France Lait

France Lait


በርካታ ወላጆችን ያስጨነቀው እና ያሸበረው የ " ፍራንስ ሌይ " የህፃናት ወተት ጉዳይ ምንድነው ?


ፍራንስ ሌይ ላብራቶሪ የፈረንሳይ ኩባንያ ሲሆን " ፍራንስ ሌይ " የተባለ የህፃናት ወተቶች አምራች ነው።

ይህንን ወተት ወደ ኢትዮጵያ እያስመጣሁ አሰራጫለሁ ያለው " ዶክ ቶክ " የተባለ አስመጪና ላኪ ከሰሞኑን ከህፃናት ወተቱ ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ሀሰተኛ መረጃ ወላጆች እየተረበሹ መሆኑንና ስራውንም ላይ እክል እንደገጠመው ገልጿል።

የህፃናት ወተቶች አለም አቀፍ ደረጃቸዉን የጠበቁ በአውሮፓ ስታንዳርድ የተመረቱ የ CODEX SASO, FDA መስፈርቶችን ያሟሉ ናቸው ያለው ይኸው አስመጪ ድርጅት እነዚህ ምርቶች በአምራች ኩባንያዉ የአሰራር ሂደት መሰረት ለምርቶቹ መለያ ይሆን ዘንድ የማይቀየርና ወጥ የሆነ መለያ ቁጥር (Bar Code) የሚጠቀሙ ናቸው ብሏል።

ይህ ባር ኮድ የምርቱን ትክክለኛነትና የምርቱን አይነት (type of product and type of Sku) ለመግለፅ ይጠቅማል ፤ እንዲሁም እነዚህ የዱቄት ጣሳዎች እንደማንኛዉም ምርቶች የባች ቁጥር (Batch Number) ያላቸዉ ናቸው ይህም የምርቱን ሁኔታ ለመከታተል (Product traceability, production date and time, expire date) ይረዳል ሲል አስረድቷል።

በዚህም ባር ኮድና የምርቱ መጠቀሚያ ጊዜ መካከል ምንም አይነት ግንኙነት የለም ሁለቱም የተለያዩ መረጃዎችን ጥቅሞችን ይይዛሉ፤ አንድ ባር ኮድ የተለያዩ የባች ቁጥር እና የመጠቀሚያ ጊዜን ይይዛል ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አዲስ ብር የተባለ ድህረገፅ የ France Lai Bar Code ን ካለ ባች ቁጥሩ እንዲሁም ከአንድ አመት በፊት የነበረውን የምርቱን ዋጋና የመጠቀሚያ ጊዜ 28/07/2022 በድህረገጽ ላይ ለጥፎት የነበረ ሲሆን ይህንን እንደ ማስረጃ በመጠቀም በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ እየተሰራጨ ይገኛል ብሏል።


ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ06/08/2022 በማስጫኛ ቁጥር SMICB22000078 እና በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤት የማስገቢያ ፍቃድ ቁጥር EMHACA/22/8402/IE1 መሰረት ወደ ሀገር ውስጥ ያሰገባናቸው ምርቶች ምንም እንኳን የመጠቀሚያ ጊዜያቸው 05/24 ቢሆኑም በባር ኮድ መመሳሰል እና ከላይ የተገለፀውን ድረገፅ እንደማስረጃ በማጣቀስ በአሁን ሰአት በገብያ ላይ ያሉት ምርቶቹ የመጠቀሚያው ጊዜ ያለፈባቸውና በጣሰው ላይ የሚገኘው የመጠቀሚያ ጊዜና የባች ቁጥር ትክክለኛ አለመሆኑ በተለያዩ ማህበራዊ ድህረገጽ ላይ በመነገር ላይ ይገኛል ሲል ገልጿል።

ድርጅቱ ይህንን ጉዳይ ለኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በደብዳቤ አሳውቆ ውሳኔ እየተጠባበቀ መሆኑንና በዚህ ጉዳይ የተሳተፉ አካላትን በህግ አግባብ ክስ በመመስረት ሂደት ላይ መሆኑን አሳውቋል።

ድርጅቱ የምርቱ ደንበኞች ምርቱ በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጥራታቸውና ደህንነቶቻቸው ተረጋግጠው ወደሃገር ውስጥ የገቡ መሆናቸውን በመረዳት ያለምንም ስጋት መጠቀም እንደሚችሉ ገልጾ ስለምርቶቹ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት https://www.france-lait.com/en/ መጠቀም እንደሚችሉ ወይም በግንባር ቦሌ መድሀኒአለም ሮቤል ፕላዛ 7 ፎቅ የሚገኘዉን ቢሮ በመምጣት መረጃ ማግኘት ይችላሉ ብሏል።

(ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ተጨማሪ መረጃ ጠይቆ የሚያቀርብ ሲሆን ተቋሙ እስከሁን ስለዚህ ጉዳይ ወይም ምርቱን ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም የሚል መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገፁ አለማሰራጨቱን ለማረጋገጥ ተችሏል)

@tikvahethiopia

Report Page