#Hamza

#Hamza


የኦሳማ ቢን ላደን ልጅ ፣ ሐምዛ ቢን ላደን፣ 'በአየር ጥቃት መገደሉ' ተነገረ

የአልቃይዳ መስራች የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ወንድ ልጅ፣ ሐምዛ ቢን ላደን፣ በአየር ጥቃት ወቅት መገደሉን የአሜሪካ የስለላ ባለስልጣናት ጠቅሰው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኀን ዘገቡ።

ሐምዛ መቼና የት እንደሞተ የተነገረ ምንም ነገር የለም። ፔንታጎንም በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን አልሰጠም።

የካቲት ወር ላይ የአሜሪካ መንግሥት ሐምዛ የት እንዳለ ለጠቆመ የአንድ ሚሊየን ዶላር ጉርሻ እንደሚሰጡ ተናግረው ነበር።

ሐምዛ ቢን ላደን ዕድሜው 30 የሚገመት ሲሆን፣ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት ላይ ጥቃት እንዲፈፀም የሚጠይቅ የቪዲዮና የድምፅ መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

ይህ ዘገባ መጀመሪያ ላይ የወጣው በኤንቢሲ እና በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆኑ የኋይት ሐውስ የሀገር ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልቶን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ሐምዛ ቢን ላደን አባቱን በጎርጎሳውያኑ 2011 ግንቦት ወር ላይ የገደሉት አሜሪካኖች ላይ ጂሀዲስቶች ጥቃት እንዲፈፅሙ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

አክሎም የአረብ ሰላጤ ሀገራት እንዲያምፁ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ሳውዲ ዓረቢያ መጋቢት ወር ላይ ዜግነቱን ነጥቃዋለች።

በኢራን ውስጥ በቤት ውስጥ የቁም እስር ላይ እንዳለ ይታመን የነበረ ሲሆን ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን እና ሶሪያ መሆኑን ይጠቅሱ ነበር።

ከአሜሪካ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቢን ላዲን በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2011 ፓኪስታን አቦታዳድ ውስጥ ከተገደለ በኋላ፣ ሐምዛ የአባቱን ስፍራ እንዲወስድና አልቃይዳን እንዲመራ ታጭቶ ነበር።

አባቱ ከተገደለበት ቤት ውስጥ ከተሰበሰቡ መረጃዎች መካከል የሐምዛ የሠርግ ስነስርዓትን የሚያሳይ ቪዲዮ የተገኘ ሲሆን በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ሐምዛ ከሌላ የአልቃይዳ ከፍተኛ አመራር ልጅ ጋር ጋብቻውን ሲፈፅም ይታያል።

የሠርግ ስነስርዓቱ ኢራን ውስጥ እንደተካሄደ ይታመናል።

የሐምዛ አማች ይሆናሉ ተብለው የሚጠረጠሩት አብዱላህ አህመድ አብዱላህ ወይንም አቡ ሙሐመድ አል ማስሪ ሲሆኑ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1998 በታንዛኒያና በኬኒያ የአሜሪካ ኢምባሲዎች ላይ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ይታመናል።

አልቃይዳ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር መስከረም 11 2001 በአሜሪካ ጥቃት ያደረሰ ሲሆን ከዚያ በፊት ግን ይህ እስላማዊ ቡድን እዚህ ግባ የሚባል ትኩረት ተሰጥቶት አያውቅም ነበር።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Report Page