Gut Health, Reproductive Health

Gut Health, Reproductive Health

Crohn's & Colitis Ethiopia

☞ የተለያዩ ስር የሰደዱ ህመሞች መድሃኒቶችና የስነ-ተዋልዶ ጤና 

የስነ ተዋልዶ ጤና፣ ከተዋልዶ ስርዓትና ሂደት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሙሉ የአካል፣ የአዕምሮና ማህበራዊ ጤንነት መጎናፀፍ ማለት እንደሆነ ከዚህ ቀደም አንስተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስር የሰደዱ ህመሞች ደግሞ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ህመሞች ሆነው ቀጣይነት ያለው የህክምና ክትትል የሚፈልጉ፤ የተለያዩና በርካታ አይነት ናቸው፡፡ በእነዚህ ስር በሰደዱ ህመሞች በተጠቁ ታካሚዎች ዘንድ የስነ ተዋልዶ ጤናቸው ከህመሞቹ ባህሪና ሰውነታቸው ለህመሞቹ ከሚሰጠው ምላሽ በተጨማሪ ለህመሞቹ በሚታዘዙ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት የተነሳ በተለያየ መንገድ ተፅዕኖ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ይህ ተፅዕኖ በነርቭ ፣ በጡንቻ፣በደምና በአጥንት ስርዓቶች ላይ ይንፀባረቃል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው ስር የሰደዱ ህመሞች አይነት እጅግ በርካታ እንደመሆኑ ለህመሞቹ የሚታዘዙ መድሃኒቶችም አይነት፣ ተግባር፣ የደም ውስጥ ስርጭትና የጎንዮሽ ጉዳትም በዛው ልክ እጅግ ሰፊና የተለያየ ነው፡፡ ከነዚህ ህመሞችና መድሃኒቶቻቸው ውስጥ የተወሰኑት የስነ ተዋልዶ፣ በተለይም የመራቢያ አካላት ላይና የተራክቦ ፍላጎትና ጤናማነት ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ እንዳላቸው ቢገለፅም መድሃኒቶቹ የሚታዘዙት ለህመሞቹ መፍትሄን ለማግኘት እጅግ ወሳኝ በመሆናቸው በመሆኑ እነዚህን መድሃኒቶችም ያለ ሃኪም ትዕዛዝ ማቋረጥ የማይቻል ሲሆን ሌሎች አማራጭ ዘዴዎችን በመጠቀም የጎንዮሽ ጉዳታቸውን ለመቀነስ እንዲሁም በተራክቦ ሂደትም ከፆታ አጋሮች ጋር በመሆን መወያየትና መደጋገፍ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ስር ለሰደዱ ህመሞች ከሚታዘዙ መድሃኒቶችና የስነ ተዋልዶ ጤና ተጽዕኖዎቻቸው ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ፡- 

♦ የከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብና ከደም ጋር ለተያያዙ ችግሮች የሚታዘዙ እንደ ቤታ ብሎከር፣ዳይሬቲክስና ቫሶዲያሌተርስ የሚባሉት ምድቦች በተወሰኑ ሰዎች ላይ የተራክቦ ፍላጎትን የመቀነስ፣ በወንዶች ላይ የብልት አለመነሳት እንዲሁም በእርግዝና ጊዜ ደግሞ ለፅንሱ እድገትና ጤናማነት ተጽዕኖ ያላቸው ሊሆኑ የሚችሉ የመድሃኒት ዘርፎች ስላሏቸው እርግዝናን ከማቀዳችን በፊት ከሃኪም ጋር መወያየትና መድሃኒቶቹን መቀየር ያስፈልጋል፡፡ 

♦ ከስኳር ህመም መድሃኒቶች ውስጥ ሜቲፎረሚን፣ ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ለተባለውና የተዛባ የእንቁላል መለቀቅ፣ የኤስትሮጅን ሆርሞን መጠና መጨመርና የማህፀን የላይኛውን ክፍል በማጠንከር ጤናማ ያልሆነ የደም መፍሰስ በማስከተል የመራባት አቅምን የሚቀንሰውን ችግር በማሻሻል ይረዳል፡፡

♦ የሰውነት የተፈጥሮ በሽታን የመከላከል ስርዓት መዛባት/ ስህተት ችግሮች-( autoimmune disease)- እንደ የአንጀት ቁስለትና የአንጓ ብግነት (arthritis) ላሉ ህመሞች የሚታዘዙ የተለያዩ መድሃኒቶች የሆርሞኖችን መጠን ከማዛባት ጀምሮ እስከ በማህፀን ውስጥ ያለን እንቁላልን የማምረት ሂደትና እርግዝና ድረስ ያለው ሂደት ላይ የተለያየ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህም የቱን መድሃኒት በምን ሁኔታ ላይ መወሰድ እንዳለበት ከሃኪም ጋር በመመካከር መወሰን እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡

♦የካንሰር መድሃኒቶች- ለካንሰር ህክምና የሚታዘዙ የኬሞቴራፒና የተለያዩ የቀዶ ህክምናዎች በሴቶች ላይ የኤስትሮጅን ሆርሞን መጠንን በማዛባት የእንቁላል ምርት ላይ ፣በወንዶች ደግሞ የወንድ የዘር ፍሬ አምራች ህዋሳት ምርት ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ከሃኪም ጋር በመመካከር የተሻሉትን የህክምና አማራጮች መውሰድና የጎንዮሽ ጉዳትን መቀነስ፣ የተሻሻለ የስነ ተዋልዶና የእርግዝና ወቅት እንዲኖር ማስቻል እንዲሁም ጤናማ ልጅን መውለድ ይቻላል፡፡

☞ የስነ-ተዋልዶ ጤናዬን እንዴት ማሻሻል እችላለሁ?

የስነ-ተዋልዶ ጤና ከአጠቃላይ የሰውነት ጤና መገለጫ አንዱ እንደመሆኑና ትውልድ በማስቀጠል ሚና ውስጥ ትኩረት የሚሻ ስለሆነ፣ በተለይም የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል የዚህን የስነ-ተዋልዶ ጤና ማሻሻልና ማስተካከል ይቻላል፡፡ ይህን ለማድረግ ከሚያስችሉን የተወሰኑ መንገዶች ውስጥ፡- 

* ጤናማ የሆነ የአመጋገብ መንገድን መከተል፡- ይህ ከፍተኛ ስብና ስኳር ያላቸውን ምግቦች ከማስወገድ ጀምሮ በቂ ውሃን መጠጣትን ያካትታል፡፡

* በቂ እንቅልፍ ማግኘት

* የሰውነት እንቅስቃሴን ማድረግና የአዕምሮ ጭንቀትን ማስወገድ

* ሲጋራን ከማጨስ መቆጠብ፣ የአልኮል መጠንን መቀነስ

* የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር

 * የስነ-ተዋልዶን ጤናን ለማረጋገጥ በየጊዜው ምርመራን ማድረግ 

* ሌሎች ህመሞች ካጋጠሙን ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ህክምናና መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ

* የወሲባዊ ጤናን ለመጠበቅ አንድ ለአንድ መወሰን

* አስፈላጊ የሆኑ የእርግዝናና የአባላዘር ህመም መከላከያዎችን በአግባቡ መጠቀም

* ከፆታና ከትዳር አጋር ጋር በግልፅ መመካከርና መተጋገዝ

☞ ማጠቃለያ

እስካሁን ስናነሳው በቆየነው የጤናማ የሆድ እቃ፤ ጤናማ ስነ-ተዋልዶ ርዕስ ጤናማ የሆድ እቃ ፤ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያንና በሽታ ተከላካይ ጥቃቅን ህዋሳትን ስለሚይዝ ሰውነታችንን እንደ ባክቴሪያ ፣ቫይረስና ፈንገስ ካሉ በሽታን ከሚያስከትሉብን ነገሮች ከመከላከል ባሻገር በነርቭና ሆርሞኖች አማካኝነት ከጭንቅላት ጋር ስለሚገናኝ አጠቃላይ የሰውነት ጤናችንን ለመጠበቅም ትልቅ አስተዋፆ እንዳለው አንስተናል፡፡ ከዚህም ውስጥ የሰውነት ሆርሞኖች የማመንጨት፣ ማዋሃድና ማሰራጨት ሂደት ላይ ያለው አስተዋጾም ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ምክንያት የሆድ እቃ ጤናችን ከስነ- ተዋልዶና መራባት ሂደትን ጋር በቀጥታ ይገናኛል ማለት ይቻላል፡፡ስለዚህም፣ከሆድ እቃ ችግሮች ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የስነ-ተዋልዶ ችግሮችን ለመከላከልና የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መጠንና ጤናን መጠበቅ፤ የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ የሰውነት እንቅስቃሴን ማድረግና ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ተገቢውን የጤና ክትትል ማድረግ አለብን፡፡

በተጨማሪም ስር በሰደዱ ህመሞች በተጠቁ ታካሚዎች ዘንድ የስነ-ተዋልዶ ጤናቸው ከህመሞቹ ባህሪ፣ሰውነታችን ለህመሞቹ ከሚሰጠው ምላሽና ህመሞቹን ለመቆጣጠር ከሚታዘዙ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት የተነሳ በተለያየ መንገድ ሊጠቃ እንደሚችልም ጠቅሰናል፡፡ በመሆኑም በሁለቱም ፆታዎች ላይ ስር በሰደዱ ህመሞች ምክንያት የሚከሰቱትን የስነ-ተዋልዶ ችግሮች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተከታታይነት ያለው ቅድመ ምርመራዎችን ማድረግና ችግሮቹም ከተከሰቱ ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ተገቢውን የህክምና ድጋፍ ማግኘትና መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፤ በተጨማሪም ችግሮቹ ምንም እንኳ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆዩ ቢችሉም ፣ ህመሞቹን መቆጣጠር ከዚያም አልፎ መዳን እንደሚቻል በማመንና በዙሪያችን ካሉ ሰዎች እርዳታን በመጠየቅ፣የስነ ልቦና ጤናችንን መጠበቅ ይመከራል፡፡

በቀጣይ ሳምንት እስካሁን ስንወያይበት በቆየነው ርዕስ ዙሪያ ባለሙያ ጋብዘን፣ ከእናንተ የሚደርሱንን ጥያቄዎች አካተን በቀጥታ ስርጭት ሰፊ ማብራሪያን ይዘን እንቀርባለን፡፡

ይከታተሉን! 

ክሮንስና ኮላይተስ ኢትዮጵያ

Source

https://www.aafp.org/pubs/afp/issues/2003/0115/p347.html

Report Page