Gut Health, Reproductive Health

Gut Health, Reproductive Health

Crohn's and Colitis Ethiopia

☑️ እርግዝናና ስር የሰደዱ ህመሞች 

እንደሚታወቀው እርግዝና ልጅ የምንጠብቅበት ጊዜ ነው፡፡በዚህ ወቅት ሰውነት በተፈጥሮ አዲስ ለተፀነሰው ፅንስ ልዩ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ስር በሰደዱ ህመሞች ውስጥ ለሚያልፉ እናቶች ደግሞ ጤናማ በሆነ የቅድመና ድህረ እንዲሁም የእርግዝና ወቅት ውስጥ ለማለፍ ሰውነታችን ልዩ ክብካቤና ድጋፍ ሊያስፈልገው ይችላል፡፡

ስር ከሰደዱ ህመሞች ውስጥ፤የተለያዩ ኢንፌክሽኖችን የሚከላከሉ የሰውነት ህዋሳት ጤነኛ የሆኑትን የሰውነት ህብረህዋሳት በሚያጠቁበት ጊዜ የሚከሰቱ እንደ የአንጀት ቁስለት ያሉ ህመሞች፣ደምን የደም ስሮችን ልብንና ሳንባን የሚያጠቁ እንደ አስም፣ የልብ ችግሮች፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም ከሆርሞኖች ጋር የሚያያዙ እንደ የስኳር ህመምና የታይሮይድ ሆርሞን ችግሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የእነዚህ ህመሞች ባህሪ በእጅጉ የተለያየና ሰፊ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን በተለይም በህመሞቹ ንቁ ደረጃ ላይ የሚፈጠር እርግዝና የሰውነት መቆጣትና የመደበኛ ሆርሞን መዛባት ችግሮችን በማባባስ የማህፀን የፅንስ መሸከም ሂደትን ሊያደናቅፈው ይችላል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ እርግዝናው በራሱ ለሰውነት፣ በተለይም በመጀመሪያዎቹና በመጨረሻዎቹ ሳምንታት፣የሰውነት መቆጣት( inflammatory state ) አይነት ምላሽን ይሰጣል፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ስር በሰደዱ ህመሞች ምክንያት የተፈጠረን የሰውነት መቆጣት ሊያባብሰው ይችላል፡፡

ስር የሰደዱ ህመሞች እንደ ያለጊዜ መውለድ፣ውርጃ፣በማህፀን ውስጥ የፅንስ መጨናገፍ፣በህጻኑ ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮች እንዲሁም ያለመውለድና የመሃንነት ችግሮችን ሊያስትሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ መከታተልና መቆጣጠር ብሎም ጤናማ በሆነ የእርግዝና ሂደት ጤናማ ልጅን መውለድ ይቻላል፡፡ በተለይም እርግዝናን በማቀድ በቅድመ እርግዝና ወቅት ከሃኪም ጋር በመመካከር ሰውነት ተገቢውን ዝግጅት ለሚመጣው ፅንስ እንዲያደርግ ማገዝ ይቻላል፡፡ ይህም እንዲሆን ተገቢውን የንጥረ ነገር ማማያዎች መውሰድ፣ ስር ለሰደዱ ህመሞች የምንወስዳቸው መድሃኒቶችን ካሉ ለፅንሱ ያላቸውን የጎንዮሽ ጉዳት ከሃኪም ጋር በመወያየት መድሃኒቶቹን ማስተካከል/መቀየር፣ አስፈላጊ የሆኑትን የእርግዝና ክትትሎች ያለማቋረጥ መከታተል እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

☑️ የእርግዝና መከላከያዎችና ስር የሰደዱ ህመሞች 

የእርግዝና መካላከያ ዘዴዎች ያልተፈለገን እርግዝና ለመከላከል የሚውሉ ናቸው፡፡ እነዚህ የእርግዝና መከላከያዎች ሰፋ ያለ አማራጮችን ያካትታሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሆርሞን ጥቅልሎች፣ ሆርሞን የሌላቸው ጥቅልሎች፣መርፌ፣የተዋሃደ የአፍ ክኒን፣በክንድ የሚቀበር መከላከያ፣በሴት ብልት ውስጥ የሚደረግ መከላከያ፣ኮንዶም፣የቀዶ ጥገና እንዲሁም የድንገተኛ ጊዜ የእርግዝና መከላከያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ የእርግዝና መከላከያዎች ሲመረቱና ሲዘጋጁ በሙሉ ጤና ላይ ላሉ ሰዎች ታስበው እንደመዘጋጀታቸው ስር በሰደዱ ህመሞች ውስጥ ላሉ ሰዎች በሚሰጡበት ጊዜ የጎንዮሽ ውጤቶቻቸውና ውጤታማነታቸው ላይ የተወሰነ ልዩነት ሊስተዋል ይችላል፡፡ 

በሁለቱም ፆታዎች ስር በሰደዱ ህመሞች ለተጠቁ ታካሚዎች በደም ዝውውራቸው ጤናማነት ሁናቴ፣ ከችግሮቹ ጋር የተያያዘ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የደም መርጋት፣ የህመሞቹ በንቁ የህመም ደረጃ መሆንና ባለመሆን፣የእርግዝና መከላከያዎቹ የህመሞቹ መጠን ላይ ያላቸው ተጽዕኖና ስር ለሰደዱ ህመሞቹ ከሚወሰዱ መድሃኒቶች ጋር ያላቸው መስተጋብርና ተፅዕኖ ምን አይነት የእርግዝና መከላከያ አማራጮችን መውሰድ እንዳለባቸው የሚወስኑ ነገሮች ናቸው፡፡ በተለይም ሆርሞን ያላቸውና በሆርሞን የተቀነባበሩ የእርግዝና መከላከያ አማራጮች በሚወሰዱበት ጊዜ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባትና ከሃኪም ጋር በመመካከር የጎንዮሽ ችግሮች እንዳይከሰቱና የእርግዝና መካለከያዎቹም ውጤታማነት እንዳይቀንስ ማገዝ ይቻላል፡፡

☑️ ጡት ማጥባት፣ ስር የሰደዱ ህመሞችና ጤናማ የሆድ እቃ

የእናት ጡት ማጥባት ለአንድ ህፃን ካለው ሁለንተናዊ የጤና ጥቅሞች በተጨማሪ ለእናቲቱም ከወሊድ በሗላ በመጀመሪያዎቹ ወራት እርግዝና እንዳይከሰት፣ ከወሊድ በሗላ ከፍተኛ የደም መፍሰስ እንዳይከሰትና የጡት መወጠር እንዳይኖር በማድረግ ከእርሱ ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ችግሮች እንዳይከሰቱ ይካላከላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማህፀን ካንሰርንና የጡት ካንሰርን መከላከል፣የግሉኮስ ሆርሞን ስርዓትን በማስተካከል አይነት ሁለት የስኳር ህመምን መከላከል፣ በተለይም ህፃኑ የጡት ወተትን ብቻ በተናጥል በሚጠቀምበት ጊዜ ለእናቲቱ ክብደትን እንድትቀንስ በማገዝ የተለያዩ የልብና የከፍተኛ የደም ግፊት ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል፡፡

አዲስ ለተወለደው ህፃንም ከመጀመሪያዎቹ ሰዓታት አንስቶ የጡት ወተትን ማግኘቱ ለረጅም ጊዜና በጎልማሳነት እድሜ ለሚከሰቱ የደምንና የልብ ችግሮች፣ከመጠን ያለፈ ውፍረትን፣ከፍተኛ ኮሌስተሮንና የስኳር ህመምንም ቀድሞ ለመከላከል አስፈላጊ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ይገልፃሉ፡፡የእናት የጡት ወተትን በተገቢው መንገድ ያገኙ ህፃናት የሆድ እቃ ጤናም በእጅጉ የተሻሻለ ነው፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት የእናት ወተት ለጤናማ የሆድ እቃ መሰረታዊ የሆኑትን የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን እድገትና ተግባርን ስለሚያግዝ ነው፡፡

ስር በሰደዱ ህመሞች ውስጥ ላሉ እናቶች ከላይ የተጠቀሱት የጡት ማጥባት ጥቅሞች እንዳሉ ሆነው ለአንዳንድ ስር ለሰደዱ ህመሞች በሚወሰዱ መድሃኒቶች ምክንያት ጡት ማጥባት ለህፃኑ ጤና እክልን በሚያመጣበት ጊዜ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ይመከራል፡፡በመሆኑም ከጡት ማጥባት እጅግ የጎላ ጠቀሜታ አንፃር ከሃኪም ጋር በመመካከር ተገቢውን ውሳኔ መወሰን አስፈላጊ ነው፡፡  

በሚቀጥለው ሳምንት የተለያዩ ስር የሰደዱ ህመሞች መድሃኒቶችና የስነ- ተዋልዶ ጤና እንዲሁም የስነ-ተዋልዶ ጤናን ማሻሻል የምንችልባቸውን ተግባሪያዊ መንገዶች እንዳስሳለን፡፡

ይከታተሉን!

ክሮንስና ኮላይተስ ኢትዮጵያ

Source

https://www.marchofdimes.org/complications/chronic-health-conditions-and-pregnancy.aspx

Report Page