IBD & Menses Part 1
Crohn's & Colitis Ethiopia By Yeabsira Taye
የወር አበባ ዑደትና የአንጀት ቁስለት
የወር አበባ ምንድነው?
የወር አበባ ዑደት የአንዲት ሴት ሰውነት በየወሩ ሊከሰት ለሚችል እርግዝና በሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት የተነሳ የሚፈጠሩ የተለያዩ ለውጦች ውጤት ነው፡፡ በየወሩ ኦቫሪ (የእንቁላል አቃፊ) ከተባለው የሰውነት ክፍል ኦቩሌሽን (ውደት) በተባለ ስርዓት አንድ እንቁላል ይወጣል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የተለያዩ የሆርሞን ለውጦች ማህጸንን ለእርግዝና ያዘጋጁታል፡፡ እርግዝና ሳይከሰት ከቀረ ግን ይህ የተደረገ ዝግጅት ፈርሶ በወር አበባ መልኩ ከሰውነት ይወገድና ለሚቀጥለው ዑደት ዝግጅት ይጀመራል፡፡ የወር አበባ ኡደት የሚባለው አንድ የወር አበባ ከመጣበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ እስከሚቀጥለው ዙር የወር አበባ የመጀመሪያ ቀን ነው፡፡ የአንድ ኡደት ርዝማኔ ከ21 እስከ 35 ቀን ሊወስድ ይችላል፡፡
የወር አበባ ዑደትና የአንጀት ቁስለት ህመም ግንኙነት
በአንጀት ቁስለት ህመም ወቅት የወር አበባ ዑደት እንደህመሙ ደረጃና እንደ ሰው የሰውነት ሁኔታ ይለያያል፡፡ አንዳንድ ሴቶች መደበኛውና ከወትሮው ባልተለየ ጤናማ ዑደት ውስጥ ሲያልፉ አንዳንድ ሴቶች ፣በተለይም በህመሙ ንቁ ደረጃ ላይ የወር አበባ ዑደት መዛባት እንዲሁም ለተወሰነ ወራት ሳይመጣ መቅረት ያጋጥማቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ የህመሙ ንቁ ደረጃ ላይ የወር አበባ ሲመጣ ከፍተኛ ህመም፣ ቁርጠትና በመጠን የበዛ ወይም ያነሰ ደም ሊከሰት ይችላል፡፡ የአንጀት ቁስለት ህመሙ ስሜትም በተወሰነ መልኩ ጠንከር ብሎና ተባብሶ ሊከሰት ይችላል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ጠንከር ያለ የስሜት መለዋወጥ፣ ድባቴ፣ግልፍተኛነትና ብስጭት ሊኖር ይችላል፡፡
ለዚህ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ፡-
1. በአንጀት ቁስለት ንቁ ደረጃ ላይ የሚከሰተው የሰውነት መቆጣት ፤የሰውነታችን መደበኛ የሆርሞን ስራ እንዲዛባ ምክንያት ስለሚሆን የወር አበባ ዑደትም በዚሁ ምክንያት ሊዛባ ይችላል፡፡
2. ጥናቶች፣ በወር አበባ ወቅት በሰውነታችን ውስጥ ያለው የኤስትሮጅን መጠን ለውጥ ስለሚኖረው፤ ይህ ደግሞ በሆድ እቃ ምግብን የማጓጓዝ ተግባር ላይና በሆድ እቃ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የመምጠጥ ሚና ላይ አስተዋፆ እንዳለው ይገልፃሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሆድ እቃን ህመምና ተቅማጥን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የአንጀት ቁስለት ህመም ደግሞ በአብዛኛው የሆድ እቃን እንደማጥቃቱ፤ ከሌሎች ሰዎች በተለየ የአንጀት ቁስለት ያጋጠማቸው ሴቶች ጠንከር ያለ የወር አበባ ህመም ሊያስተናግዱ ይችላሉ፡፡
3. በወር አበባ ወቅት ኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን የሚባሉ ሁለት ሆርሞኖች ላይ ለውጥ ይካሄዳል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአንጎላችን ውስጥ የሚገኘው ሴሮቶኒን የተባለው የሰውነታችንን የስሜት መለዋወጥ የሚቆጣጠረው ሆርሞንም ላይ ለውጥ ይከሰታል፡፡ ለዚህም ነው በወር አበባ ወቅት የስሜት መቀያየሮችና ድባቴ የሚስተዋለው፡፡
4. በተጨማሪም ቀደም ሲል የተደረጉ ቀዶ ህክምናዎች፣ የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶችና ሲጋራን ማጨስም እንደምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡