Gut Health & Reproductive Health

Gut Health & Reproductive Health

Crohn's & Colitis Ethiopia

      ጤናማ ስነ-ተዋልዶ ምን ማለት ነው?

የስነ- ተዋልዶ ጤና

የስነ- ተዋልዶ ጤና ማለት ከተዋልዶ ጤና ጋር ተያይዞ የተሟላ የአካል፣ የስሜት፣የአዕምሮ፣ እንዲሁም የማህበራዊ ጤንነት ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የበሽታ አለመኖር ወይም የመራቢያ አካላት ተገቢውን የተግባር ሂደት መተግበር መቻልን ያካትታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሁኔታ የሚገኙ ነገሮች የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች ናቸው፡፡

የሰው ልጅ ሲሰራ ከሁለት ህዋሳት ድብልቅ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ህዋሳት ሲባዙ የምናውቃቸው የተሟሉ የሰውነት ክፍሎች ማለትም አይን፣ እጅ፣ እግር እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡በዚሁ የህዋሳት አሰራር ሂደት ውስጥም የሰው ልጅ ውጫዊና ውስጣዊ የስነ-ተዋልዶ አካላት ወይም የመራቢያ አካላት ይፈጠራሉ፡፡ የማባዛት ችሎታ የህይወት መሰረታዊ ባህሪይ እንደመሆኑ በዚሁ በስነ-ተዋልዶ ጤና ውስጥ የመራቢያ አካላት ትልቁን ስፍራ በመያዝ ተቀዳሚ ተግባር አላቸው፡፡ የእነዚህ የሰውነት ክፍሎች እና መዋቅሮች እድገትና እንቅስቃሴ ደግሞ በሆርሞኖች ይመራል፡፡ ከእነዚህም ሆርሞኖች ውስጥ ኤስትሮጅን፣ ቴስተስትሮንና ፕሮጀስትሮን ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የጤናማ ስነ-ተዋልዶና የሆድ እቃ ጤና ግንኙነት

በደፈናው የሆድ እቃችን ጤናማ ነው የምንለው እንደ የምግብ ማሳለፊያ ቱቦ፣ጨጓራና አንጀት በአንድነት በመስራት ምግብን መመገብ ስንችልና የተመገብነውን ምግብ መፍጨትና አላስፈላጊ ነገሮችን ያለ እንከን ማስወገድ ስንችል ነው፡፡ በሆድ እቃ ውስጥ ያሉ የጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መጠንና ተግባር የተስተካከለ መሆንም የሆድ እቃን ጤናማ ከሚያስብሉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡

ጤናማ የሆድ እቃ ፤ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያንና በሽታ ተከላካይ ጥቃቅን ህዋሳትን ስለሚይዝ ሰውነታችንን እንደ ባክቴሪያ ፣ቫይረስና ፈንገስ ካሉ በሽታን ከሚያስከትሉብን ነገሮች ይከላከልልናል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ጤናማ የሆድ እቃ በነርቭና ሆርሞኖች አማካኝነት ከጭንቅላት ጋር ስለሚገናኝ አጠቃላይ የሰውነት ጤናችንን ለመጠበቅም ትልቅ አስተዋፆ አለው፡፡ ከዚህም ውስጥ የሰውነት ሆርሞኖች የማመንጨት፣ ማዋሃድና ማሰራጨት ሂደት ላይ ያለው አስተዋጾ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ምክንያት የሆድ እቃ ጤናችን ከስነ- ተዋልዶና መራባት ሂደትን ጋር በቀጥታ ይገናኛል ማለት ይቻላል፡፡

Ø የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መጠን መዛባት የአንጀት ንክኪነት መጨመር የሚባለውን የአንጀት ግድግዳ ክፍተቶች ጤናማ ባልሆነ መንገድ መፍታታትና እንደ ባክቴሪያ፣ መርዞች፣ ያልተፈጩ የምግብ ቅንጣቶችና ትላልቅ ንጥረ ነገሮች በአንጀት ግድግዳዎች በኩል ወደ ደም ውስጥ እንዲገቡ ማድረግን፣ የኤስትሮጅን ሆርሞን ስራ መዛባትንና የሰውነት የበሽታን መከላከል ስርዓት መዳከምን ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ ለተለያዩ የመራባት ችግሮችና የፅንስ መጨናገፎች እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡

Ø የአንጀት ንክኪነት መጨመርና የሰውነት የበሽታን የመከላከል ስርዓት መዛባት ደግሞ ለፕሮጀስትሮን ሆርሞን መጠን መቀነስ አስተዋፆ ያደርጋል፡፡ ፕሮጀስትሮን ፣ፅንስ በውስጠ ማህፀን በተገቢው ጤና ተስተካክሎ እንዲያድግ ያደርጋል፡፡ የዚህ ሆርሞን መዛባትና መጠን መቀነስ ደግሞ የጥባቄ ፅንስን ስርዓት በማዛባት የፅንስ መጨናገፍ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡

Ø በሌላ በኩል በሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መጠን መዛባት ምክንያት የሚከሰት የሰውነት የበሽታ የመከላከል ስርዓት መዛባት፤ የፀረ የወንድ የዘር ፍሬ ፀረ እንግዳ አካላትን በመፍጠር የወንድ የዘር ፍሬ ምርትን በማጥቃት የመራባት መጠንን እጅጉን ይጎዳል፡፡

Ø የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን የኤስትሮጅን መጠንን የማስተካከል ሚናም አላቸው፡፡ የእነዚህ ረቂቅ ባክቴሪያዎች መጠን መዛባት ደግሞ ህዋሳት ከማህፀን ግድግዳ ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል በመፍለስ የውስጠ ማህፀን ችግርን በማስከተል ለተፈጠረው ፅንስና ለማህጸን አሉታዊ የተቃውሞ አፀፋዊ ምላሽን በመስጠት ለፅንስ መጨናገፍ ሊዳርግ ይችላል፡፡

በአጠቃላይ የሆድ ዕቃ ጤና ከስነ- ተዋልዶ ጤናችን ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ በማስተዋል በተለይም የሆድ እቃ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋሲያን መጠንና ጤናን ለመጠበቅ፤ የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ የሰውነት እንቅስቃሴን ማድረግና ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ተገቢውን የጤና ክትትል ማድረግ አለብን፡፡

በቀጣይ ሳምንት ስለ ስነ- ተዋልዶ ሆርሞኖችና የሆድ እቃ ጤና እንዲሁም ስለ ስር የሰደዱ ህመሞችና የስነ- ተዋልዶ ጤና ሰፊ ማብራሪያ ይዘን እንቀርባለን፡፡

ይከታተሉን!

 

Crohn's & Colitis Ethiopia

ክሮንስና ኮላይተስ ኢትዮጵያ 

  1. Source: Davis JS. Connecting female infertility to obesity, inflammation, and maternal gut dysbiosis [Internet]. Vol. 157, Endocrinology. Endocrine Society; 2016 [cited 2020 Oct 2]. p. 1725–7. Available from: https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC6285284/

Report Page