Gibi Gubae
ግቢ ጉባኤ#መኑ_ውእቱ_ገብርሔር?
#ቸር_አገልጋይ_ማነው?
#ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን አላችሁ? እኛ የክርስቶስ ባሪያ የምንሆን ወንድሞችና እህቶቻችሁ እግዚአብሔር ይመስገን ሰላም ነን?
የእግዚአብሔር ጸጋና ሠላም ጠብቆት ለናንተ ይብዛላችሁ...........
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆይ ይህ ሳምንት #ገብርሔር (#ቸር_አገልጋይ) ተብሎ የሚጠራው የዐቢይ ጾም ስድስተኛው ሳምንት ነው።
እንደምታውቁት #ገብርሔር ታማኝ እንዲሆን ያደረገው የተሰጠውን አምስት #መክሊት(ጸጋ) አትርፎ ለጌታው ስለመለሰ ነው።በጥቂቱ ታምኖ ጌታው በብዙ ሹሞታል።ወደ ጌታው ደስታም ገብቷል።
ባለሁለት ገብረ ምዕመን መክሊቱም እንደዛው።
.......ነገር ግን ባለ አንድ መክሊቱ ገብረ ሀካይ ከመሬት ቆፍሮ ቀበረው ሳያተርፍም ለጌታው መለሰ።ጌታውም አንተ ክፉና ሀኬተኛ ባሪያ አለው ከርሱ ነጥቆ ለገብርሔር ጨመረለት፤ ላለው ይጨመርለታልና።
ያም ሰው ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት እሳቱ ወደማይጠፋበት ትሉ ወደማያንቀላፋበት ቦታ ተጣለ። ምክንያቱም በጥቂቱ አልታመነምና።ባንዷ መክሊት ያልታመነ እንዴት ለአምሰት መክሊት ይታመናል።
ማለትም #ለራሱ_ያልታመነ_ሰው_እንዴት_ለሰው_ሊታመን_ይችላል?
(ማቴ25:14-31)
....በዚህ ላይ ስለታማኝነት በደንብ ማስተዋል አለብን።...
እናም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆይ እኛም ጸጋ ሆኖ ስለተሰጠቻችሁ ስለ ንጽህት ቅድስት ሐይማኖታችሁ ስለ #ተዋህዶ ትጋደሉ ዘንድ እንጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብን።(ይሁዳ1:3)
#ሐይማኖት ጸጋ ሆኖ ከባህርይ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ነው።ሐይማኖት ማመን(በልብ) ና መታመን(በተግባር) ማለት ነው።አስቀድሞ ከሰው በፊት ለ#መላዕክት ተሰጠ ከዛ ለ#አዳም ከዛ #ለኛ ተሰጠ።
ነገር ግን እዚህ ጋር አንዳንድ ነገሮችን ልናነሳላችሁ ወደድን.....
✝ #ለመላዕክት ሐይማኖት መክሊት ሲሰጣቸው ያተረፉም ያላተረፉም።ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሚካኤል #የፈጠረንን_አምላካችንን_እስክናውቅ_ድረስ_ባለንበት_ጸንተን_እንቁም አሉ አተረፉ .....ነገር ግን ሳጥናኤል #እኔ_ፈጣሪ_ነኝ በማለት ካደ እንደ ባለአንዱ መክሊት መክሊቱን ቆፍሮ ቀበራት በሀሰት ለወጣት አላተረፈም ...ጌታቸውም መጣ ተቆጣጠራቸው...ላተረፉት ወደርሱ ደስታ አስገባቸው ያላተረፉትን ደግሞ ወደ ዘላለማዊ እሳት ጣላቸው።
✝ #ለአዳምም ሐይማኖት መክሊት ጸጋ ሆና ተሰጥታው ነበር ፤ እንዴት ነው ቢሉ በነገረ ድኅነት አስተምሮ እግዚአብሔር ለአዳም ፍቅሩን በመፍጠር ገለጸለት ፤ ጌታም አዳም እርሱን ምን ያህል እንደሚወደው ና እንደሚያምነው (ሐይማኖት ማለት ነው) ያውቅ ዘንድ ዕፀ በለስን አትብላ ፤ ከበላህ የሞት ሞትን ትሞታለህ አለው።...
ሰይጣንም ወደሴቲቷ ቀረበ እግዚአብሔር ምን አላችሁ? አላት መልካሙንና ክፉውን የምታስለየውን ዕፀ በለስን አትብሉ ብሎናል አለችው። ሰይጣንም ልክ እንደሱ መክሊታቸውን እንዳያተርፉ ይፈልግ ነበርና እግዚአብሔር እኮ እናንተን አትብሉ ያላችሁ አምላክ እንዳትሆኑ እንደሱ እንዳትሆኑ ፈልጎ ነው ይቺን ዕፀ በለስ በበላችሁ ጊዜ አምላክ ትሆናላችሁ አላት ሔዋንም እግዚአብሔር ታዲያ በኛ እንዲህ የሚጨክን ከሆነ ለምን ፈጠረን? ብላ መመለስ እየቻለች እርሷ ግን አምላክነትን ሽታ በላች አዳምንም አበላቸው።
#አስተውሉ የአዳም ትልቁ ችግሩ እንደ ዲያቢሎስ በሐይማኖቱ በመክሊቱ አለማትረፉ ነው።
እንዴት ቢሉ እግዚአብሔር አዳምን አትብላ አለው ፤ ሰይጣን ብላ አለው በዚህ ሰዓት አዳም ግን ፈጣሪ ያለውን ትቶ ፍጡር ያለውን ሠማ ፤ ይህ ማለት አዳም ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ይልቅ አምኖታል ማለት ነው።
እግዚአብሔርንም ካደው ማለት ነው።ይህ ብቻ አይደለም የሠይጣንን ቃል ማመኑን እግዚአብሔርን አለማመኑን ዕፀ በለስን በመብላት(በተግባር/በመታመን) ገለጠው። እንደ ባለአንድ መክሊቱ ቆፍሮ ሐይማኖቱን ቀበረ።የአዳም ትልቁ ስህተቱ ዕፀ በለስን መብላት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን አለማመኑና አለመታዘዙ/አለመታመኑ ነው። ጌታውም ልክ እንደባለአንድ መክሊቱ እሾክና አሜኬላ ወደምታበቅል መሬት አወረደው።የሞትንም ሞት(የነፍስ ሞትን) ሞተ።
✝ #ለሁላችንም_የሐይማኖት መክሊት ተሰጥቶናል ...ወይ #ገብርሔርን ወይ #ገብረ_ሀካይን መሆን አለብን። ጌታ በዳግም ምፅዓት እንደየስራችን ይከፍለናል።
እንደ ገብርሔር ለመሆን በተሰጠን የሐይማኖት ጸጋ ማትረፍ አለብን ፤ እንደነ ቅዱስ ገብርኤል እስከ መጨረሻው ጸንተን ፤ የፈጠረንን አምላካችንን በመጠበቅ እንግዳ በሆነ ትምህርት ሳንወሰድ ፤ ሳንክድ ፤ ሳንሰንፍ ፤ ሳንተኛ ፤ በማመንና በመታመን በማትረፍ ልንቆይ ግድ ይለናል።
በጥቂቱ ልንታመን ያስፈልጋል።
#እርሱም #በጥቂቱ መታመን እንዴት ነው ቢሉ... በተዋህዶ ሐይማኖት ፍጹም ያለጥርጥር በማመን ፤ ቤተክርስቲያን አብዝቶ በመመላለስ ፤ መልካም ምግባር በማድረግ ፤ 10ቱ ትዕዛዛትን(ዘጸ 2:20) ፤
6ቱ ሕግጋተ ወንጌልን (ማቴ 5:21-43 ፤ ምግባራተ ወንጌልን(ማቴ 25:34-) ፤ የተራራው ስብከቶቹን(ማቴ5:1-) በመጠበቅ፤ በማክበር ፤ ከሥጋ ሥራ(ገላ 5:19-) ከሐጢአት በመለየት ፤ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት (ገላ5:26-) ፤ ንስሀ በመግባት ፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመብላትና በመጠጣት፤ ተዘጋጅታችሁ አትርፋችሁ ስትገኙ ነው።
ያኔ ጌታ ሲመጣ ሀይሉ ሲገለጥ ኑ የአባቴ ብሩካን አለም ሳይፈጠር ያዘጋጀሁላችሁን መንግስቴን ውረሱ ብሎ በመንግስተ ሠማይ በብዙ ይሾማችሁዋል።
ካልታመናችሁ ግን ወደዘላለማዊ እሳት ይጥላችሁዋል።ስለዚህ በመክሊታችሁ በሐይማኖታችሁ አትርፉ።
ለዚህም በሐይማኖታችሁ እስከመጨረሻው ጽኑ
እስከ መጨረሻው የሚጸናው እርሱ ይድናልና።
#ደግሞ ይህ #ቸነፈር ያልፍ ዘንድ ጸልዩ ብንሞት እንኳ ተዘጋጅተን አትርፈን ከሆነ ችግር የለውም ክብሩን እንወርሳለን።ብንሞትም ብንኖርም የእግዚአብሔር ነን።በየቀኑ የምንሰማው የቸነፈሩ ተጠቂና ሟች ቁጥር አያስደንግጠን። እናንተ ብቻ
ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ።
ወዳጆች ሆይ ጊዜው ደርሷል፤ ጌታ በቶሎ እመጣለሁ እንዳለው ሊመጣ ነው።
ታዲያ ማነው ቸር አገልጋይ(መኑ ውእቱ ገብርሔር?) ሐይማኖቱን የጠበቀ ፤ በመክሊቱ ያተረፈ፤ በጥቂቱ የታመነ ፤ ወደ ጌታው ደስታ ለመግባት የጓጓ ፤ እኮ እርሱ #ማነው?????
ያቺ ሰዓት በእግዚአብሔር ፊት የምትቆምባት ሰዓት ምን ያህል የምታስፈራ ናት።ሳያተርፉ በጌታ ፊት መቅረብ ምን ያህል ያስፈራል።
#በሉ_እንውጣ_እንውረድ አትርፈን ጌታችንን ጸንተን እንጠብቀው ረሀብ ፣ቸነፈር ፣ሰይፍ ፣ሀሰተኛ ነቢያት ፣የምድር መናወጥ፣መከራ፣ሞትም ...ሌላም ሌላም ቢሆን በአመነው ታምነን እንጠብቀው ዋጋችንን በመጣ ጊዜ ይከፍለናልና።
"...በጥቂቱ ታምነሀልና በብዙ እሾምሀለሁ..."
ይቆየን...
#ሀሳብ አስተያየታችሁን
https://t.me/gibigubaehasb_bot ላይ አድርሱን።
እግዚአብሔር ከምንሰማው ወረርሽኝ እኛንም ሀገራችንን ኢትዮጵያንም ይጠብቅልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን!!!
በትምህርታዊ ስነጽሁፍ ንዑስ ክፍል የተዘጋጀ