Gut Health, Reproductive Health

Gut Health, Reproductive Health

Crohn's & Colitis Ethiopia

የስነ-ተዋልዶ ሆርሞኖችና የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን 

☞ የስነ-ተዋልዶ ሆርሞኖች 

የስነ-ተዋልዶ ሆርሞኖች፤ በወንዶችና በሴቶች አጠቃላይ የስነ-ተዋልዶ ጤና፣የጉርምስና የሰውነት ለውጦች ላይ እንዲሁም በሰውነት እድገት፣ ፆታዊ ጠባይና መገለጫዎች ላይ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የሆርሞኖቹ ውቅርና ውህደት መነሻ ከተመሳሳይ ህዋስ ቢሆንም በሰውነታችን ውስጥ የሚገለጹበት መንገድና የስርጭት ሂደታቸው በስነ- ተዋልዶና በመራቢያ አካሎቻችን ውስጥ ባላቸው ሚና ላይ ይወሰናል፡፡ የስነ- ተዋልዶ ሆርሞኖች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኞቹ፤ ኤስትሮጅን/ፕሮጀስትሮን እና ቴስተስትሮን ናቸው፡፡ ኤስትሮጅን፣ ሴት ልጅ የጉርምስና እድሜ ላይ ከደረሰች በሗላ እንቁላል በእንቁላል እጢ ውስጥ እንዲዳብርና ለመራባት ዝግጁ እንዲሆን የሚሰራ ሲሆን፤ ቴስተስትሮን ሆርሞን ደግሞ በወንዶች በኩል የወንዴ ዘር/ ነባዘር እንዲዘጋጅ ያደርጋል፡፡ 

☞ የስነ-ተዋልዶ ሆርሞኖችና የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን ግንኙነት

የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን በአንጀትና በሆድ እቃ መዋቅር ላይ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ እነዚህ ተህዋሲያን የሆድ እቃን ጤናማነት ከመጠበቅ ባሻገር በርከት ባሉ የሰውነታችን ሂደቶች ውስጥም ይሳተፋሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ በሆድ እቃ ውስጥ የረቂቅ ተህዋሲያኑ ውጤትና ምርት የሰውነት አጠቃላይ ተስተካክሎ( Homeostasis) እንዲፈጠር መልዕክትን ወይም ምላሽን ለሰውነት ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የስነ- ተዋልዶ ሆርሞኖችን ስራ የማስተካከልና የመቆጣጠር ሚና አላቸው፡፡ ይህም የሚሆነው ረቂቅ ነፍሳቱ በተለያዩ ኤንዛይሞች አማካኝነት ስቴሮይዳል ሆርሞኖች የሚባሉት ሆርሞኖች ተስተካክሎን በመጠበቅ ነው፡፡ ስቴሮይዳል ሆርሞንስ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደግሞ የስነ-ተዋልዶ ሆርሞኖች( ኤስትሮጅን፣ፕሮጀስትሮን) ይካተታሉ፡፡

የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መጠን መዛባት ሲከሰትና እነዚህ ረቂቅ ተህዋሲያን ከምንመገበው ምግብ ውስጥ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች ወደ ሰውነት እንዲመጠጥ ማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ የሚከሰተው የአልሚ ምግቦች እጥረትም ለሆርሞኖች መጠን መዛባት እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡ የሆርሞኖች መዛባቱ ደግሞ በስነ-ተዋልዶ ሆርሞኖችም ላይ ይታያል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተወሰኑ ጥናቶች እንደሚገልፁት የስነ- ተዋልዶ ሆርሞኖች/ ኤስትሮጅን/ መጠን በራሱ በሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መጠንና ውቅር ላይም ተፅዕኖ እንዳላቸው ነው፡፡ ይህ ተፅዕኖ በፆታ፣በከባቢያዊ ሁኔታ፣በዘረ መልና የአመጋገብ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ 

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የስነ-ተዋልዶ ሆርሞኖች መጠን መዛባት ሲከሰት፤ በተለይም የኤስትሮጅን ሆርሞን መዛባት የተለያዩ የእርግዝና ችግሮችን፣ የማህፀን ችግሮችንና እንደ ካንሰር ያሉ ስር የሰደዱ ችግሮችንም ሊያስከትል ይችላል፡፡

☞ ስር የሰደዱ ህመሞችና የስነ-ተዋልዶ ጤና 

ስር የሰደዱ ህመሞች የሚባሉት ለረጅም ጊዜ የቆዩ ህመሞች ሆነው የእለት ተዕለት ኑሮዋችንን በአግባቡ ለመምራት እንቅፋት የሚሆኑብንና ቀጣይነት ያለው የህክምና ክትትል የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ህመሞች ውስጥ የልብ ህመም፣ የደም ግፊት፣ ስኳርና ካንሰር በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

ስር በሰደዱ ህመሞች በተጠቁ ታካሚዎች ዘንድ የስነ-ተዋልዶ ጤናቸው ከህመሞቹ ባህሪ፣ሰውነታችን ለህመሞቹ ከሚሰጠው ምላሽና ህመሞቹን ለመቆጣጠር ከሚታዘዙ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት የተነሳ በተለያየ መንገድ ይጠቃል፡፡

♦ በሴቶች ላይ፡-

 የአመጋገብ ስርዓት መዛባት፣የሰውነት እንቅስቃሴ መቀነስ፣የሰውነት ክብደት ከመጠን ባለፈ መጨመርና ሲጋራን ማጨስ ባሉ ምክንያቶች የተነሳ በርካታ ሴቶች ለተለያዩ ስር ለሰደዱ ህመሞች ይጠቃሉ፡፡ እነዚህ ህመሞች ደግሞ የሆርሞኖችን መዛባት በማስከተል ለተለያዩ የስነ-ተዋልዶ ችግሮች ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ የማህፀን ችግሮች፣የወር አበባ መዛባት፣ መካንነት፣ያለጊዜ መውለድ፣የእርግዝና መጨናገፍና በሚወለደው ህፃን ላይ የጤናን ችግር ሲያስከትሉ ይስተዋላል፡፡

♦በወንዶች ላይ፡-

ስር የሰደዱ ህመሞች በወንዶች ላይ በሚከሰቱበት ጊዜ ሰውነት ለህመሞቹ በሚሰጠው ምላሽ፣ በህመሞቹ ደረጃና በመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ምክንያት የዘገየ የመራቢ አካላት እድገት፣ የጉርምስና የሰውነት ለውጦች መዘግየት፣መካንነትና የወንድ ነባዘር እክል ሊከሰት ይችላል፡፡

በሁለቱም ፆታዎች ላይ ስር በሰደዱ ህመሞች ምክንያት የሚከሰቱትን የስነ-ተዋልዶ ችግሮች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተከታታይነት ያለው ቅድመ ምርመራዎችን ማድረግና ችግሮቹም ከተከሰቱ ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ተገቢውን የህክምና ድጋፍ ማግኘትና መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፤ በተጨማሪም ችግሮቹ ምንም እንኳ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆዩ ቢችሉም ፣ ህመሞቹን መቆጣጠር ከዚያም አልፎ መዳን እንደሚቻል በማመንና በዙሪያችን ካሉ ሰዎች እርዳታን በመጠየቅ፣የስነ ልቦና ጤናችንን መጠበቅ ይመከራል፡፡

በቀጣይ ሳምንት ስለ የወር አበባ ዑደትና ጤናማ የሆድ እቃ እንዲሁም ስለ ስር የሰደዱ ህመሞችና እርግዝና ሰፊ ማብራሪያን ይዘን እንቀርባለን፡፡ 

ይከታተሉን!

ክሮንስና ኮላይተስ ኢትዮጵያ

Source:https://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC7971312/&ved=2ahUKEwiNm7SqqaX6AhUO_hoKHVBYDjoQFnoECA0QAQ&usg=AOvVaw2RKmQCBXEsxANiyJCOqGiX

Report Page