Justice

Justice


ከክልል ፍርድ ቤቶች እስከ ፌዴሬሽን ደርሶ ወደ ከፍተኛ የተመለሰው የንብረት ክርክር መጨረሻ ምን ይሆን ?

(ከሪፖረትር ጋዜጣ)

ክርክሩ የተጀመረው ከአሥር ዓመታት በፊት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነበር፡፡

የክርክሩ መነሻ፣ በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ በሚገኘው ጌትእሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሽያጭ ነው፡፡ ድርጅቱ የእነ ጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) አራት ሰዎች ሲሆን፣ ጠቅላላ የቦታው ስፋት 11,305 ካሬ ሜትር ነው፡፡

የዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካው ያረፈው በ3,015 ካሬ ሜትር ላይ ሲሆን፣ ስመ ሀብቱ የተመዘገበው በጌታቸው እሸቴ (ኢንጂነር) ስም ነው፡፡ ቀሪው 8,290 ካሬ ሜትር ደግሞ ጅምር ግንባታ ያለበት ሆኖ፣ ስመ ሀብቱ (ካርታው) የተመዘገበው በጌትእሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ነው፡፡

ፋብሪካውንና ጅምር ግንባታ ያረፈበትን (በሁለት የተለያዩ ስሞች የተመዘገቡ ይዞታዎች) ሁለት ይዞታዎች እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) (አራት ሰዎች) ለእነ ዶ/ር በዕውቀቱ ታደሰ ከአሥር ዓመታት በፊት ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በ22,500,000 ብር ሸጠውላቸዋል፡፡

የሽያጭና የግዥ ውሎች የኢትዮጵያ ፍትሐ ብሔር ሕጎችን ሒደት በጠበቀ ሁኔታ ተፈጽመዋል፡፡ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ፋብሪካውን የገነቡት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ወስደው በመሆኑ፣ ገዥዎች እነ ዶ/ር በዕውቀቱ የግዥ ውሉን ሲፈጽሙ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ከልማት ባንክ ጋር የገቡትን የውል (ብድር) ግዴታም ገብተው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ላይ ያልተከፈለ ሰባት ሚሊዮን ብር ለመክፈል እነ ዶ/ር በዕውቀቱ ተስማምተዋል፡፡

እነ ዶ/ር በዕውቀቱ ለእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ሁለት ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያና ለባንክ የሚከፍሉትን ሰባት ሚሊዮን ብር አቀናንሰው፣ ቀሪውን 13,500,000 ብር በአራት ዓመታት ለመክፈል ተስማምተው፣ በሕግ ውልና በምስክሮች ፊት መፈራረማቸውን በዝርዝር መጻፌ ይታወሳል፡፡ ዶ/ር በዕውቀቱ በገቡት ውል መሠረት በመጀመርያው ዓመት 3,375,000 ብር ለመክፈል፣ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) የይዞታውን (የፋብሪካውንና ጅምር ግንባታ ያለበትን ቦታ) ስም፣ በገዥ ስም እንዲያዘዋውሩና እንዲያስረክቧቸው ሲጠይቋቸው፣ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር)፣ ‹‹በስሜ ጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) በሚለው ስም ያለው ቦታ (3,015 ካሬ ሜትር) አይመለከትህም፡፡ የገዛኸው በ8,290 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውን ጌትሽን ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን ነው፤›› ይሏቸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በሻጭና በገዥ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት፣ በክልሉ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተመሠረቱት ክሶችና የይግባኝ አቤቱታዎች ለገዥ (ዶ/ር) በዕውቀቱ ቢወሰንም፣ ሻጭ ክርክሩን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመውሰዳቸው፣ የክልል ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሊሻር ችሏል፡፡

በውሳኔው የተበሳጩት ገዥ እነ ዶ/ር በዕውቀቱ በሥር ፍርድ ቤት (የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት) ‹‹መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ተፈጽሟልና ሊታረም ይገባል›› በማለት ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡

ችሎቱ ግን ‹‹የሥር ፍርድ ቤት የፈጸመው የሕግ ስህተት የለም›› ብሎ ውሳኔውን በማፅደቁ፣ ዶ/ር በዕውቀቱ በውሳኔው ተበሳጭተው ዳኞችን በመሳደባቸው ችሎት በመድፈር ወንጀል ከእነ ቤተሰቦቻቸው ስድስት ወራት ተፈርዶባቸው ለእስር ተዳርገዋል፡፡

ዶ/ር በዕውቀቱ ለእስር ቢዳረጉም፣ በጠበቃ አማካይነት ጉዳዩን ወደ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ ወስደውት ነበር፡፡

አጣሪ ጉባዔው የቀረበለትን አቤቱታ ተመልቶ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናቱ፣ እነ ዶ/ር በዕውቀቱ የመጨረሻ ‹‹የፍትሕ ያለህ!›› አቤቱታቸውን ያቀረቡት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ይመለከታቸዋል ላሏቸው ባለሥልጣናት ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሒደት ሲከናወን የክርክር ጊዜው አራት ዓመታትን ፈጅቶ 2009 ዓ.ም. ላይ ደርሶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቶቹም ሆኑ ባለሥልጣናቱ በሻጭና በገዥ መካከል የተፈጸመውን የውል ሕግ እያዩ እንደየሥልጣቸው ደረጃ ውሳኔ ሰጥተው በመጨረሳቸው፣ የመጨረሻውን ውሳኔ ለሚያስፈጽመው ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ትዕዛዝ በመድረሱ፣ አፈጻጸሙ ደግሞ በተዋረድ ፋብሪካው ለሚገኝበት ክልል ለኦሮሚያ ቢሾፍቱ ከተማ መሬት አስተዳደር፣ ለሕግ ባለመብቶች ፈጽሞ ሪፖርት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተላልፎ ነበር፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ፍርድ ቤቶች (የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔና (ሰበር ችሎት ያፀደቀው ውሳኔ) ውሳኔ የሰጡት፣ ዶ/ር በዕውቀቱ የገዙት ቦታ ጌትእሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካ ያረፈበትን 8,290 ካሬ ሜትር በመሆኑ፣ በጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) ስም የተመዘገበው 3,015 ካሬ ሜትር፣ ለእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) እንዲሰጥ ነበር፡፡

ነገር ግን ፍርድ ቤቶቹ የሰጡ ውሳኔ የተደራረበ (Over Lap) በመሆኑና ስመ ሀብቱ የተመዘገበው ወይም ማለትም ፋብሪካው የተገነባው በ3,015 ካሬ ሜትር ላይ በመሆኑ፣ የቢሾፍቱ ከተማ መሬት አስተዳደር ሊያስፈጽም አልቻለም፡፡

የቢሾፍቱ መሬት አስተዳዳሪና አጠቀቀም ጽሕፈት ቤት ችግሩን ዘርዝሮ እንደ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስረከብ እንደማይቻል በመግለጽ ለፌዴራል ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የፍርድ ባለመብቶች እነ ጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ፣ ምንም እንኳን ክርክራቸው እስከ ሰበር ደርሶ ለእነሱ የተወሰነላቸው ቢሆንም፣ ውሳኔው ሊፈጸምላቸው እንዳቻለ በማብራራት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም አቤቱታውን መርምሮ ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ብይንና ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፍርድ ባለመብቶቹ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ ካርታውን አደራርቦ (Over Lap) ያዘጋጀው የቢሾፍቱ ከተማ መሬት አስተዳደር መሆኑንና ለማስተካልም ፈቃደኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ አብራርቶና ግልጽ አድርጎ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡፡

ነገር ግን እነ ዶ/ር በዕውቀቱ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምላሽ፣ የፍርድ ባለመብቶቹ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) የቢሾፍቱ መሬት አስተዳደር፣ ፍርድ ቤቱ ካዘዘው የይዞታ ማረጋገጫውን (ካርታውን) ለማስተካል ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸው ያቀረቡት አቤቱታ ሐሰት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ርክክብ የሚፈጸመው በተሰጠው ፍርድ ልክ ብቻ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ፍርድ የተሰጣቸው ባለመብቶች 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲረከቡ እንጂ፣ ተስተካክሎ ወይም ትርፍ ቦታ እንዲረከቡ የበላይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ አለመስጠታቸውን በመግለጽም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳረፈባቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ከባንክ ብድር ተወስዶባቸው፣ በማስያዣነት በባንኩ የሚገኙ ሆነው ሳለ፣ ለማስቀየር የሚደረገው ክርክር የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑንም ጠቁመው ተከራክረዋል፡፡ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ሁለቱንም ካርታ አስይዘው የተበደሩና እነ ዶ/ር በዕውቀቱም ግዥ ሲፈጽሙ ሁለቱንም ካርታ ወደ እነሱ ለማዘዋወር በፈጸሙት ውል መሠረት፣ የብድር ኃላፊነቱንም በመውሰድ ከባንኩ ጋር ውል መፈረማቸውንም አብራርተዋል፡፡

በውላቸውም ላይ አጠቃላይ የይዞታው ስፋት 11,305 ካሬ ሜትር መሆኑን፣ በግዥ ውሉ ላይ መሥፈሩንም አክለዋል፡፡ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች ሰፋ ያለ ክርክር ካደረጉ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱም ክርክሩን መርምሮ አከራካሪ ናቸው ያላቸውን ጭብጦች ለይቷል፡፡

የያዘው ጭብጥም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ፣ ጌትእሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካ ያረፈበትን 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ለእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) እንዲሰጥ የወሰነው ውሳኔ እንዳይፈጸም የሚያደርግ ነው? ወይስ አይደለም?፣ የይዞታዎቹ መደራረብ ፍርዱን ከመፈጸም የሚያግድ አይሆንም የሚባል ከሆነ፣ አፈጻጸሙ በምን መልኩ ይሁን?፣ የፋብሪካውን የሽያጭ ውል አስመልክቶ ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. የተደረገው ውልና ይህንን ተከትሎ ታኅሳስ 16 ቀን 2005 ዓ.ም. የተያዘው ቃለ ጉባዔ ‹‹በሕግ ፊት የፀና ወይም ፉርሽ ሊሆን አይገባም›› ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ አፈጻጸም ሊጠየቅበት የሚችል ነው ወይስ አይደለም? የሚሉ ጭብጦችን ይዞ አንድ በአንድ እየዘረዘረ አግባብ ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ ዕልባት ሰጥቷቸዋል፡፡

የካርታዎቹን መደራረብ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በጥልቀት መርምሮና ከክልሉ ጭምር ማስረጃዎች አስቀርቦ እንዳረጋገጠው፣ 3,015 ካሬ ሜትር ለባለመብቶች ማስረከብ እንዳልተቻለ (በአፈጻጸም) መገንዘቡን አብራርቶ፣ የተሰጠው ፍርድ እንዳይፈጸም የሚያግድ ነው ብሎ መደምደም ስለማይቻል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ትርጉም የሰጠባቸውን አስገዳጅ ትርጓሜዎችን ጠቅሷል፡፡

በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ በይግባኝ እስካልተሻረ ድረስ ዋጋ አልባ ማድረግ እንደማይቻል (መ/ቁ/38041/2001፣ ፍርዱን ላለመፈጸም ሕጋዊ ምክንያቶች ያሉ ከሆነ (መ/ቁ/59301/2003)፣ ውሳኔው ሕጋዊ ባልሆነና ውጤት አልባ በሚያደርግ መልኩ ውድቅ ሊደረግ የሚችልበት አግባብ የለም (መ/ቁ/85746/2006) በሚሉት ምክንያቶች የፍርድ ባለዕዳዎች ያቀረቡት የመከላከያ ሐሳብ የሕግም ሆነ የፍሬ ነገር ድጋፍ የለውም ብሏል፡፡

የሰበር ችሎት በሰጠው ፍርድና የቢሾፍቱ ከተማ መሬት አስተዳደር በሰጠው የማስማሚያ ሐሳብ መሠረት፣ እነ ዶ/ር በዕውቀቱ የጌትእሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈፈያ ፋብሪካ ካረፈበት ቦታ ውጪ ያለውን ትርፍ ቦታ እንዲያስረክብ ለፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፋብሪካውን የሽያጭ ውልና ማሻሻያውን በሚመለከት እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ያቀረቡን አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የፌዴራል ፍርድ አፈጸጸም ዳይሬክቶሬት አስፈጽሞ እንዲያሳውቅ ቢታዘዝም፣ ውሳኔውን ማስፈጸም አልቻለም፡፡

በመሆኑም የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ለእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) የወሰነው 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ጌትእሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈያ ፋብሪካን ያጠቃልላል ወይስ አያጠቃልልም? በሚለው ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡

ነገር ግን የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ አፈጸጸሙን የሚመራው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑን ጠቁሞ፣ ቀደም ብሎ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የተሰጡትን ውሳኔዎች ይዘት፣ ከግራ ቀኙ ክርክር ጋር አገናዝቦ በመመርመር በራሱ ተገቢውን አቋም ይዞ ውሳኔ እንዲሰጥ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ማብራሪያ ሊሰጥ የሚያስችለው ሥነ ሥርዓታዊ አግባብ እንደሌለው በመግለጽ፣ መዝገቡን ዘግቶ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መልሶለታል፡፡ አሥር ዓመታት የፈጀው የፍትሐ ብሔር ክርክርም ‹‹የመጨረሻ ዕልባት ያገኛል?›› ወይስ ‹‹አያገኝም?›› የሚለው መጨረሻ የሚጓጓ ሆኗል፡፡      

(ይህ ፅሁፍ በሪፖርተር አሳያዬ ቀፀላ የተዘጋጀና ጥቂት የቃላት ማስተከከያ (ከዋናው አውድ ሳይወጣ የተደረገበት ነው ፤ ይህ ጉዳይ ይታይልን ብለው የላኩት ደግሞ ፍትህ አጣን ያሉ ቤተሰቦች ናቸው)

@tikvahethiopia

Report Page