Healthy Diet, Healthy Gut
Crohn's & Colitis Ethiopia
አመጋገብና የሆድ እቃ ጤና
የምግብ ልመት ስርዓት
ምግብ በምግብ ልመት ስርዓት ውስጥ ያለውን ሚና ለማወቅና ለመረዳት፤ የምግብ ልመት ስርዓት በራሱ ምን እንደሆነ መረዳትና ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
የምግብ ማሳለፊያና መፍጫ ቧንቧ ከአፍ ጀምሮ እስከ ፊንጢጣ ይዘልቃል፡፡ ይህም የምንመገበው ምግብ እንዲፈጭና ከምግብ የሚገኙ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች ወደ ሰውነታችን እንዲመጠጡ ይረዳናል፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ ለሰውነት እድገት፣ ሀይልና ጉልበትን ለማግኘትና በሽታን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡
ምግብ በአፍ ውስጥ ከላመ በሗላ በምግብ ቧንቧ ወደታች በማለፍ ሆድ እቃ ውስጥ ይገባል፤ በሆድ እቃ ውስጥም በጨጓራ አሲድና ሌሎች ውህዶች በመታገዝ የተወሰነ የመፈጨት ሂደትን ካካሄደ በሗላ ወደ ትንሹ አንጀት ይጓዛል፡፡ በአንጀት ውስጥም የተቀረውን የመፈጨት ሂደት ይከናወንና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወደ ሰውነት እንዲመጠጡ ይሆናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የተፈጠሩት ከሰውነት መወገድ ያለባቸው ነገሮች ወደ ትልቁ አንጀት ይጓዛሉ ፤ ትልቁ አንጀትም በእነዚህ ውስጥ ያለውን ውሃ ወደ ሰውነት በመምጠጥ ቀሪው ከሰውነታችን እንዲወገድ ያደርጋል፡፡
ጤናማ የሆድ እቃ
በደፈናው የሆድ እቃችን ጤናማ ነው የምንለው እንደ የምግብ ማሳለፊያ ቱቦ፣ ጨጓራና አንጀት በአንድነት በመስራት ምግብን መመገብ ስንችልና የተመገብነውን ምግብም መፍጨትና አላስፈጊ ነገሮችን ያለ እንከን ማስወገድ ስንችል ነው፡፡ በሆድ እቃ ውስጥ ያሉ የጠቃሚ ባክቴሪያዎች መጠንና ተግባር የተስተካከለ መሆንም የሆድ እቃን ጤናማ ነው ከሚያስብሉት ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡
ጤናማ የሆድ እቃ ጠቃሚ ባክቴሪያዎችንና በሽታ ተከላካይ ጥቃቅን ህዋሳትን ስለሚይዝ ሰውነታችንን እንደ ባክቴሪያ፣ቫይረስና ፈንገስ ካሉ በሽታን ከሚያስከትሉብን ነገሮች ይከላከልልናል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ጤናማ የሆድ እቃ በነርቭና ሆርሞኖች አማካኝነት ከጭንቅላት ጋር ስለሚገናኝ አጠቃላይ የሰውነት ጤናችንን ለመጠበቅም ትልቅ አስተዋፆ አለው፡፡ ስለሆነም ጤናማ የአመጋገብ መንገድን በመከተል፣ በቂ እንቅልፍ በመውሰድ፣ የሰውነት እንቅስቃሴን በማድረግና ከሃኪም ትዕዛዝ ውጪ መድሃኒቶችን ከመውሰድ በመቆጠብ የሆድ እቃ ጤናችንን መጠበቅ አለብን፡፡
አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለምን እንድንመገብ ይመከራል?
ከላይ እንደተጠቀሰው ለጤናማ የሆድ እቃ፣ ጤናማ አመጋገብ ዋናውና ቁልፉ ነገር ነው፡፡ ከዚያም መካከል ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ ዋነኛው ነው፡፡
ብዙውን ጊዜ አትክልትና ፍራፍሬን ያካተተ አመጋገብ ለጤና እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ይጠቀሳል። ለእነዚህም የጤና ጥቅሞች ዋና ዋና ምክንያቶች ከሚባሉት ውስጥ የተወሰኑት፡-
Ø አትክልትና ፍራፍሬዎች የቫይታሚንና ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ማዕድናት ምንጭ ናቸው፡፡
- ከአትክልትና ፍራፍሬዎች የተሻለ የቫይታሚን ኤ፣ሲ እናኢ እንዲሁም የማግኒዥየም፣ዚንክና ፎስፈረስ ምንጭ አለ ለማለት ይቸግራል፡፡ ስለዚህም አትክልትንና ፍራፍሬዎችን ስንመገብ በውስጣቸው ካለው ቫይታሚንና ማዕድናት የተነሳ፤ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅምን መጨመር፣ ቁስል በቶሎ እንዲድን፣ አጥንቶቻችን ጠንካራ እንዲሆኑና የተስተካከለ የሰውነት ሆርሞን መጠን እንዲኖረን ይረዳናል፡፡
Ø በአትክልትና ፍራፍሬዎች ውስጥ ያለው የጨው መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡
- ትኩስ አትክልትና ፍራፍሬዎች በውስጣቸው ያለው የጨው እንዲሁም የስኳር መጠን ጥቂት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮሌስትሮን በአትክልትና ፍራፍሬዎች ውስጥ የለም፡፡ ስለዚህም በኮሌስትሮንና ከመጠን ባለፈ የጨው መጠን ምክንያት የሚከሰቱ ህመሞችን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡
Ø አትክልትና ፍራፍሬዎች እንደ ካንሰር፣ የልብ ህመምና አይነት ሁለት የስኳር ህመምን ለመከላከል አስፈላጊ ናቸው፡፡
- በርከት ባሉ የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶች ውስጥ በራሳቸው በተክሎቹ የሚመረቱ የኬሚካል ቅመሞች (phytochemicals) ለአትክልትና ፍራፍሬዎች በሽታን የመከላከል ባህሪ የሚሰጡት ምክንያቶች ናቸው፡፡
Ø አትክልትና ፍራፍሬዎች በውስጣቸው ባለው የፀረ ኦክሲዳንት (antioxidant) ሃይል የሰውነት መቆጣትንና መቁሰልን የመከሰት እድል ይቀንሳሉ፡፡
እንደ አትክልትና ፋራፍሬዎች ውስጥ ካሉ ውህዶች ወይም ንጥረ ነገሮች ውስጥ በርከት ካለ የጤና ጥቅሞቹ አንፃር በተደጋጋሚ የሚነሳው polyphenol ነው፡፡
polyphenols ምንድን ናቸው?
polyphenols ከእፅዋት በሚገኙ ምግቦች ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ፍራፍሬዎች፣ አትክልቶች፣ ቅጠላ ቅጠሎች፣ ቅመማ ቅመሞች፣ ሻይና ወይን ይጠቀሳሉ፡፡ የpolyphenol የምግብ ምንጮችን አዘውትሮ መመገብ የምግብ መፍጨት ስርዓትን ለማሳለጥ፣የልብ ህመምን ለመከላከል፣ የአይነት ሁለት የስኳር ህመምንና የተወሰኑ የካንሰር ህመም አይነቶችን ጭምር ለመከላከል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
እነዚህ polyphenols በሰውነት ውስጥ ያሉ free radicals የሚባሉና በሰውነት ውስጥ በብዙ መጠን ከተገኙ ጥቃቅን ህዋሳቶቻችንን በማጥቃት እንደ ካንሰር፣የስኳር ህመምና የልብ ህመም ያሉ ችግሮች የሚያስከትሉትን የማስወገድ እጅግ ትልቅ አስተዋፆ አላቸው፡፡በምግብ ውስጥ ያለ የ polyphenols መጠንና አይነት እንደ የምግቡ መገኛ፣ የመጓጓዝ ሂደት፣የአቀማመጥ ሁኔታና የአበሳሰል መጠን ላይ ይወሰናል፡፡
#በቀጣይ ሳምንት የ polyphenols የጤና ጥቅሞች በዝርዝርና እነዚሀንም ከምን ከምን አይነት ምግቦች እንደምናገኝ የምንገልፅ ይሆናል፡፡ ይከታተሉን!!
Crohn's & Colitis Ethiopia
June 29, 2022