ISON Xprience

ISON Xprience


የሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል ሰራተኞች ጥያቄ ምንድነው ? ሳፋሪኮምስ ምን ይላል ?

ከትላንት ጀምሮ የሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል ሰራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ላይ መሆናቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከቤተሰቦቹ የደረሰው መረጃ ያሳያል። ሰራተኞቹ የሥራ አድማውን ያደረጉት መስሪያ ቤታችን ቅሬታችንን ሊመልስልን አልቻለም በሚል መሆኑን ገልጸዋል።

ሰራተኞቹ ካቀረቡት ጥያቄዎች ዋነኛው "ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የጥሪ ማዕከል ሰራተኞቹን በራሱ ሥር ያካተን በኤጀንት ለምን ያሰራናል" የሚል ነው።

ቲክቫህ ከቤተሰቦቹ እንደተረዳው የሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል ሰራተኞች በቀጥታ የተቀጠሩት በሳፋሪኮም ሳይሆን ISON Xprience በተባለ ድርጅት አማካኝነት ነው። ድርጅቱ ለሳፋሪኮም በሚሰጠው አገልግሎት በስሩ ከ500 በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን 5 የሥራ ክፍሎችንም ያካትታል።

ከሰራተኞቹ ጋር ውል የገባው ISON Xprience ሲሆን የተመለከትናቸው የሥራ ውሎች ሥራው ኮንትራት (Project Based Contract ) የ2 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው። ይህም ሰራተኞቹ የሳፋሪኮምን ሥራ በዋነኛነት ይስሩ እንጂ ውላቸው ለISON Xprience ነው።

ሌላው የሰራተኞቹ መሰረታዊ ጥያቄ የደሞዝ ጉዳይ ሲሆን ሥራውና የሥራው የሚከፈለን የክፍያ መጠን አለመጣጣምና የዘገየ ክፍያ እንደሆነ ይገልጻሉ። የሰራተኞቹ ጥቆማ እንደሚያመለክተው ሳፋሪኮም ለዚህ ሥራ በሰራተኛ ከሚከፍለው 20 በመቶው ብቻ ለሰራተኞቹ እንደሚደርሳቸው ጠቁመዋል።

ሌላው የኢንሹራንስ አለመመቻቸት እንዲሁም በመስሪያ ቤቱ በሚገኘው ካፍቴሪያ ያለው የምግብ ውድነት የተጠቀሰ ሲሆን ሰራተኞቹ እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ድርጅቱ በቂ መልስ እንዳልሰጣቸው በመግለጽ ለሦስት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

የ ISON Xprience የሥራ አመራሮች ህዳር 1 ቀን ከሰራተኛ ተወካዮች ጋር ስብሰባ አካሂዶ ነበር። ከስብሰባው በኋላ በወጣ "ቃለጉባኤ" ድርጅቱ ኤጀንሲ አለመሆኑንና የጥሪ ማዕከል ሥራዎችን ለመስጠት የተቋቋመ መሆኑን ገልጿል። ኢንሹራንስንም በተመለከተ ከሕዳር 22 ጀምሮ የጤና ኢንሹራንስ ለመጀመር ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቋል።

ክፍያንም በተመለከተም "በኢትዮጵያ ህግ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን ስለሌለ ደመወዝ በድርድር ወይም በድርጅቱ የደመወዝ ስኬል የሚወሰን ነው። ድርጅቱ በኦገስት 2022 የ30% የደመወዝ ማስተካከያ አድርጓል።" ሲል ገልጿል።



ይህንን በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የቤተሰብ አባላቱን ቅሬታ በተመለከተ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጹሑፍ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን "የጥሪ ማዕከላችንን በሚያስተዳድርልን ድርጅት (ISON Xprience) እና በሰራተኛው መካከል አለመግባባቶች እንዳሉ ተረድተናል። በደርጅቱ ሥራ አስፈጻሚዎችና ሰራተኞች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተፈትቶ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴዎች እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን" የሚል ምላሽ አግኝቷል።

ሳፋሪኮም በዚህ ወቅት ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት እንደከዚህ ቀደሙ በተለመደ መልኩ እንደቀጠለ ገልጾ በጉዳዩ ላይ ማንኛውም ለውጥ የሚኖር ከሆነ ለደምበኞቹ እንደሚያሳውቅ ገልጾልናል።

(ከቲክቫህ ቤተሰቦች)

@tikvahethiopia

Report Page