥያት ተመላልሰው በሳምንት አንድ ቀን በልበ ሙሉነት ያለ ወቀሳና ኩነኔ ህብረት ፕሮግራም አለኝ ብለው ሲመጡ ሳይ ከበደኝ። በነርሱ ላይ አልፈርድም ነበር በእርግጥም የሚከታተለን እረኛ አልነበረንም። በትንሽ ከተግባባኋቸው ጋር ስለ እግዚአብሔር ጥቂት ሳወራ ፊታቸው ላይ መሰላቸት ይታየኝ ነበር። አፍ አውጥተው ባያወሩትም በእግዚአብሔር ቤት እያሉ የሉም ነበረ። ለመፀለይ አንገታችንን ስንደፋ ቤቱ በዝምታ ተውጦ ያስጨንቀኝ ነበር። እንደኔ ሁሉም በራሱ ሀሳብ የሚመላለስ እንጂ የሚፀልይ ያለ እስከማይመስለኝ ድረስ። 

ከቤታችን ራቅ ወዳለ ሰዎች ወደማይመጡበት ቦታ ተቀምጬ ትውልዱ ለእግዚአብሔር ፍቅር አለኝ የሚለው ውሸቱን ነው እንድል አደረገኝ። ተቀባይ ከሌለ እግዚአብሔር ክብሩን በማን ይገልጣል። ኑሮአችን ለእግዚአብሔር መንፈስ መስራት የሚመች አለመሆኑን ደጋግሜ አሰብኩ ፤ እንደ ድሮው ግን ውስጤ የነበረው እሳት በርዶ ዝምታና ፤ መተያየት ከውስጤና ከውጪው አለም ጋር ሙግት መግጠም ላይ ብቻ ነበርኩ። ወጣቶች ጊዜያዊ ደስታቸውን አስበልጠው ጌታን ያሉ እየመሰሉ ሊሸውዱት ይሞክራሉ። ግን ያውቃል የሉም..... በመንፈስ የተሞሉ መስለው ለስላሳ ዝማሬዎችን ሲዘምሩ ይታያል ህይወታቸው ግን ውስጡ ባዶ ነው። ለእግዚአብሔር ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት የማይወጡት ግብግብ ሆኖባቸዋል። በትልቁ በትንሹ መረበሽ ፤ ብቸኝነት ፣ ፍርሀት ፤ ግራ መጋባት እና ጭንቀት ቤታቸውን አማኝ ነኝ በሚሉ ላይ ሰርተው ሳይ ለሌላ ትውልድ ቀርቶ ይሄ ትውልድ ለራሱ ይሆናል ወይ ብሎ አስጨነቀኝ። አገልጋዮች አገልግሎትን ገበያ አድርገው በገንዘብ ሲተምኑ ፤ ነቢያት ነን ባዮች በአባቶች ተከብሮ የመጣውን የጌታን ስም እየጠሩ አደባባይ ላይ ሲቀልዱ ፤ በአህዛብ ዘንድ እምነታችን የቀልድና የፌዝ ምንጭ ሲሆን የሚከላከል ንፁህ እምነት ያለው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ቁጥር ትንሽ ሲሆን ሳይ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገባሁ።

በተስፋመቁረጥ የጀመረው ውድቀቴ ከእግዚአብሔር በመራቅ ማስመሰል ከሞላው ህብረታችን በመራቅ ከቤተሰብ ህብረት በመራቅ በብቸኝነት አለም አስቀረኝ። በብቸኝነቴ ወቅት ሌላ ራሴን ያስለመድኩት የምሰራው አንዳች ስላልነበረኝ እንደ አብዛኛው ወጣት ስልክ እና ኮምፒውተር ስላልነበረኝ ከብቸኛዋ ጓደኛዬ መፅሐፍቅዱሴ ስርቅ ድብርት እና ጭንቀቴ በረታብኝ። ከቀን ወደ ቀን በህይወቴም በተስፋዬም እየዛልኩ መውረድ ጀመርኩ። 

አንድ ቀን ከሰአት ትምህርት ስላልነበረን ከትምህርት ቤት ተመልሼ ወክ ለማድረግ ወደ መሀል ከተማ ወጣሁ። አደባባይ ላይ ወንጌል የሚሰብኩ ትናንሽ ወጣቶችን አየሁ። ትንሽ ተመለከትኳቸውና ትቼ ሄድኩ ከረጅም ጉዞ በኋላ ድጋሚ ተመልሼ ወደ ቤት ለመመለስ ስመጣ እነዛው ወጣቶች ለሰአታት ቦታ ሳይቀይሩ ተራ በተራ ወንጌል ይሰብኩ ይመሰክሩ ነበር። አንደኛውን ጠጋ ብዬ አዋራሁት አማኝ ስላልመሰልኩት የክፍለሀገር ልጅነቴ ንግግሬ ላይ ስለሚያስታውቅ በትህትና ተሞልቶ ጌታን እንድቀበል ነገረኝ። ውስጤ የማላውቀው መነቃቃት ሲፈጠር ተሰማኝ። ከነርሱ ጋር መተዋወቅና ህብረት ማድረግ እንደምፈልግ ነገርኩት ስልኬን ልስጥህ አለኝ። ስልክ እንደሌለኝ ስነግረው ቅዳሜ 10ሰአት እዚሁ ቦታ እንገናኝና አብረን እንሄዳለን አለኝ። ደስ ብሎኝ ተመለስኩ። ቤት ገብቼ ባልፀልይም ከሰሞኑን ቆይታዬ የተሻለ ደስተኛ ስሜት ውስጥ ሆኜ ተኛሁ።

ቀኑ ደርሶ ከተባባልነው ሰአት ቀደም ብዬ ደረስኩና መጠበቅ ጀመርኩ። በሰአቱ መጥቶ መሄድ ጀመርን መንገዳችን ላይ ስለኔ የተለያየ ጥያቄዎችን እየጠየቀኝ ነበር። ወደ ቤተክርስቲያኑ ደረስን መኖርያ ቤት የነበረች አነስተኛ የጭቃ ቤት ነበረች። ከውስጥ ግን የብዙ ሰዎች የፀሎት ድምፅ ይሰማኝ ነበር። ወደ ውስጥ ስንገባ ያየሁት ወጣት ሁሉ ወንድ ሴት ሳይል እንባ እያወረደ ይፀልይ ፤ ይጮህ ነበር። የእግዚአብሔር መገኘት ቤቱን እንደሞላው ሊካድ በማይችል መልኩ ያስታውቃል። ለፀሎት ስንበረከክ አንዳች የከበደ ነገር ከትከሻዬ የተነሳ ይመስል ቀለለኝ። የእግዚአብሔር ድምፅ እጅጉን ናፈቀኝ። መፅሐፍቅዱስ ማንበብ ውስጤ ተራበ ፤ ከወንድሞቼ እና ከእህቶቼ ጋር ድሮ በማውቀው የእግዚአብሔር መገኘት ለሰአታት ማቆም እስኪያቅተን ቤቱ በሙቀት እስኪታፈን ልባችን እየቀለጠ ፀለይን። ቤቴን አገኘሁት። በእርግጥም የአባቴን ቤት። ነፍስን የሚማርክ አምልኮ ሁለት ወንድሞች አቅርበው አስመልከውን የእግዚአብሔርን ቃል የሚያካፍል ሌላ ወጣት ወደ መድረክ ወጣ። እያንዳንዱን በስም እየጠራ አመስግኖ ስለ " እግዚአብሔር ክብር መገለጥ " ሲያስተምር ነፍስም አልቀረልኝ። ህብረቱን ተዋውቄ በቋሚነት ከነርሱ ጋር እንደምቀጥል እያሰብኩ ወደ ቤቴ ሄድኩ። ከወራት በኋላ የመጀመርያዬን ፀሎት ፀለይኩ። የመፅሐፍቅዱስ ጥናቴን ካቆምኩበት ቀጥዬ የዕለቱን ካጠናቀቅኩ በኋላ አንድ ነገር አሰብኩ። እግዚአብሔር ክብሩን ሊገልጥባቸው የሚያስባቸው ብዙ ልጆች አሉት በጓዳ የሚያዘጋጃቸው ፤ ምናልባት በተመቻቸ የኑሮ ገጠመኝ ውስጥ አሁን ላይ ላይሆኑ ይችላሉ ፤ በቤተሰባቸው በጓደኞቻቸው የበታች ተደርገው የሚቆጠሩ ይሆናሉ እግዚአብሔር ግን በነርሱ ውስጥ ስላለው ንፁህ መሻት ክብሩን በሚገልጥበት ጊዜ ኋላ ከሚቀሩት አይሆኑም። የክብሩ መገለጫ የክብር እቃ ይሆናሉ እንጂ። ትውልዱ አንቀላፍቷል ፤ የወንጌሉ ትርጉም ጠፍቶታል። እግዚአብሔር ግን ትውልዱን ለመቀስቀስ በጓዳ ያሰባቸው ጥቂቶቹ ይበቁታል።

እግዚአብሔር ይመስገን የቀድሞ ረሀቤ ተመልሶልኝ ከምወዳቸው ወንድሞቼ ጋር የጌታን የፀጋ ወንጌል እየሰበኩ ነኝ። በተለያየ የህይወት ገጠመኝ ውስጥ የምትገኙ ወንድሞቼ እህቶቼ ቀድሞ ለእግዚአብሔር ፍቅር የነበራችሁ ፤ እግዚአብሔርን ልጁን ጌታ ኢየሱስን የምትወዱ የምታከብሩ። እናት ዘጠኝ ወር የጠበቀችውን ልጇን ለማየት እንደምትናፍቅ የመውለጃዋ ቀን እንደማይቀር የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል። የክብሩ አካል እንድትሆኑ ንቁ! ትጥቃችሁን አንሱ!

------||--------


#Share

🔳 Life Ex. Show

ON KALTUBE

በቀጣይ ሌላ ታሪክ ይኖረናል።

JOIN KALTUBE

Report Page