Healthy Gut, Healthy Kidney

Healthy Gut, Healthy Kidney

Crohn's & Colitis Ethiopia

Written By Yeabsira Taye

Medically Reviewed by Dr. Hamelmal Gebeyehu Nephrologist

የሰውነት ፈሳሽና የኤሌክትሮላይት መጠን መዛባትና ኩላሊት

ኤሌክትሮላይቶች ምንድን ናቸው?

ኤሌክትሮላይቶች በሰውነታችን ፈሳሽ ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኙ ኬሚካሎች ናቸው፡፡እነዚህም ክሎራይድ፣ፎስፌት፣ፖታሺየም፣ሶድየም እና ካልሺየምን ያካትታሉ፡፡ ኤሌክትሮላይቶች ለጤነኛ እና ለተመጣጠነ የሰውነት ተግባር አስፈላጊ ሲሆኑ በተመጣጠነ እና ለሰውነት በሚያስፈልገው ልክ መገኘት አለባቸው፡፡

በሰውነታችን ውስጥ የተመጣጠነ የኤሌክትሮላይቶች መጠን መኖር ሰውነታችን ተግባሩን በአግባቡ እንዲያከናውን ይረዳዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑትን ኤሌክትሮላይቶች ከምግባቸው ውስጥ ያገኛሉ፤ሆኖም በሰውነት ውስጥ በሚካሄዱ አንዳንድ ሂደቶች ምክንያት በእነዚህ ኤሌክትሮላይቶች መጠን ላይ መዛባት ይከሰታል፡፡ የኤሌክትሮላይቶች አለመመጣጠን ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች አንዱ ብዙ የሰውነት ፈሳሽን በአንድ ጊዜ ስናጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ የሰውነት ላብ እና ማስመለስ ሲኖረን በሰውነታችን ውስጥ ያለ የኤሌክትሮላይቶች መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

ኩላሊታችን በሰውነታችን ውስጥ ያለን የሶድይም መጠንን በማስተካከል እና ሰውነታችን በሚፈልገው ልክ በማመጣጠን ኤሌክትሮላይቶችን በሰውነት ውስጥ የማተካከል ስራን ከሚሰሩ አካላት አንዱ ነው፡፡

የሆድ እቃችንም በቀን እስከ ሁለት ሊትር የሚደርስ በኤሌክትሮላይቶች የበለፀገ ፈሳሽን የመምጠጥ ስራን ያከናውናል፡፡ ስለዚህም በሆድ እቃችን ውስጥ የሚከሰት መቆጣት እና ህመም ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ እንደ ሶድየምና ካልሺየም ( በተለምዶ ጨው የምንለው) ያሉ ንጥረ ነገሮች ወደ ሰውነታችን የመምጠጥ ሂደትን ያስተጓጉላል፡፡ እነዚህ ሁለቱ፤ ሶድየምና ካልሺየም በደማችን ውስጥ ያለን ውሃ በማመጣጠን ሂደት ላይ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ ስለዚህም በተገቢው መጠን ሳይገኙ ሲቀሩ ኩላሊት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡

በሰውነታችን ውስጥ ያሉ የኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ከኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት ምልክቶች ውስጥ የተወሰኑት፡-

·       ቁርጠት

·       የማዞር ስሜት

·       ከመደበኛው የተለየ የልብ ምት

·       ድካም

በአንጀት ቁስለት ህመም ምክንያት የሚከሰት የሰውነት ፈሳሽና ኤሌክትሮላይት መጠን መዛባትና የኩላሊት ህመም

በርከት ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአልሰሬቲቭ ኮላይተስና በክሮንስ ህመም ታካሚዎች ላይ የሚከሰት የኤሌክትሮላይቶች እጥረት አነስ ያለ ጉዳትን ከማስከተል ጀምሮ ለህይወት እስከሚያሰጋ ደረጃ ድረስ ሊደርስ እንደሚችል ነው፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት በተለይም በአንጀት ቁስለት ህመም ንቁ የህመሙ ደረጃ ላይ በአንጀት ግድግዳ ንጣፍ ቁስለት ምክንያት የሚከሰት የአንጀት መዋቅር ለውጥ የሰውነታችን ኤሌክትሮላይቶች በአስፈላጊው መጠን እንዳይመረቱና ወደ ሰውነታችንም እንዳይመጠጡ በማድረግ የኤሌክትሮላይቶችን መጠን መዛባት ያስከትላል፡፡ እንደ ማስመለስና ማስቀመጥ ባሉ ምክንያቶች ሰውነታችን ብዙ ፈሳሽን በሚያጣበት ጊዜም የኤሌክትሮላይቶች መዛባት የመከሰት እድሉ የሰፋ ይሆናል፡፡

በጤነኛ የሰውነት ሁኔታ ኩላሊታችን ደማችንን በማጣራትና አላስፈላጊ ንጥረ ነገሮች በማስወገድ የተስተካከለና የተመጣጠነ የሰውነት ፈሳሽና ኤሌክትሮላይት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ስለዚህም የኩላሊት ተግባር ላይ መዛባት ሲከሰት የኤሌክትሮላይቶችና የሰውነታችን ፈሳሽ ላይም መዛባት እንዲከሰት ይሆናል፡፡ ልክ እንደዚሁ እንደ የአንጀት ቁስለት ህመም ባሉ ህመሞች ምክንያት የሚከሰት የኤሌክትሮላይት መጠን መዛባት በኩላሊት ስራ ላይ ተፅዕኖው የጎላ ነው፡፡

የኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት ምርመራ

ይህ ምርመራ በቀጥታ የደም ናሙናን በመውሰድና በመመርመር ሊካሄድ ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ምርመራ የኤሌክትሮላይቶች መዛባት በሰውነታችን ውስጥ ለምን እንደተከሰተ ማወቅ ላንችል እንችላለን፡፡ ስለዚህም እንደ ሌሎች የደም ምርመራ አይነቶች፣ በምስል ውጤትን የሚገልፁ የምርመራ ሂደቶችንና ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎች ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡

የኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት ህክምና

የኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት ህክምና፤ ይህንን ችግር እንዳስከተሉት የጤና ችግሮች አይነት ላይ ይወሰናል፡፡አብዛኛውን ጊዜ የኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባትን ያስከተሉት የጤና ችግሮች ሲታከሙ፤ ይህ መዛባትም ይስተካከላል፡፡ ብዙ የሰውነት ፈሳሽን ማጣት ለዚህ ለየኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት ምክንያት ከሆነ ታካሚው በደምስር የሚሰጡ የሰውነት ፈሳሽን የሚተኩ መድሃኒቶችን እንዲወስድ ይደረጋል፡፡በሌላ በኩል ታካሚው ከአስፈላጊው መጠን በላይ የሆነ የኤሌክትሮላይት መጠን ካለው ብዙ ፈሳሽን ከመውሰድ እንዲቆጠብና ይህንን ከመጠን የበዛ ፈሳሽ በሽንት የሚያስወግዱ መድሃኒቶችን እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

የኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት እንዳይከሰት ምን ማድረግ እንችላለን?

1. ዉሃን መጠጣት ፡- ዉሃን መጠጣት ቀላሉና ወሳኙ በኤሌክትሮላይቶች መጠን መዛባት ምክንያት የሚከሰቱ ውስብስብ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ልንከላከልበት የምንችለው መንገድ ነው፡፡ በተለይም የሰውነት እንቅስቃሴ ስናደርግ የሚወጣውን ፈሳሽ ለመተካት ውሃን መውሰድ አለብን፡፡ ከዚያ በተጨማሪም የሰውነት ፈሳሽን በፍጥነት የምናጣበት ሁኔታ ሲከሰት እንደ የለስላሳ መጠጦች ያሉ ካርቦኔትድ መጠጦች የሚባሉት መጠቀም የሰውነት የስኳር መጠን በጣም በፍጥነት እንዲጨምር ሊያረጉት ስለሚችሉ እነዚህን መጠጦች መጠቀም አይመከርም፡፡

2. በኤሌክትሮላይት የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ ፡- እንደ ካሮት፣አቮካዶ፣ብርቱካን፣ሙዝ፣እንጆሪና ሰላጣ ያሉ ምግቦችን መመገብ የኤሌክትሮላይቶች መጠንን ለማስተካከል እና ለመጠበቅ ይረዳናል፡፡ በኢንዱስትሪ የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶ መጠቀም በጤና ላይ ጉዳት ስለሚኖረው ይህንን መቀነስም አለብን፡፡


በቀጣይ ሳምንት ከኩላሊት ህክምና ባለሙያ ዶ/ር ሀመልማል ገበየሁ እንዲሁም ከኢትዮጲያን ኪድኒ ኬር መስራች እና ስራ አስኪያጅ ጋር በሚኖረን ቆይታ ስለኩላሊት ጤና አጠባበቅ፣ ከአንጀት ጤና ጋር ምን እንደሚያገናኘው እና የመሳሰሉት መረጃዎችን በቀጥታ ስርጭት ይከታተሉ። ባለሙያዎቹን መጠየቅ እንዲሁም በዝግጅቱ ላይ አስተያየት መስጠት ይቻላል። አልያም ቀድመው ስለኩላሊት ጤና እና አንጀት ጤና ያሎትን አስተያየት በማህበራዊ ትስስራችን ላይ በመጻፍ ልናደርስሎት እንችላለን።


ቀጥታ ስርጭት ዕሮብ በቲክቫህ ማጋዚን ላይ ብቻ!

Crohn's & Colitis Ethiopia


ማጣቀሻ

1. Kunzelmann K, Mall M. Electrolyte transport in the mammalian colon: mechanisms and implications for disease. Physiol Rev. 2002;82:245–289. [PubMed ] [ Google Scholar ].

2. Debongnie JC, Phillips SF. The capacity of the human colon to absorb fluid. Gastroenterology. 1978;74:698–703. [PubMed ] [ Google Scholar ]

3. Halm DR, Halm ST. Secretagogue response of goblet cells and columnar cells in human colonic crypts. Am J Physiol Cell Physiol. 2000;278:C212– C233. [PubMed ] [ Google Scholar]

4. Lubran M, Mc AP. Potassium deficiency in ulcerative colitis. Q J Med. 1951;20:221–232. [ PubMed] [ Google Scholar]

5. Head LH, Heaton JE, Jr, Kivel RM. Absorption of water and electrolytes in Crohn's disease of the colon. Gastroenterology. 1969;56:571–579. [ PubMed] [ Google Scholar]

6. Beeken WL. Remediable defects in Crohn's disease: a prospective study of 63 patients. Arch Intern Med. 1975;135:686–690. [PubMed ] [ Google Scholar ]

7. https://www.karger.com/Article/Fulltext/326682#menu

Report Page