Healthy Gut, Healthy Mind
Crohn's & Colitis Ethiopia
ጤናማ የሆድ እቃ፣ ጤናማ አዕምሮ
የሆድ እቃና አዕምሮዋችን እንዴት ይገናኛሉ?
የሆድ እቃና አዕምሮ፤ የሆድ እቃ- አዕምሮ ዘንግ ( Gut- brain axis ) በሚባል የመረጃ ማስተላለፊያ አውታር ከአንጎል ወደ ታች የሆድ እቃ ድረስ፣ እንዲሁም ከሆድ እቃ ወደ ላይ አንጎል ድረስ ይገናኛሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ዋና የሚባሉ የሰውነት ክፍሎቻችን ይህን ግንኙነት የሚያስቀጥሉበት የተለያዩ መንገዶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
I. የነርቭ ስርዓት ( ቫገስ ነርቭ /መስተሃውር ነርቭ)
የሆድ እቃችን ከ500 ሚሊዮን በላይ የነርቭ ሴሎች ወይም ህዋስ ነርቭ ይዧል፡፡ እነዚህም ህዋሳት በነርቮች አማካኝነት ከአዕምሮዋችን የነርቭ ስርዓት ጋር ይገናኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ቫገስ ነርቭ ትልቁና መልዕክትን ወደ ሁለቱም ማለትም ከሆድ እቃ ወደ አዕምሮና ከአዕምሮ ወደ ሆድ እቃ የሚያስተላልፍ ነው፡፡ በእንስሳቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው የአእምሮ ውጥረት ወይም ጭንቀት ይህ ነርቭ መልዕክትን በተገቢው መንገድ እንዳያስተላልፍ በማድረግና ስራውን በማዛባት የሆድ እቃ የመረበሽ ስሜት እንዲከሰት ምክንያት እንደሚሆን ነው፡፡
II. የነርቭ አስተላላፊዎች / Neurotransmitters/
የሆድ እቃና አዕምሮዋችን የነርቭ አስተላላፊዎች በሚባሉ ኬሚካሎችም ይገናኛሉ፡፡ እነዚህ በአንጎላችን ውስጥ የሚመረቱ ኬሚካሎች የሰውነታችንን የስሜት ለውጦች ይቆጣጠራሉ፡፡ የሆድ እቃ ረቂቅ ተህዋሲያንም እንደ ሴሮቶኒን ያሉ ኬሚካሎችን በማምረት የሰውነት ስሜትንና የሆድ እቃን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ፡፡
III. የሰውነት በሽታን የመከላከል ስርዓትና የሰውነት ብግነት
የሆድ እቃ- አዕምሮ ዘንግ በሰውነት የበሽታን የመከላከል ስርዓት በኩልም ይገናኛሉ፡፡ የሆድ እቃና የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን ወደ ሰውነታችን የሚገቡና በደም ውስጥም የሚመጠጡ ነገሮችን የመለየት ሚና ስላላቸው በሰውነት በሽታን የመከላከል ስርዓትና የሰውነት ብግነት ወይም መቆጣት መጠን ላይ ትልቅ አስተዋፆ አላቸው፡፡ በሆድ እቃ ውስጥ ያሉ የበሽታ መከላከያ ሴሎች ከሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን ጋር መስተጋብር ያላቸው ሲሆን፤ የዚህ ግንኙነት ጤናማነት ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በሚመገበው የአመጋገብ ስርዓት ላይ ይወሰናል፡፡ ስለሆነም የእነዚህ የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን ስራ መዛባት የሰውነት የበሽታን የመከላከል ስርዓት በማዛባት ለተለያዩ ህመሞች ይዳርጋል፡፡ ይህ የተዛባ የሰውነት የበሽታ የመከላከል ስርዓት ደግሞ ለረዥም ጊዜ እንደተዛባ ሲቆይ ለተለያየ አይነት የሰውነት መቆጣት ወይም ብግነት ይዳርጋል፡፡ ከዚህም ውስጥ እንደ ድባቴና አልዛይመር የሚባሉ የአዕምሮ ህመሞች ይካተታሉ፡፡
በአጠቃላይ በህመም የተጠቃ የሆድ እቃ የተዛባን መልዕክት ለአዕምሮ የሚልክ ሲሆን አዕምሮም እንዲሁ በስራው ላይ እክል ሲገጥመው የተዛባን መልዕክት ለሆድ እቃ ያደርሳል፡፡
የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን ተፅዕኖ በአዕምሮ ጤና ላይ፡-
የተለያዩ ጥናቶች የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን እና አዕምሮ ተያያዥነት እንዳላቸው ሲገልፁ ከዚህም ግንኙነታቸው ውስጥ በፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ምክንያት የሚከሰት የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን ስራ መዛባት ለተለያዩ ስሜታዊ የባህሪ ለውጦች እንደሚዳርጉ የሚገልፅ ጥናት ይጠቀሳል፡፡ በተለይም በጎልማሳነት የእድሜ ክልል የሚከሰት የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መዛባት ትንንሽ የሚመስሉ ነገር ግን በጊዜ ሂደት እየሰፉ የሚሄዱ የአዕምሮና አካላዊ ህመሞችን ያስከትላል፡፡
ከባቢያዊ ሁናቴዎችና የአኗኗር ዘይቤ ተፅዕኖ በአዕምሮና በሆድ ዕቃ ጤና ላይ፡-
በሆድ እቃ ላይ ትልቁን አስተዋፆ ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ የአመጋገብ ስርዓት፣ መድሃኒቶችና የፀረ ባክቴሪያ ውህዶች ሲጠቀሱ፤ እንደ የሰውነት እንቅስቃሴና የእንቅልፍ ስርዓትም የሆድ እቃንና አዕምሮን ጨምሮ ሁለቱም ላይ አስተዋፆ በማሳደር ከሚጠቀሱት ውስጥ ናቸው፡፡
የአመጋገብ ስርዓት ፡- የአመጋገብ ስርዓታችን የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን አወቃቀርና ስርዓት ላይ ትልቅ አስተዋፆ አለው፡፡ እጅግ በርከት ያሉ ጤናማ ያልሆኑ እንደ ብዙ የቅባትና የስኳር መጠን ያላቸውን ምግቦች በተመገብን ቁጥርና ጤናማ የሚባሉ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ምግቦችን ባልተመገብን ቁጥር የሆድ እቃ ስርዓት እንዲዛባና በርከት ያለ ተግባር ያላቸውም የሆድ እቃ ጠቃሚ ተቂቅ ተህዋሲያን ተግባር እንዲዛባ ምክንያት ይሆናል፡፡
የሰውነት እንቅስቃሴ፡- እንደሚታወቀው የዘውትር የሰውነት እንቅስቃሴ የልብና የደም ዝውውር ስርዓትን በማስተካከል የአዕምሮን ጤና ለመጠበቅ ይረዳል፤ በአንፃሩም የሰውነት እንቅስቃሴ የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያንን መጠንና አወቃቀር የማስተካከል ሚና አለው፡፡ ሆኖም ጤናማ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ መጠን እንደየሰው የሰውነት አቋም፣ የጤና ሁኔታ፣የእድሜ ደረጃና ፆታ ስለሚለያይ ከመጠን ያለፈና ለሰውነት ከሚጠቅመው ይልቅ ፤ በተለይም የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያንን መጠን የሚያዛባና ላልተፈለገ የሰውነት ብግነት ከሚዳርግ እንቅስቃሴ መቆጠብ ይመከራል፡፡
የተለያዩ ንጥረ ነገሮች አጠቃቀም ፡- እንደ አልኮል፣ ኒኮቲን፣ ካናቢስና የተለያዩ በተለይም ህጋዊ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮችን በርከት ያሉ በጎልማሳነት የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ሲጠቀሟቸው ይስተዋላል፡፡ እነዚህን መጠቀም ደግሞ ለአካላዊም ሆነ አዕምሯዊ የጤና ዕክሎች ምክንያት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በርከት ያለን አልኮል መጠቀም ከአዕምሮ ክፍሎች ውስጥ የፊተኛውን ክፍል በማጥቃት የመማር፣የማስታወስ፣የትኩረት ማጣት፣የችኩልነትና ያለማስተዋል ችግሮችን ያስከትላል፡፡ በሆድ እቃ ውስጥም አልኮል፤ የሆድ እቃ ውህዶችን በማዛባት፣ የሰውነት ብግነትን በመፍጠርና በማባባስ እንዲሁም የሆድ እቃ ግድግዳ ሽፋንን ውህደት በማዛባት የጤናን እክል ያስከትላል፡፡
የእንቅልፍ ስርዓት ፡- የእንቅልፍ መዛባት በሆድ እቃ ውስጥ የሚገኙ አስፈላጊና ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያንን መጠንና አወቃቀር በማዛባትና ጤናማ ያልሆኑ ተህዋሲያን እንዲባዙ በማድረግ ጤናችንን ያቃውሳል፡፡ ይህ ደግሞ በሆድ እቃ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በአዕምሮ ላይም ትልቅ ተፅዕኖ አለው፡፡
በቀጣይ ሳምንት ለአዕምሮ ጤና የሚመከሩ የምግብ አይነቶች፣እንደ የአንጀት ቅስለት ያሉ ስር የሰደዱ ህመሞችና የአዕምሮ ጤና እና የመሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት በሚሉ ርዕሶች በሳይንሳዊ መረጃዎች የተደገፈ ማብራሪያን ይዘን እንቀርባለን፡፡
ይከታተሉን!!