Facts: Colonoscopy

Facts: Colonoscopy

Crohn's & Colitis Ethiopia

በብዙዎች ዘንድ የሚነሳው የኮሎኖስኮፒ ምርመራ ምንነት እና የህክምናው ሂደቶች

የኮሎኖስኮፒ ሂደት የታችኛውን የምግብ መፍጫ ሥርዓት በምስል ለመመርመር ረጅም እና ተጣጣፊ ቱቦ መጨረሻው ላይ ትንሽ ካሜራ ባለው መሳሪያ በመጠቀም የሚካሄድ የምርመራ ሂደት ነው ፡፡ የምግብ መፍጫ ሥርዓት (ጋስትሮኢንተሮሎጂስት) ባለሙያ (ስፔሻሊስት) የኮሎኖስኮፒ መሳሪያውን በፊንጢጣ በኩል ወደ አንጀት እንዲገባ በማድረግ በአንጀት ውስጥ ያለን ችግር ለመለየት ይጠቀመዋል፡፡

ለኮሎኖስኮፒ ምርመራ እንዴት መዘጋጀት ይቻላል?

ለኮሎኖስኮፒ ምርመራ ለመዘጋጀት ሃኪሞ የተወሰኑ መመሪያዎችን ይሰጥዎታል ፡፡ከእነዚህም መካከል በጥቂቱ፡-

  • ከምርመራው ሶስት ቀናት በፊት ጀምሮ ዝቅተኛ የፋይበር መጠን ያላቸውን ምግቦች ( እንደ ፓስታ እና መኮሮኒ) ብቻ መመገብ
  • ከምርመራው አንድ ቀን በፊት ምንም አይነት ምግብን አለመውሰድ፣ በምትኩ ሃኪሞ በሚሰጦት መመሪያ መሰረት ለምርመራው የሚፈቀዱ እንደ ውሃ ያሉ ፈሳሾችን ብቻ መውሰድ
  • ከሃኪሞ የሚሰጡ ሆድን ባዶ የሚያደርጉ እና የሚያፀዱ ቅባታማ ዘይቶችን በሚሰጠው መመሪያ መሰረት በአግባቡ መውሰድ
  • እንደ የስኳር በሽታ ፣ የልብ በሽታ ወይም የደም ግፊት ያሉ ሥር የሰደዱ ህመሞች ካሉዎት ሐኪሞችዎ መድኃኒቶችዎን በተመለከተ የሚሰጦትን ምክሮች መተግበር

በሂደቱ ወቅት

 የኮሎኖስኮፒ ሂደቱን ለማስጀመር  የሆስፒታል ቀሚስ እንዲለብሱ ይጠየቁ ይሆናል ፡፡ ብዙውን ጊዜ ማደንዘዣ ይሰጣል ፡፡ ሂደቱ ብዙውን ጊዜ እርሶ በጎንዎ ተኝተው እግሮችዎን ወደ ደረቶ በማስጠጋት ይጀምራል ፡፡ 

በፊንጢጣ በኩል መሳሪያው ከገባ በሗላ ሀኪሙ አየር በማስገባት የአንጀትን ንጣፍ እንዲሞላው ያደርጋል ፣ ይህም የአንጀት ሽፋን የተሻለ እይታ እንዲኖረው ያደርጋል ፡፡ መሳሪያው ሲዘዋወር ወይም አየር ሲገባ ፣ የሆድ መነፋት ሊሰማዎት ይችላል ፡፡

የኮሎንስኮፒ መሳሪያ ጫፉ ላይ ትንሽ የቪዲዮ ካሜራ ይይዛል ፡፡ ሃኪሞ የአንጀትዎን ውስጣዊ ክፍል ማጥናት እንዲችል ካሜራው ምስሎችን ወደ ውጫዊ መቆጣጠሪያ ይልካል ፡፡ በተጨማሪም ሐኪሙ የሕብረ ሕዋሳትን ናሙናዎች (ባዮፕሲዎችን) ለመውሰድ በኮሎኖስኮፒው ቱቦ ወደ አንጀት ውስጥ የተለየ መሳሪያን ሊያሳልፍ ይችላል፡፡

የኮሎኖስኮፒ ሂደት በተለምዶ ከ 30 እስከ 60 ደቂቃ ያህል ይወስዳል ፡፡

 

ከሂደቱ በኋላ

    ከሂደቱ በኋላ ከማደንዘዣው ማገገም ለመጀመር አንድ ሰዓት ያህል ይወስዳል ፡፡ ማደንዘዣው የሚያስከትለው ውጤት ሙሉ በሙሉ ከሰውነት እስኪጠፋ ድረስ አንድ ቀን ሊወስድ ስለሚችል ወደ ቤት የሚወስድዎ ሰው ያስፈልግዎታል ፡፡ አይንዱ ወይም አስፈላጊ ውሳኔዎችን አያድርጉ ወይም ቀኑን ሙሉ ወደ ሥራዎ አይሂዱ ፡፡

    አንጀት ውስጥ የገባው አየር ሙሉ ለሙሉ እስኪወገድ ከሂደቱ በኋላ ለጥቂት ሰዓታት የሆድ መነፋት ሊያጋጥሞ ወይም ጋዝ ሊያሳልፉ ይችላሉ ፡፡ በእግር መሄድ፣ አየርን ከሆድ ውስጥ ቶሎ ለማስወገድ ይረዳል ፡፡ እንዲሁም ከሂደቱ በኋላ በመጀመሪያ መፀዳጃ ቤት ሲፀዳዱ ትንሽ ደም ሊያዩ ይችላሉ ፡፡ ብዙውን ጊዜ ይህ አሳሳቢ አይደለም ፡፡ ደም በሰገራ ማየት ከቀጠሉ ወይም የማያቋርጥ የሆድ ህመም ወይም ትኩሳት ካለብዎ ያኔ አሳሳቢ ስለሚሆን ሐኪምዎን ያማክሩ። እምብዛም ባይሆንም ይህ ከሂደቱ በኋላ ወዲያውኑ ወይም በመጀመሪያዎቹ ቀናት ውስጥ ሊከሰት ይችላል፡፡


Crohn's & Colitis Ethiopia

 

 

 

Report Page