ህልውና

ህልውና

https://t.me/adey_y1


ፀሃፊ :- አደይ


ልብሴን ለብሼ ጨርሼ መስታወት ፊት ቆሜ የጆሮ ጌጥ እያደረኩ ስልኬ የመልዕክት ድምፅ አሰማ። ጌጡን ጆሮዬ ላይ አድርጌ ሄጄ ከአልጋው ላይ አነሳሁት። አሮን ነው። እሱ መሆኑን ሳይ በደመነፍስ ፈገግ አልኩ "አየመጣሁ ነው። ሀያ ደቂቃ።" ይላል መልዕክቱ። ስልኩን መልሼ አልጋው ላይ አስቀምጬ ከክፍሌ ወጣሁ።

እቴቴ መኝታ ቤት ስገባ እቴቴ መስኮት ፊት ለፊት ቆማለች። ልብሷን ለብሳ ዘንጣለች። ተዘጋጅተሽ ጨርሺ ልላት ነበር አመጣጤ።

(ከሁለት ሰአት በኌላ የሚጀምር የፋሽን ሾው ፕሮግራም አለብን። ሾዉ ላይ በራሳችን ልብስ እንሳተፋለን። ከጠዋት ጀምረን ለዝግጅቱ ስንሯሯጥ ነው የቆየነው። አሮን የሚመጣው ከዚያ ነው። ከሰአት በፊት ትንሽ ለማረፍና ልብስ ለመቀየር አሮንንና ቤዛን እዚያው ትቼያቸው ነበር የመጣሁት።)

ከአጠገቧ ሄጄ ቆምኩኝ። በመስኮቱ ወደ ውጪ ታያለች። ከመስኮቱ በስቲያ የግቢው ጔሮ አለ። ጔሮው መሃል ግንቡን ተጠግቶ ያደገ ትልቅ የካዝሚር ዛፍ አለ። ካዛፉና ከግንቡ ውጪ ብዙም ሚታይ የለም። 

እንደእሷ በመስኮቱ ውጪውን እያየሁ ጥቂት በዝምታ ቆየን

"የእማማን ደስታ የካዝሚር ዛፍ ታስታውሻለሽ?" አለችኝ

ፈገግ ብዬ ራሴን ነቀነኩ። እንዴት እረሳዋለሁ?

"ግቢው ውስጥ ብዙ የፍራፍሬ ዛፎች ነበሩ። ለምን የካዝሚሩን ዛፍ ላይተሽ እንደምትወጂ ይገርመኝ ነበር። አማማ ደስታ የህሊና ዛፍ ይሉት ነበር።" 

ፈገግ ብለን ተያየን።

እማማ ደስታ ጎረቤታችን ነበሩ። ቤታቸው ከመኖሪያ ግቢያችን ሁለት ግቢ ቀጥሎ የሚገኝ ሰፊ ግቢ ነው። ግቢያቸው በስፋቱ ልክ በተለያየ ዛፎች የተሞላ በመሆኑ ከሰፈሩ መኖሪያ ግቢዎች ነጠል ብሎ ይታያል። ግቢው መሃል የቆመ ትልቅ ያማረ ቤት አላቸው። ህሊና ብለው ነበር የሚጠሩኝ። እቴቴን ይወዷት ነበር። ሰፈር ውስጥ ቡና ለመጠጣት እሳቸው ጋር ብቻ ነበር የምትሄደው። በሳምንት ሶስቴ አራቴ ቡና ይጠሯት ነበር። የቤታቸው ሰራተኛ ቡና ልትጠራት ስትመጣ "ህሊናንም ይዘሻት ነይ ብለውሻል" ትላለች። ተከትያት እሄዳለሁ። ግቢያቸው መሄድ ደስ ይለኝ ነበር። እነሱ በረንዳ ላይ ተሰብስበው ቡና ሲጠጡ እኔ ግቢውን ከዳር እስከዳር አዳርሰዋለሁ። ዛፍ ላይ እንጠላጠላለሁ። እንደልጅ ሚያደርገኝ እዚህ ግቢ ስመጣ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ታዲያ በማይገባኝ መንገድ ከዚያ ሁሉ ዛፍ የካዝሚሩ ዛፍ ደስ ይለኛል። ጉዳዬ ከዛፍነቱ ጋር አይመስለኝም። ዛፍነቱ ላይ የተለየ ነገር አይታየኝም። ለመጀመሪያ ጊዜ እማማ ደስታ እቤታቸው ሄጄ ያጠቡትን ካዝሚር በጎድጔዳ ሳህን ውስጥ አድርገው ሰጥተውኝ ስሙን ሲነግሩኝ ልዩ ነገር ሆኖብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። 'ካዝሚር' ስሙን ወደድኩት። ከዚያ ፍሬው ስበላው ልጅነት ልጅነት አለኝ። ይሄ ግር የሚለኝ ነገር ነው። ልጅ ነበርኩ። ግን ስበላው የተሰማኝ እንደዚያ ነበር። አሁንም ስበላ ማስታውሰው ልጅነቴን ነው። እማማ ደስታ ግቢ ምትሮጠውን ልጅ።

'ልጅነት ምን ምን ይላል?' ምንአልባት ካዝሚር ካዝሚር።

"አድገሽ እንደድሮው ቤታቸው መሄድ ካቆምሽ በኋላ እንኳን በአባተ አስወርደው ይልኩልሽ ነበር። ታስታውሺያለሽ.. አንድ ጊዜ ለእረፍት ከናዝሬት ስትመጪ በትልቅ ፌስታል ሞልተው ላኩልሽ። ስትሄጂ የላኩልሽን ሁሉ በሻንጣሽ ይዘሽው ሄድሽ። " ፈገግ አለች

አልረሳውም እናቴ።

የላኩልኝን ሁሉ ይዤ ሄጄ እንድታበስለው ለኢዛና እናት ሰጠኋት። ሶስተኛው ቀን ላይ ከኢዛና ጋር የቤታቸው በረንዳ ላይ ተቀምጠን ካዝሚሩን እየበላን ብዙ የልጅነቴን ትዝታዎች አወራሁት። የልጅነቴ አካል ያደረኩት ያህል ተሰምቶኝ ነበር። "ልጅ ሆነሽ ባውቅሽ ኖሮ" አለኝ.. ብዙ ጊዜ እንደዚህ ይላል። ወደፊት የሚኖረኝ ግቢ የካዝሚር ዛፍ እንዲኖረኝ እንደምፈልግ ስነግረው "ለምን እዚህ አንተክልም?" ብሎ እጄን ይዞኝ ተነሳ። ጔሮ ገብተን ሶስት ቦታ አራርቀን ፍሬውን ቀበርን።

"ባባን አይተሽዋል?" አለች

"እማዬ መኝታ ቤት ነው መሰለኝ" 

"እስኪ ልየው። ልንወጣ ነው አይደል?"

"አው አሮን እየመጣ ነው"

ዞራ ሄደች።

መስኮቱ ፊት እንደቆምኩ የካዝሚሩን ዛፍ እያየሁ ተከዝኩ። ብዙ ብዙ ነገር አስታወስኩ። 

'እማማ ደስታ እንዴት ሆነው ይሆን?' ካየኌቸው ብዙ አመት ሆኖኛል። ከዚያ ሰፈር ከወጣሁ በኋላ አይቻቸው አላውቅም። እቴቴም በቅርብ መሄዷን አላስታውስም። የተከልነው የካዝሚር ፍሬ ፀድቆ ይሆን? መሊ እንዴት ሆና ይሆን? (መሊ የኢዛና እናት ነች። መልህቅን ሲያቆላምጡት መሊ ይሏታል።)

 የካዝሚሩ ዛፍ ብዙ አፍርቷል። መውረድ አልነበረበትም? ለምን ችላ እንዳልኩት አላውቅም። ጥቂት አሰብኩና ወደ ጔሮ የሚወስደውን በር ከፍቼ ወጣሁ። ዛፉ ጋር ደርሼ ሽቅብ ሳየው ቆይቼ ግንቡ ግማሽ የሚደርሰው ውሃ ልኩ ላይ ከተቀመጥኩ በኋላ ሁለቱን እግሬን በየተራ አውጥቼያቸው ውሃ ልኩ ላይ ቆምኩ። ራሴ የግንቡ ጫፍ ላይ ደረሰ። ከቆምኩበት ሆኜ ዙሪያ ገባዬን ቃኘሁና ቅርንጫፉን እየጎተትኩ መቁረጥ ከጀመርኩ በኋላ ፌስታል አለመያዜን አስታወስኩ። ተመልሼ ወርጄ ወደ ውስጥ ገብቼ ከእቴቴ መኝታ ቤት ፈልጌ ይዤ ወጣሁ።

በድጋሜ ውሃ ልኩ ላይ ወጥቼ ቅርንጫፎቹን እየሳብኩ ፍሬውን እየቀጠፍኩ ፌስታሉ ውስጥ መክተት ስጀምር የምሰራው ነገር ለራሴ አሳቀኝ። ከሰአታት በኋላ ትልቅ ዝግጅት አለብኝ። የለብሰኩት ልብስ ለዚህ ቀን ብዬ ያዘጋጀሁት ነው። ውሃልኩላይ ለመውጣት ስሞክር የግንቡን አዋራ ጠርጔል። ስጨርስ ሌላ ልብስ መፈለግ አለብኝ። ግን ግድ አልሰጠኝም። ማቆም አልፈለኩም። 

ከሆነ ያህል ደቂቃዎች በኌላ

"እገዛ ትፈልጊያለሽ?" የሚል ድምፅ ስሰማ ወደ ጎን ዞርኩኝ።

አሮን የበሩ መቃን ላይ ደገፍ ብሌ ያየኛል። ሳየው ፈገግ አልኩኝ። 

ፈገግ ብሎ የሸሚዙን እጀታ እየፈታ መጣ። ዝም ብዬ አየሁት። 'ምንድነው የምትሰሪው? ለዚህ ጊዜው ነው?' ምናምን አላለኝም። የሸሚዙን እጀታ ጠቅልሎ በቀላሉ ዛፉ ላይ ተንጠላጠለ። እኔም 'የግድ አሁን ማድረግ ያለብን እንደሆነ ሁሉ 'ሌላ ቀን መሆን ይችላል .. ሰአት ረፍዶብናል' ምናምን አላልኩም። የያዝኩትን ፌስታል ተቀብሎኝ አንዱ ቅርንጫፍ ላይ አንጠለጠለው።

ግንቡን እንደተደገፍኩ ዝም ብዬ አየው ጀመር።

አያሳሳም? ማን እንደዚህ ይሆናል? ማን ክብሬ ምኔ ሳይል አብሮ እንደልጅ ለመሆን ይፈቅዳል? ደግሞ ልቤ ትዘላለች። በአየሁት ቁጥር ... አብሮኝ እየዋለ... ልቤ እንደዚህ መሆን አትተውም። የሆነ አይነት ለውጥ ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል። የመርሳት ሂደት ውሰጥ። ትናንትን እየተወኩ ወደፊት መራመድ የጀመርኩ ይመስለኛል...

"ካዝሚር ልጅነቴን ያስታውሰኛል። ግቢ ውስጥ እህቴ በልጅነቷ የተከለችው የካዝሚር ዛፍ አለ። ተንከባክባ ነበር ያሳደገችው። የእሷ ዛፍ ነበር የሚባለው።" አለ

(እኮ... ካዝሚር ልጅነትን ይመስላል...ሃሃ..)

እንዳስተዋልኩት ስልጅነቱን ሲያነሳ እህቱን አብሮ ያነሳታል። ከአወራሩ የነበራቸው ቅርበት የጠበቀ መሆኑ ያስታውቃል። 

ብዙ ብዙ ነገር አወራን።

ስንጨርስ ቀድሞኝ ከዛፉ ወረደና ከፊቴ ቆሞ "ነይ ላውርድሽ" ሊያወርደኝ እጁን ዘሩጋ።

"አረ...ራሴው እወርዳለሁ ቅርብ ነው።" ሳቅኩኝ።

እንደልጅ አቅፎ አወረደኝ።

በጣም እየሳኩ ከፊት ለፊቱ አይኖቹን እያየሁ ቆምኩኝ። 

ትኩር ብሎ አይኖቼን አያቸው። አተኳኮሩ ቀስ በቀስ ሳቄን አስቆመኝ።

"እወድሻለሁ።" አለ በሆነ አይነት አስተያየት እያየኝ።

እያየሁት ዝም አልኩ። ፊቴ ይነዳል። ደግሞ ልቤ። 

(ምን እንደዚህ ያስደርጋል? ስንት ነገር አብረን አልሆንም...? በአፋችን ባንለውም በድርጊታችን አልተባባልንም...?

አይ አይ ይሄ ይለያል... ይሄ እወድሻለሁ ብዙ ማለት ነው። )

"ልብስ ለመቀየር ስንት ደቂቃ ይበቃሻል?" አለኝ ባለው ነገር በአንድ ጊዜ ምስቅልቅል ያለ ስሜት ውስጥ እንዳልከተተኝ ሁሉ በስሱ ፈገግ ብሎ።

ዝቅ ብዬ ልብሴን አየሁት። አዋራ በአዋራ ሆኗል።

"አስር ደቂቃ ስጠኝ "አልኩና ጥድፍ ብዬ ትቼው በበሩ አልፌ ወደ መኝታ ክፍሌ ሄድኩኝ። መኝታ ቤት ገብቼ አልጋው ላይ ዘፍ ቤዬ ተቀመጥኩኝ።

ልቤ መደለቋን አላቆመችም። (ልቤ እንደዚህ ሰርታ የምታውቅ አይመስለኝም። ሃ..) የሚያስቸኩል ነገር ባይኖርብኝ ረጅም ሰአታት ያለኝን እያሰብኩ... አይኖቹን እያሰብኩ...የልብ ምቴን እያደመጥኩ መቀመጥ የምችል ይመስለኛል።

.

.

ከሶስት ሳምንት በፊት መርካቶ ለስራ የሚያስፈልገኝን እቃ ልንገዛ አብረን ሄደን ጨርሰን አንድ ቤት ቡና እየጠጣን "ዛሬ ልደቴ ነው።" አልኩት።

የሚጠጣውን ቡና አቁሞ ዝም ብሎ አየኝና ከኪሱ ሂሳብ አውጥቶ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠ። 

"ነይ እንውጣ።" አለኝ ከወንበሩ ተነስቶ

"ወዴት ልንሄድ ነው?" 

"አላውቅም... አንድ ቦታ። ሃፒ በርዝደይ ብዬ የምዘምርልሽ ቦታ።"

በተቀመጥኩበት ሳኩኝ።

"ልደት ማክበር አልወድም።"

"እኔም።" አለ።

ተነስተን ወጣን። የገዛነውን እቃ ሱቅ ለቤዛ ሰጥተናት መኪና ውስጥ ገባን። 

ደብረዘይት ሄድን። 

በመንገዳችን አስብ የነበረው ምን ያህል ህይወት እየቀደደችልኝ ባለው ወንዝ በዝምታ ለመፍሰስ እንደፈቀድኩ ነበር። 

ያረፍንበት ሎጅ ራት በልተን የያዝነው ማረፊያ ፊት ለፊት ወንበር ላይ ተቀምጠን ወይን እየጠጣን ከታች የሚታየውን ሀይቅ እያየን ስለኢዛና ነገርኩት። ምንም ሳላጎድል። እሱ ያላየልኝ ክፍል እንዲኖረኝ እንደማልፈልግ ሁሉ እያንዳንዱን ነገሬን አሳየሁት... የቆሰለ ልቤን ... የተሰበረ ክንፌን... ልጠግናቸው ያልቻልኳቸው የውስጥ ስብራቶቼን ሁሉ። በዝምታ ሰማኝ። ሩቅ ሩቅ እያየ...

ማታ ከጀርባዬ አቅፎኝ ፊቱን ራሴ ላይ አድርጎ በዝምታ ስናወራ ከአንገቴ ወደማጅራቴ እንባው በዝግታ ሲወርድ ተሰማኝ። በድንጋጤ ሰውነቴ ደነዘዘ። ላየው ልዞር ስል እንዳልዞር በእጁ አጥብቆ ያዘኝ። በዝምታ ብዙ ቆየን።

(እየተሰማው ያለው ነገር ይገባኛል። ስላሳለፍኩት ነገር ስነግረው ለእኔ ከተሰማው ሀዘን በተጨማሪ 'ለእሷ' ስለሰጣት ጊዜ እያሰበ ነው። ለራሄል። የጥፋተኝነት ስሜት ነው። ፀፀት ነው።

የዚያን ዕለት ስለእሷ ሲነግረኝ አይኖቹ ላይ ያየሁት ህመምና ስቃ ከአይምሮዬ በላይ ሆኖብኝ ነበር።

"ህሉ አፈቅራት ነበር። ግን ሞኝ ሆንኩኝ። ከጊዜያዊ መሰልቸቴ በላይ አርቄ ማየት አልቻልኩም። በቁሟ በሀዘን ገደልኳት። የዛን እለት የሞተችው ሁለተኛ ሞት ነበር። ከዚያ በፊት በቸልታዬ ስንቴ ገድያታለሁ ።" 

 የዚያን ቀን ምሽት አልጋዬ ላይ ተኝቼ .. በሂወቴ ውስጥ ሌላ ምእራፍ ተከፍቶ ቀልቤን እሱ ቤት ትቼ መጥቼ... አልጋዬ ላይ እየተገላበጥኩ የማስበው እንዴት ቻለው? እያልኩ ነበር። ህመምን የመቋቋም አቅማችን ግን አይገርምም? ይሄ ሁሉ ደርሶብን መተንፈስ መቻላችን... )

'

"ሀፒ በርዝደይ ልዘምርልሽ?"

Happy birthday to you..

Happy birthday to you...

' እስካሁን የትነበርክ አሮን? የት ነበርክ?'

ሌላ ልደት... ሌላ ትዝታ...!

.

.

የፋሽን ሾው ፕሮግራም እስኪያልቅ ድረስ ሌላ አለም ውስጥ ነበርኩ። በሰራነው ስራ ከዚህ በላይ መደሰት የምችል አይመስለኝም። አደይ የሚል ርዕስ የሰጠነው የልብስ ስብስባችን በአብዛኛው ቢጫ የገነነበት ከዚህ በፊት ከሞከርነው ወጣ ያለ ቆንጆ ስራ ነው። ሞዴሎቻችን ልብሱን ለብሰው ወደዚህ ወደዚያ ሲሊ እዚህ ለመድረስ ምን ያህል እንደተጔዝኩ አሰብኩ። ምንም እንኳን ህይወት ፌር አልሆነችልኝም ብዬ ባስብም ብዙ የተረዳሁኝም ነኝ። 

ሁሉም ነገር አልቆ ከቤዝ ጋር ሰዎችን ስንተዋወቅ ሰላም ስንል ቆይተን መውጣት ስንጀምር እነአሮንን በአይኔ ፈለኳቸው። መውጪያው ጋር ከእቴቴ ጋር ባባን ይዘው ቆመዋል። ስንተያይ ፈገግ አልኩ። ምላሹን ፈገግ አለ። 

ከቤዛ ጋር እያወራን እነአሮን ከቆሙበት ተቃራኒ አቅጣጫ ኮርነሩ ላይ ድንገት አይኔን ስወረውር ልቤን ስልብ ያደረገኝን ነገር አየሁ። መራመዴን በቀስታ አቆምኩ። እግሬ አልነሳ አለኝ። ዝም ብዬ ቆምኩ። 

 ኮርነሩ ላይ ኢዛና ቆሟል። ኢዛና እራሱ። እያየኝ ነው። 

ዞር ያለብኝ መሰለኝ። 

እዚህ ምን ይሰራል? ምን ይሰራል??

እንዳልወድቅ ፈራሁ።

 እንደምንም አይኔን ከጎኑ የቆሙት ሰዎች ላይ አደረኩ።

አንዲት ፈረንጅና ምህረት ከአጠገቡ ቆመዋል። የሆነ አጓጊ ትርኢት እንደሚያዩ ሰዎች ሆነው ያዪኛል።

ምህረት!! ምህረት! እሷው ነች እዚህ ይዛው የመጣችው።

"አንቺ... ህሉ..? " አለች ቤዛ ክንዴን ይዛኝ አይኔን ተከትላ በእኔ አቅጣጫ እነኢዛናን እያየች።

"መፀዳጃ ቤት ደርሼ ልምጣ።" አልኩና በፍጥነት ዞርኩኝ።

ተከተለችኝ።

መፀዳጃ ቤት ገብቼ ሲንኩን ተደግፌ ቆምኩኝ። ምን እየተሰማኝ እንደሆነ አላውቅም።

"ልጅቷ ምህረት ነች አይደል? ባለፈው ሱቅ የመጣችው? ማናቸው ሌሎቹ?"

አይኖቼን ጨፈንኩ። በምንም ቃል የማልገልጠው ስሜት ይንጠኛል።  ሰውነቴ እንግዳ ሆነብኝ። ልቤ ከምትችለው በላይ ትደልቃለች። የሆነ አይነት የተለየ ሪያክሽን ሰውነቴ ውስጥ እየተካሄደ መሰለኝ። ወዲያው ቶሎ ቶሎ መተንፈስ ጀመርኩኝ። ልቆጣጠረ የማልችለው አየር እንደጎርፍ ከውስጤ መውጣት ጀመረ።

"አንቺ ህሉ... ምንድነው የሆንሽው... " ዘላ መጥታ እጄን ያዘችኝ። ልታለቅስ መሰለኝ።

እንደምንም ዞሬ ቧንቧውን ከፍቼ ፊቴን ደጋግሜ ታጠብኩኝ።

"ደህና አይደለሽም.. እርዳታ ያስፈልግሻል.." ለቃኝ ልትወጣ ስትዞር አቅሜን አሰባስቤ እጇን ያዝኳት።

"ተይ... ትንሽ ጊ..ዜ ስጭኝ።" አልኩ እያለከለኩ።

እርግጠኛ ባለመሆን አይነት እያየችኝ አጠገቤ መጥታ አቀፈችኝ። ራሴን ትከሻዋ ላይ አደረኩ። 

ጀርባዬን እያሻሸች ደጋግማ "አይዞሽ... አይዞሽ.."ትላለች..

ከደቂቃዎች በኋላ ትንፋሼ መስተካከል ጀመረ።

"ሌላ መውጪያ አለ?" አልኳት በደከመ ድምፅ..

"አው በዚህ ጋር አለ።" 

በሌላ በር ከአዳራሹ ወጣን። አሮን መኪና ጋር ስንደርስ ቤዛ ደወለችለት። እስኪመጡ ራሴን ለማረጋጋት አድካሚ ጥረት አደረኩ። ገና አሮንና እቴቴ አጠገቤ መጥተው በጥያቄ አይን ሲያዩኝ ድካሜ ፍሬ እንዳላፈራ ገባኝ።

ገና ምንም ሳይሉ ቀድሜያቸው "ትንሽ አሞኛል።" አልኩ።

"ምንሽን ነው? ምን ሆንሽ?" አለች እቴቴ እንደመርበትበት እያለች

".. ጨጔራዬን ... ድካሙም ይሆናል.. " ድምፄ ታሟል።

" ምግብ አልበላም እያልሽ... ለመሆኑ ከነጋ ምግብ ቀምሰሻል.።" በእጇ ግንባሬን ፊቴን ነካካች

"... ሳርፍበት ይተወኛል...። " አልኩና አሮንን አየት አደረኩት

በጭንቀት ገፅ ያየኛል። በሙሉ አይኔ አይኑን ማየት አስፈራኝ። ሁኔታዬን የሚያውቅብኝ መሰለኝ። ያልኩት ነገር ምን ያህል እንደሚያሳምነው አላውቅም። ውስጥ የሆንኩትን ነገር አስተውሎ ከሆነም እንዴት እንደሚረዳው አላውቅም።

 "ደህና ነኝ..ድካም ነው" አልኩት።

በዝምታ ራሱን ነቅንቆ በሩን ከፍቶልን ሁላችንም ገባን። 

ሙሉውን መንገድ የመኪናውን መስኮት ተደግፌ ውጪውን እያየሁ ስብሰለሰል ቆየሁ።

 ነገ በሬ ላይ እንደማገኘው ገብቶኛል። ይሄ እንዲሆን ደግሞ በፍፁም አልፈልግም። ላየው አልፈልግም። አጠገቤ እንዲደርስ አልፈልግም። 

ዞሬ አሮንን አየሁት። ትኩረቱን መንገዱ ላይ አድርጔል።  ልነግረው ፈለኩ። ግን ምን እንደምለው አላውቅም። እንደዚህ የተዘባረኩት እሱን አይቼ ነው ልለው አልፈልግም።

በር ላይ ደርሰን ቤዛ እቅፏ ውስጥ የተኛውን ባባን አቅፋ ስትወርድ እቴቴ ተከተለቻት። አሮንን ልሰናበት ወደ ኋላ ቀረሁ።

"ጥሩ ምሽት ነበር አይደል? ምንም ሳናወራ .." አልኩ።

ፀጉሬን ወደኌላ እያደረገ በመስማማት ቅንድቡን ሰቅሎ 

"ደህና አይደለሽም ...በቂ ረፍት አግኚ። ጠዋት አይሻለሁ። አብረን ቁርስ እንበላለን።" አለኝ

"ደህና እደር" ብዬ ወደቤት ዞርኩኝ።

እቤት ገብቼ የለበስኩትን አወላልቄ አልጋ ውስጥ ገባሁ። ወዲያው እቴቴ የለበሰችውን ልብስ ሳትለውጥ የበጠበጠችውን ተልባ ይዛ መጣች። በግድ ትንሽ ፉት አልኩለት። በወሰድኩት የእንቅልፍ መድሃኒት እገዛ ለማሰብ ብዙ ሳልደክም ካሰብኩት ጊዜ ጊዜ ቀድሞ እንቅልፍ ወሰደኝ። 

ስድስት ሰአት አካባቢ ስልኬ ሲጮህ ነቃሁ። የማላውቀው ቁጥር ነው።

"ማነው በዚህ ሰአት ሚደውለው?" አለች ቤዛ ከእኔ እኩል ነቅታ።

"አሮን ነው። ተኚ።" አልኳት ፈጠን ብዬ

"ብትተኚለት አይሻለውም ለምን ይቀሰቅስሻል...።" ተሸፋፈነች

የለሊት ልብሴ ላይ ጋወን ደርቤ ስልኬን ይዤ ወጣሁና ሳሎን ሶፋ ላይ ሄጄ ተቀመጥኩ። እራሴንና አይኔን ክፉኛ ወጥሮ ይዞኛል። (ያለ ሀኪም ፍቃድ እንቅልፍ ባጣሁ ቁጥር የምቅመው የእንቅልፍ መድሃኒት ውጤቱ ይሄ ነው። የማያቋርጥ ራስ ምታት...)

የደወለው እሱ እንደሆነ ደመነፍሴ ነግሮኛል። አውቄያለሁ።

ለሁለተኛ ጊዜ ተደወለ። ማንሳት ፈራሁ። ስልኩን እያየሁ ፈዝዤ ቆየሁ።

ሶስተኛ ጊዜ ጠራ። አነሳሁት። ጆሮዬ ላይ አድርጌ በዝምታ ጠበኩ።

ከትንሽ የዝምታ ቆይታ በኋላ "ህሉ..." የሚል ድምፅ ተሰማኝ..

ራሱ ነው። የራሱ ድምፅ ነው። 

"እባክሽ አትዝጊው። እባክሽ...."

"...በር ላይ ነኝ። የግቢያችሁ በር ላይ።"

ምንም ማሰብ አልቻልኩም።

ምንም መመለስ አልቻልኩም።

ምንም ቃል ማውጣት አልቻልኩም።

ምንስ እላለሁ?

"...ህሉ"

..ስልኩን ዘጋሁት።

እዚያው ሶፋ ላይ ጉልበቴን እንዳቀፍኩ ተቀመጥኩ። ሁሉ ነገሬ ደንዝዟል። ምን እየተሰማኝ እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም። ብዙ አይነት ስሜት ሲፈራረቅብን እንደነዝዝ ይሆናል። አላውቅም። ለደቂቃዎች አይኔን መሬት ላይ እንደተከልኩ ቆየሁ።  

ምን እየሆነብኝ ነው?

.

.

.

አሮን ለሶስተኛ ጊዜ ብርጭቆውን በወይን ሞልቶ መስኮቱ ጋር ሄዶ ቆመ። በትንሹ በተከፈተው መጋረጃ ከህልውና ቤት ፊት ለፊት የቆመው መኪና ይታየዋል። ሶስት ሰአት አልፎታል ከቆመ። መኪናው ከፋሽን ሾው ፕሮግራም ሲወጡ ጀምሮ ሲከተላቸው እንደነበር አይቶታል። እሱ እንደሆነ አውቋል። ኢዛና። 

ሁኔታዋን አይቶ ነው ያወቀው።

ፕሮግራሙ አልቆ ህልውናና ቤዛ እስኪመጡ ከእቴቴ ጋር ቆመው እየጠበቋቸው ነበር። ከርቀት መድረኩ አካባቢ ይታዩታል። ሰው ሰላም ሲሉ .. ሲያወሩ... በአይኑ እያደነ ያያታል። እያያት ያስባል... ያስባል.. ደግሞ ለሚሰማው ስሜት ስም ሊሰጥ ይለፋል... 

ሲያያት ለሚሆነው...

በዝምታ አጠገቧ ተቀምጦ ለሚሆነው...

እቅፉ ውስጥ ክትት ስትል ለሚሆነው...

ስታወራው አይን አይኗን እያየ ለሚሆነው...

ሳቋን እያየ ለሚሆነው...

ብቸውን ሲሆን.. አልጋው ላይ ተኝቶ... መኪናውን እየነዳ ሲያስባት ለሚሆነው...

አውቆታል የሆነ አይነት ፍቅር ነው የያዘው። ከዚህ በፊት ያላጋጠመው አይነት። ሆኖበት የማያውቅ አይነት።

ጨርሰው ከቤዛ ጋር እያወሩ ሲመጡ ተያዩ። አየችው። ፈገግ አለች። ፈገግ አለ። ወዲያው አይኗን ከእርሱ አንስታ ወደሆነ አቅጣጫ ወረወረችውና ርምጃዋን ቀስ በቀስ ቀንሳ ሙሉ ለሙሉ ቆመች። ግር ብሎት አይኗን ተከትሎ ወደ ጎን ዞረ። በዚያኛው ጥግ ኮሊደር ላይ አንድ ልጅ እንደእሷ ፈዞ ያያታል። በትኩረት ተመልክቶት መልሶ ህልውናን አያት። ገጿ ተለዋውጧል። በቅፅበት ሌላ ሰው ሆናለች።

አልፋት የሄደችው ቤዛ ተመልሳ የሆነ ነገር ትላታለች።

ወዲያው ዞራ መራመድ ጀመረች።

ቤዛ ተከተለቻት።

ልጁን ዞሮ አየው።

በሄደችበት አቅጣጫ እያየ ቆሟል።

ገፁ ነፍስ ያለበት አይመስልም። ብዙም ሳይቆይ ከአጠገቡ ላሉት ሴቶች የሆነ ነገር ብሏቸው በአጠገቡ አልፎ ከአዳራሹ ወጣ። 

ኢዛና ለመሆኑ የሚያረጋግጥለት ሰው አላስፈለገውም። በቅፅበት የሆነችው ሁኔታ በቂ ምስክሩ ነበር። ህልውናን እንዲህ ሊያደርጋት የሚችል ሌላ ሰው የለም።

ከ15 ደቂቃ በኋላ ቤዛ መኪናው ጋር ነን ብላ ደወለችለት። ከአዳራሽ ሲወጣ በአይኑ ኢዛናን ፈለገው። ግቢው መውጪያ ጋር መኪና ውስጥ ተቀምጧል። 

መኪናው ጋር ደርሶ ህልውናን ሲያያት ልቡ ፍስስ አለች። በግልፅ የሆነ ህመም ውስጥ እንዳለች ታስታውቃለች። 

"ትንሽ አሞኛል ..ደክሞኝ ..." ምናምን አለች።

ምንም ማለት አልቻለም። 

በመንገዱ ሊቆጣጠራቸው የማይችላቸው ሀሳቦች ሲረብሹት ቆዩ። ችላ ሊለው ቢፈልግም ተረብሿል። ምክንያታዊ ለመሆን ቢፈልግም የሚቆጣጠረው አልሆነለትም።

.

እንቅልፍ እንደማይወስደው ቢያውቅም ጎኑን ሊያሳርፍ አሰበ። እዚያ ቆሞ ሲያይ መቆየቱ ጥቅም የለውም። ደክሞታል። መጋረጃውን ሊዘጋ እጁን ሲዘረጋ ህልውና የሳሎኑን በር ከፍታ ስትወጣ ታየችው። በዝግታ እጁን የነበረበት መለሰው። 

የከፈተችውን በር ዘግታ የበረንዳውን ሁለት ደረጃ ከወረደች በኊላ ቆመች። በሁለት እጇ የለበሰችውን ጋወን ከሰውነቷ ጋር አጥብቃ ይዛለች። በቆመችበት አምስት ደቂቃ ያህል በር በሩን እያየች ቆየችና ዝቅ ብላ እዚያው ደረጃው ላይ ተቀመጠች። 

 ልቡ ትር ትር ስትል ይሰማዋል። እንድታደርገው አይፈልግም። ሌላው ቢቀር በዚህ ለሊት ወጥታ እንድታገኘው አይፈልግም። 'እባክሽ ህሉ..' ውስጡን የሚገለባብጠውን የስሜት ጎርፍ ምን እንደሚያደርገው ግራ ገባው። 

ቀላል ጉዳይ አይደለም። ኢዛና በትክክል ለእርሷ ማን እንደሆነ ያውቃል። ትናንት በክህደቱ ያቆሰላት ስሙ ሲነሳ በደሉ ብቻ የሚተረክ ሰው አይደለም። ልጅነቷ ነው። በእድሜዋ ጠዋት ላይ ህይወቷ ላይ ብቅ ያለ በሙሉ አቅሟ ያፈቀረችው.. ስርአት ሳታበጅ ራሷን የሰጠችው ሰው ነው። ከአመታት በኋላም የሚያስለቅሳት... የሚያብሰለስላት ሰው ነው። የልጇ አባት ነው። ሁሉን የሰጠችው ሁሉን የተወችለት ሰው ነው። በስራው ልቧንና ቅስሟን ቢሰብረውም .. በጎ ታሪኩን ጨርሶ እንደማያጠፋው ይገባዋል። 

ተብሰለሰለ... አትውጪ እባክሽ ህሉ...

 ለደቂቃዎች ያህል አየር ላይ ስታፈጥ ቆይታ ከተቀመጠችበት ተነስታ ቆመች።

ቀጣዩን ማየት መፈለጉን እርግጠኛ አይደለም። መጋረጃውን ዘግቶ መሄድ ቢፈልግም አልቻለም። 

 ወደ ግቢው በር መራመድ ጀመረች...


ይቀጥላል...


https://t.me/adey_y1

https://t.me/adey_y1



Report Page