#GERD
በግድቡ ጉዳይ በኢትዮጵያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመመከት ዝግጁ መሆኗን ግብጽ አስታወቀች!
የዓባይ ወንዝን በተመለከተ ሀገራቸው የትኛውንም አማራጭ እንደምትጠቀምና ታሪካዊ ተጠቃሚነቷን እንደምታስቀጥል የግብጽ ፓርላማ ምክትል አፈ-ጉባኤ አስጠነቀቁ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት አሜሪካ ላይ ሊካሄድ በነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ኢትዮጵያ አለመገኘቷን ተከትሎ ግብጽ ጉዳዩን በአሉታ እየተመለከተችው ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ ሰፊ ምክክር ማድረግ እና ብሔራዊ ጥቅሟን በዘላቂነት የሚያስጠብቅ አቋም መያዝ በሚያስችላት ሐሳብ ላይ መምከርን ማስቀደም ስላለባት በድርድሩ እንደማትሳተፍ መግለጧ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎም የግብጽ ፓርላማ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሶሊማን ዋድሃን ዛቻ የተሞላበት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ምክትል አፈ-ጉባኤው ይህንን ያሉት የግብጽ ውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች ‘ኢትዮጵያ በድርድሩ ያልተገኘችው ድርድሩን ሆን ብላ ልታደናቅፍ ነው’ የሚል ሐሳብ ማሰራጨታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ባሳለፍነው ዓርብ ሊጠናቀቅ በነበረው ድርድር ሦስቱ ሀገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ታስቦ ነበር፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ሀገራዊ አቋም ለመያዝ አዲስ አበባ ላይ እያደረገች የነበረውን ውይይት ባለማጠናቀቋ በድርድሩ እንደማትገኝ ማሳወቋን ተከትሎ የታሰበው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ግብጽ በጤናማ ድርድር ሽፋን የ1929 እና የ1959 (እ.አ.አ) የቅኝ ግዛት ውሎችን ለማስፈጸም የጓጓችለት፣ በግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ሽፋን የውኃ ድርሻ ላይ የልቧን ለማድረስ ያሰበችው ድርድር ፍጻሜ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ መጀመሪ ላይ ታዛቢ፣ በኋላም አደራዳሪ ስትባል በነበረችው አሜሪካ አርቃቂነት የቀረበው ሰነድም ሳይፈረም ቀርቷል፡፡ ይህም ግብጽን ብቻ ሳይሆን አሜሪካንም ቅር አሰኝቷል፤ አቋሟም ይፋ እንዲወጣባት አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ድርድሩን ጤናማ እና የኢትዮጵን ሉዓላዊ መብት በማይዳፈር መልኩ ማስኬድ፣ ይህ ካልሆነ ግን ግድቡን ለማጠናቀቅና ለታሰበው ዓላማ ለማዋል የማንንም ፈቃድ ኢትዮጵያ እንደማትፈልግ ግልጽ አድርጓል፡፡
ይህ ነው እንግዲህ የግብጽን ተደራዳሪ ሚኒስትሮቿንም ሆነ ምክትል አፈ-ጉባኤዋን “ያዙኝ ልቀቁኝ” እያሰኛቸው የሚገኘው፡፡ በተለይም ምክትል አፈ-ጉባኤው የኢትዮጵን በውኃ ሀብቷ የመጠቀም መብት ገደል የከተተ የሚመስል ንግግር ነው ያደረጉት፡፡ “ግብጽ በዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ሥምምነቶች መሠረት ያገኘችውንና በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት ላለማጣት ሁሉንም አማራጮች ለመጠቀም ዝግጁ ናት፤ ግብጽ ብቻዋንም አይደለችም” ብለዋል ሶሊማን ዋድሃን፤ ከግብጽ ጎን እነማን እንደተሰለፉ በግልጽ ባይናገሩም፡፡ “ኢትዮጵያ በድርድሩ ያልተገኘችው በየትኛውም መንገድ ሂደቱ እንዲራዘምና የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያስችላትን ጊዜ ለመግዛት ነው” ሲሉም ትችት ሰንዝረዋል፡፡ በዛቻ በተሞላው ንግግራቸውም ግብጽ በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻዋን አንዳልሆነችና ጥቅሟን ለማስጠበቅ የትኛውንም አማራጭ እንደምትጠቀም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዘርፉ ምሁራንና የረዥም ጊዜያት ተደራዳሪዎች እንዳሉት ደግሞ ኢትዮጵያ በውኃው የመጠቀም ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብቷን የሚያሳጣ ድርድርም ስምምነትም ማድረግ የለባትም፡፡ አሁን ግብጽ የጀመረችው አካሄድም የዓባይ ወንዝን በፍትሐዊነት የመጠቀም፣ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ሳይሆን የውኃ ክፍፍል ላይ ያተኮረ አለፍ ሲልም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ እንዳትጠቀም የሚያደርግ ነው፡፡ ምክንያቱም አቋሟ “የውኃውን ተፈጥሯዊ ፍሰት በጠበቀ መልኩ ይለቀቅልኝ” የሚል በመሆኑ ነው፡፡
[አህራም ኦንላይን, አብመድ]