IMF

IMF


#IMF

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ፥ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ዝግ እንደሚያደርገው አሳውቋል።

IMF ፤ የዓለም ምጣኔ ሀብት እ.አ.አ. ባለፈው 2021 በ6.1 ከመቶ ማደጉን አስታውሶ ዘንድሮ ግን ዕድገት የሚኖረው በ3.6 ከመቶ ብቻ እንደሚሆን ተንብዩዋል።

" ጦርነቱ በምጣኔ ሀብት ላይ ያሳደረው አንድምታ ራቅ እያለም አድማሱንም እያሰፋ ነው " ሲል ገልጿል።

IMF የውጭ ንግድ የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል እንዲሁም የነዳጅ እና የምግብ ዋጋ ንረት በማስከተል የዓለም ኢኮኖሚ ወደ አሉታዊ አቅጣጫ እንዲያመራ አድርጓል ሲል አመልክቷል።

ዋናው የIMF ኢኮኖሚስት ፒየር ኦልቪዬ ጉሪንቻስ በጻፉት የዓለም ኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርቱ መግቢያ ፦

" በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ምክንያት ተንኮታኩቶ የነበረው የዓለም ኢኮኖሚ ጠንከር ብሎ ሊያንሰራራ ተቃርቦ ነበር።

ጦርነቱ መጣና በቅርብ ጊዚያት የተገኙ አብዛኞቹን ስኬቶች ጠራርጎ የሚያጠፋ ሁኔታ ፈጠረ።" ሲሉ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ፤ IMF ከዚህ ቀደም ለዓለም አገራት በሰራው ትንበያ የገደፈውን የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት የተመለከቱ መረጃዎች በትላንት ሪፖርቱ አካቷል።

እኤአ 2022 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት 3.8 በመቶ ያድጋል ሲል ተንብዩዋል። በ2023 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ 5.7 በመቶ ያድጋልም ብሏል።

IMF ከዚህ ቀደም ለዓለም አገራት በሰራው ትንበያ "ባልተለመደ ከፍተኛ የእርግጠኝነት መጥፋት" ምክንያት የገደፋቸውን የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት የተመለከቱ መረጃዎች በትላንት ሪፖርቱ አካቷል።

በሸማቾች የዋጋ ግሽበት መለኪያ (Consumer Prices) ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ 26 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው የሸቀጦች ዋጋ ንረት በተያዘው ዓመት ወደ 34 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚደርስ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል። ይኸ እኤአ 2023 በአንጻሩ 30 ነጥብ 5 በመቶ ይሆናል።

ባለፈው አመት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 3 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የውጭ ንግድ ሚዛን ጉድለት (Current Account Balance) በጎርጎሮሳዊው 2022 በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ መሠረት ወደ 4 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ይላል። በሚቀጥለው ዓመት ወደ 4 ነጥብ 4 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል የተቋሙ ትንበያ ይጠቁማል። 

IMF ትንበያ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2022 ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ምጣኔ ሐብት በ3 ነጥብ 8 በመቶ ያድጋል። ይኸ ዕድገት በሚቀጥለው ዓመት ጥቂት ጭማሪ አሳይቶ ወደ 4 በመቶ ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል።

የIMF ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሰሐራ በርሐ በታች ከሚገኙ 35 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት 20 ገደማዎቹ በዕዳ ጫና ውስጥ የገቡ አሊያም የመግባት ሥጋት የተጫናቸው ናቸው።

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት በቀጠናው በሚገኙ አገራት ከሚያሳድረው ጫና መካከል ይኸው ተጨማሪ ፋይናንስ የሚፈልጉ ግን ዕዳ ያጎበጣቸው አገራትን ሁኔታ እንደሚገኝበት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኤኮኖሚ አማካሪ እና የጥናት እና ምርምር ክፍል ኃላፊ ፒየር ኦሊቪዬ ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካሳደረባቸው ዳፋ በማገገም ላይ ሳሉ የተቀሰቀሰው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ብርቱ ጫና አሳድሮባቸዋል።

በተለይ የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመር ደሐ ቤተሰቦች ላይ የሚያሳድረው በትር የIMF አማካሪ የጠቀሱት ብርቱ ፈተና ነው። ፒየር ኦሊቪዬ "ነዳጅ እና ኃይል የሚሸምቱ አገሮች የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑ እንጠብቃለን።

ከፍ ያለ ዕዳ ያለባቸው አገሮች ወይም ለዕድገት ከፍ ያለ ፋይናንስ የሚፈልጉት እና ሕዝባቸውን ለመደገፍ በቂ አቅም የሌላቸው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። እነዚህ አገሮች የውጪ ድጋፍ ወይም የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ይፈልጉ ይሆናል" ብለዋል።

የጦርነቱ ዳፋ ከሰሐራ በርሐ በታች ወደሚገኙ አገራት በዋናነት የተዛመተው በምግብ እና በነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ በኩል አድርጎ ነው።

እንደ ተቀረው ዓለም ስንዴ ዋንኛ የገበታ ምግብ ባይሆንም በአፍሪካውያን ፍጆታ ከፍ ያለ ቦታ አለው።

የIMF ሰነድ የምግብ ዋጋ መናር የሸማቾችን የመግዛት አቅም እና ፍላጎት በመጪዎቹ ጊዜያት እንደሚፈታተን አስጠንቅቋል። ይኸ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ፖለቲካዊ ቀውስ የመቀስቀስ ዕድል አለው። የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ እንደ ናይጄሪያ ላሉ አምራች አገራት የዕድገት ተስፋን ከፍ አድርጓል።

መረጃው ከቪኦኤ እና ከዶቼ ቨለ የተውጣጣ ነው።

@tikvahethiopia


Report Page