IBD & Sports

IBD & Sports

Crohn's & Colitis Ethiopia

የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የአንጀት ቁስለት


የሰውነት እንቅስቃሴ የእለት ተዕለት ኑሮዋችን አካል የሆነና የሰውነታችንን አጠቃላይ ጤናን ለመጠበቅ የሚረዳን ነው፡፡


ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ በአንጀት ቁስለት ታካሚዎች የጤና ሁኔታ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዳለው ነው፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል፡-


- በርከት ያሉ ጥናቶችና የጤና ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ለአንጀት ቁስለት ህመም ማገርሸት የጭንቀትና ድባቴ መጠን መጨመር እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡ እንደ ዮጋ ያሉ የሰውነት እንቅስቃሴን ማድረግ ደግሞ የአእምሮንና የሰውነት አካልን ትስስርና ተግባቦት በማጠናከር የጭንቀት መጠንን ለመቀነስ ይረዳል፡፡


- ረዘም ላለ ጊዜ የስቴሮይድ መድሃኒቶችን በሚወስዱ የአንጀት ቁስለት ታካሚዎች ዘንድ የአጥንት እፍጋት መጠን መቀነስና የአጥንት መሳሳት አይነት ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህም ደግሞ የሰውነት ማጎልመሻና የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎች የአጥንት የጥንካሬን መጠን ለመጠበቅ ይረዳሉ፡፡


- መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ የሰውነት ብግነት መጠንንም ለመቀነስ ይረዳል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት የሰውነት እንቅስቃሴ ስናደርግ በአፅመ- አጥንታችን(skeletal muscle) ወደ ሰውነታችን የሚለቀቁ ‘Myokines’ የሚባሉ የፕሮቲን አይነቶች የሰውነት ብግነትን የመቀነስ ባህሪ ስላላቸው ነው፡፡


በርከት ያሉ የአንጀት ቁስለት ህመም ታካሚዎች ፤ የአንጀት ቁስለት ካጋጠማቸው በሗላ የህመሙን መልሶ መቀስቀስ በመስጋትና በሰውነታቸው ላይ በሚሰማቸው አለመመቸት ምክንያት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንደቀነሱ ይገልፃሉ፡፡ሆኖም በህመሙ የማገገም ደረጃ ላይ እነዚህ ስሜቶች ስለሚስተካከሉ በተቻለ መጠን የሰውነት እንቅስቃሴን በቋሚነት መቀጠል ይመከራል፡፡

ጠንከር ያሉና ብዙ ጉልበትን የሚጠይቁ በተለይም የሆድ እቃን እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚፈልጉ እንደ ሲት-አፕና መተጣጠፍ የሚበዛባቸው እንቅስቃሴዎች በሆድ እቃ ላይ የተወሰነ ህመም ሊያስከትሉ ስለሚችሉ፤ ቀለል ያሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣ ሃኪሞትን ስለ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ማማከር እንዲሁም የሰውነታችንን ለዉጥና ምላሽ ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡

Report Page