#FD
በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ውጭ አገር የመላክ ወንጀል የሚያስከትለዉ ተጠያቂነት!
--------------------------------------------
ከህገ ወጥ ስደት ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚደመጡት መረጃዎች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክት ነዉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ህገ ወጥ ስደትን እንደ አማራጭ በመውሰድ የሚያደርጉት ስደት የተወሰነ ጊዜ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በባህር ላይ ህይወታቸውን የሚያጡ እንዲሁም እንደ እነሊቢያ እና የመንን በመሳሰሉ አገራት ውስጥ በህገ ወጥ ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ሆነው በባርነት እስከ ማገልገል ደርሰው በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙበት ሁኔታ በመታየት ላይ ነው፡፡
ይህን የዜጎችን ህይወት እስከ መንጠቅ ደረጃ ለሚደርሰው አደገኛ ስደት በዋናነት ተጠቃሹ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የሚፈፀመው የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ዜጎችን ከሀገር ማስወጣት ወንጀል መሆኑ ቢታወቅም ነገር ግን አሁንም ድርጊቱ ከሀገር ውስጥ ጀምሮ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚያከናውኑ ደላሎች ትስስር ወንጀሉ እየተፈፀመ በመሆኑ የበርካታ ዜጎች እጣ ፈንታ በአጭሩ እየተቀጩ መቅረት እየሆነ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ውጭ አገር የመላክ ወንጀልን መፈፀም የሚያስከትለውን የህግ ተጠያቂነት በ1997ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ ላይ የተቀመጠውን እንመለከታለን፡፡
በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ውጭ አገር የመላክ ወንጀል በሚለው አንቀፅ 598(1) ማንም ሰው ፍቃድ ሳይኖረው ወይም በማናቸውም ሌላ ህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያዊ ዜጋን ለስራ ወደ ውጭ አገር የላከ እንደሆነ፤ ከ5 አመት እስከ 10 አመት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራትና 25.000 (ከሀያ አምስት ሺ ብር) በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
አንቀፅ 598(2) በዚህ ድርጊት ምክንያት የተላከችው ኢትዮጵያዊት በሰብዓዊ መብቷ፣ በህይወቷ ወይም በአካሏ ላይ ጉዳት የደረሰባት እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከ5 አመት እስከ 20 አመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከ50.000 (ከሀምሳ ሺ ብር) የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
አንቀፅ 598(3) ተመሳሳይ ድርጊት በወንዶች ኢትዮጵያውያን ላይ በሚፈፀምበት ጊዜ የዚህ አንቀፅ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
አንቀፅ 599(1) በዚህ ርዕስ እንደተደነገገው በሰዎች ነፃነት ላይ ወንጀል የተፈፀመው ማለትም ዛቻው የባርያ ሽያጩ ወይም ዝውውሩ ወይም በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላኩ የተፈፀመው በማናቸውም መንገድ በሰዎች ለመነገድ በተቋቋመ ቡድን ወይም ማህበር እንደሆነ፤ ቡድኑ ወይም ማህበሩ ፈርሶ ከ100.000 (ከአንድ መቶ ሺ ብር) በማይበልጥ መቀጮ የሚቀጣ ሲሆን ይህ ቅጣት ጥፋተኞቹ በየግላቸው ለፈፀሙት ወንጀል የሚወሰንባቸውን ቅጣት አያስቀርም፡፡
አንቀፅ 599(2) ወንጀሉን የፈፀመው የህግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት እንደሆነ፤ እንደ ወንጀሉ አይነት እና ከባድነት1997ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 90 መሰረት ይቀጣል፡፡
በዚሁ መሰረት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ዉጭ አገር የሚልኩ ማናቸዉም ግለሰቦች፣ቡድኖች ብሎም ድርጅቶች ክቡር ለሆነዉ የሰዉ ልጅ ህይወት መጥፋት ተጠያቂ ከመሆን አስቀድሞ ከህገወጥ ወንጀላቸዉ ተቆጥበዉ የግለሰቦችን ደህንነት እንዲጠበቅ የበኩላቸዉን ድርሻ መወጣት የሚገባቸዉ ሲሆን ከዛም አልፎ የአገርን ገጽታ የመጠበቅ የዉዴታ ግዴታ አድርጎ በመዉሰድ ሚናቸዉን ሊወጡ ይገባል መልእክታችን ነዉ፤ ምክንያቱም ከቅጣት በፊት ሰብአዊነት የሚቀድም በመሆኑ ሁላችንም በህገወጥ መንገድ እህት ወንድሞቻችችን ከላክን በኋላ ከሚደመጡ አሰቃቂ ዜናዎች ለመዳንና ከህሊና እዳ ነፃ ለመዉጣት ከዚህ ተግባራችን ልንቆጠብና በሰብአዊነት ልንረዳቸዉ ይገባል፡፡
FDRE Attorney General የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ