Gut Health, Reproductive Health

Gut Health, Reproductive Health

Crohn's and colitis Ethiopia

✔️ የወር አበባ ዑደት፣ ጤናማ የሆድ እቃና ስር የሰደዱ ህመሞች ግንኙነት

☞ የወር አበባ ዑደት ምንድነው?

የወር አበባ ዑደት የአንዲት ሴት ሰውነት በየወሩ ሊከሰት ለሚችል እርግዝና በሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት የተነሳ የሚፈጠሩ የተለያዩ ለውጦች ውጤት ነው፡፡ በየወሩ ኦቫሪ (የእንቁላል አቃፊ) ከተባለው የሰውነት ክፍል ኦቩሌሽን (ዑደት) በተባለ ስርዓት አንድ እንቁላል ይወጣል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የተለያዩ የሆርሞን ለውጦች ማህጸንን ለእርግዝና ያዘጋጁታል፡፡ እርግዝና ሳይከሰት ከቀረ ግን ይህ የተደረገ ዝግጅት ፈርሶ በወር አበባ መልኩ ከሰውነት ይወገድና ለሚቀጥለው ዑደት ዝግጅት ይጀመራል፡፡ ለዚህ ሂደት መከናወን አስፈላጊ ከሆኑ ሆርሞኖች ውስጥ ደግሞ ኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን ይጠቀሳሉ፡፡

☞ የወር አበባ ዑደትና ጤናማ የሆድ እቃ

 ጤናማ የሆድ እቃ ፤ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያንና በሽታ ተከላካይ ጥቃቅን ህዋሳትን ስለሚይዝ ሰውነታችንን እንደ ባክቴሪያ ፣ቫይረስና ፈንገስ ካሉ በሽታን ከሚያስከትሉብን ነገሮች ይከላከልልናል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ጤናማ የሆድ እቃ በነርቭና ሆርሞኖች አማካኝነት ከጭንቅላት ጋር ስለሚገናኝ አጠቃላይ የሰውነት ጤናችንን ለመጠበቅም ትልቅ አስተዋፆ አለው፡፡ ከዚህም ውስጥ የሰውነት ሆርሞኖች የማመንጨት፣ ማዋሃድና ማሰራጨት ሂደት ላይ ያለው አስተዋጾ ይጠቀሳል፡፡ የጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያኖቹ መዛባት ለሆርሞኖች መዛባት እንደምክንያት ሲጠቀስ፤ በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች የሆርሞኖች መዛባት ሲከሰትም ከሆድ እቃ ጋር ለተያያዙ ችግሮች ምክንያት ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ ለተስተካከለ የወር አበባ ዑደት አስፈላጊ የሆነው የኤስትሮጅን ሆርሞን መጠን ሲዛባ ከሆድ እቃ ጋር የተያያዙ እንደ የሆድ መነፋትና ቁርጠት እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው የወር አበባ መከሰትን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

☞ የወር አበባ ዑደትና ስር የሰደዱ ህመሞች 

ስር በሰደዱ ህመሞች፣ ማለትም፤ ለረጅም ጊዜ የቆዩና ቀጣይነት ያለው የህክምና ክትትል በሚፈልጉ ህመሞች ውስጥ የሚያልፉ ሴቶች የወር አበባ ዑደት እንደህመሙ ደረጃና እንደ ሰው የሰውነት ሁኔታ ይለያያል፡፡ አንዳንድ ሴቶች መደበኛውና ከወትሮው ባልተለየ ጤናማ ዑደት ውስጥ ሲያልፉ አንዳንድ ሴቶች ፣በተለይም በህመሞቹ ንቁ ደረጃ ላይ የወር አበባ ዑደት መዛባት እንዲሁም ለተወሰነ ወራት ሳይመጣ መቅረት ያጋጥማቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ የህመሞቹ ንቁ ደረጃ ላይ የወር አበባ ሲመጣ ከፍተኛ ህመም፣ ቁርጠትና በመጠን የበዛ ወይም ያነሰ ደም ሊከሰት ይችላል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ፤ ስር በሰደዱት ህመሞች ንቁ ደረጃ ላይ የሚከሰተው የሰውነት መቆጣት ፤የሰውነታችን መደበኛ የሆርሞን ስራ እንዲዛባ ምክንያት ስለሚሆን የወር አበባ ዑደትም በዚሁ ምክንያት ሊዛባ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ቀደም ሲል የተደረጉ ቀዶ ህክምናዎች፣ የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶችና ሲጋራን ማጨስም እንደምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡በወር አበባ ወቅት ስር የሰደዱት ህመሞቹ ስሜትም በተወሰነ መልኩ ጠንከር ብሎና ተባብሶ ሊከሰት ይችላል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ጠንከር ያለ የስሜት መለዋወጥ፣ ድባቴ፣ግልፍተኛነትና ብስጭት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የወር አበባ ሂደቱና የስሜቶቹም ለውጦች መጠንና አይነት እንደየህመሞቹ አይነትና የጎንዮሽ ጎዳት ሊለያይ እንደሚችል ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ 

ስለዚህ ከሃኪም ጋር በመመካከርና ክትትል በማድረግ እንዲሁም የህመሞቹን ስሜቶች ለመቆጣጠርና የእለት ተዕለት ኑሯችን በአግባቡ ከመምራት እንዳያግዱን ለመከታተል የተለያዩ ፤ እንደ፣ አስፈላጊ የሆኑ የአመጋገብ ለውጦችን ማድረግ፣ በቂ ውሃ መጠጣት፣ የሰውነት ተስተካክሎትን ለመጠበቅ ከሃኪም ጋር በመመካከር ተጨማሪ የንጥረ ነገር ያላቸው ማሟያዎች መውሰድ ፣ ባጠቃላይ አስፈላጊ የሆኑ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችን ለማድረግ መወሰን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የስሜት ለውጦቻችንን ማስተዋልና በአጠገባችን ካሉ ሰዎች እርዳታን መጠየቅም ከህመሞቹ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ድባቴና ሌሎች ችግሮችን ለመቆጣጠር ይረዱናል፡፡

የተስተካከለ የወር አበባ ዑደት መኖር የአጠቃላይ የስነ- ተዋልዶ ጤና ማሳያ እንደመሆኑ እንዲሁም በቀጣይነት ላሉ የመራቢያ አካላት ተግባር፣ ለጤናማ እርግዝና መከሰትም አስፈላጊ ስለሆነ፣ በተጨማሪ ከተዋልዶ ጤና ጋር ተያይዞ የተሟላ የአካል፣ የስሜትና የአእምሮ ጤንነት አንዱ መገለጫ እንደመሆኑ ፤ በተለይም ስር በሰደዱ ህመሞች ታካሚዎች ዘንድ አጠቃላይ የስነ-ተዋልዶን ጤና ለማረጋገጥ የወር አበባን ዑደት ተስተካክሎት መከታተል ያስፈልጋል፡፡

በቀጣይ ሳምንት በዚሁ የስነ- ተዋልዶ ርዕስ ዙሪያ ስለ እርግዝና፣ የእርግዝና መከላከያዎች፣ ጡት ማጥባትና ስር የሰደዱ ህመሞች ሰፊ ማብራሪያ ይዘን እንቀርባለን፡፡ 

ይከታተሉን !

ክሮንስና ኮላይተስ ኢትዮጵያ


Report Page