EwnetMedia10032020

EwnetMedia10032020

EwnetMedia

የኢትዮጵያ ነገሥታት፡- የኦርቶዶክስ ‹‹ምርጦች››፣ የኦሮሞ ‹‹ጠላቶች››?

✍️ ጠርዘኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን በብዙ ነጥቦች ይከሷታል፡- ‹‹ጨካኝና ጨፍጫፊ ነገሥታትን ቀብታ አንግሣለች›› በሚል፤ ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘምነገደ ይሁዳ›› የሚለውን ‹‹ሴማዊ›› ማዕርግ የምትሰጣቸው እንደ ኦሮሞ ያሉትን የኩሽ ሕዝቦች ለማሸማቀቅ እንደሆነ፤ ‹‹ኦርቶዶክስ ነገሥታቱን ቀብታ ያነገሠቻቸውን ያህል ሲያጠፉ ግን አልፈገሰጸቻቸውም፤ እንዲያውም ጥፋቱን በመባረክ ተባብራለች፤ በፖለቲካቸው ማሳለጫ መሣርያነትም አገልግላለች›› በማለት እና ‹‹ግፈኞቹን ነገሥታት ዛሬም ድረስ በጸሎተ ቅዳሴዋ ትዘክራቸዋለች›› እያሉ፡፡ 

✍️ ቤተ ክርሰቲያቱ ግን ቀብታ ‹‹ንጉሥ›› እንዲሆኑ እውቅና ሰጠቻቸው እንጂ ጨካኝ እንዲሆኑ፣ ‹‹ፈጽመው የማይበድሉ መላእክት›› አላደረገቻቸውም፤ ልታደርጋቸውም አትችልም!

✍️ የ ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ›› ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡- ‹‹ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው…በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም…›› እንዲል (ዘፍ.49፥9-10)፡፡

✍️ ‹‹ሕዝቡ ይጨፈጨፍ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታ ሰጥታለች›› ብሎ ለመደምደም ከሳሾቿም ቢሆኑ የተጨበጠ ማስረጃ አላቀረቡም፣ ምስክርም አልቆጠሩም፡፡ ኦርቶዶክስ ብሔራዊ ሃይማኖት ስለነበረች፣ ነገሥታቱ የሃይማኖቱ ተከታዮች ስለነበሩ ‹‹ይህንን ሳታደርግ አትቀርም›› የሚል ተራ የግምት ክስን እንዳለ ተቀብሎ ምላሽ ፍለጋ መኳተን ግን ከንቱ ድካም ነው!

✍️ ነገሥታቱ መበደላቸው እውን ከሆነ ‹‹ለምን በጸሎት ይዘከራሉ?›› አይባልም፤ የቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮም ‹‹ኃጢአት በበዛችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች›› ነውና ይልቁን ለእነርሱ መጸለይ ይገባልና!

 (ለተሻለ ግንዛቤ ሙሉውን ያንብቡት፤ ጽሑፉን #Share ቢያደርጉ ደግሞ ሌሎችንም ይጠቅማሉ!)

`````````````````````````````````````````````````````````````````````

የቤተ ክህነቱ (ሃይማኖት) እና ቤተ መንግሥቱ (ነገሥታት) ግንኙነት በብዙ ፈርጁ የሚታይ ነው፤ በአዎንታዊም፣ በአሉታዊም፡፡ ከእነዚህ ገጽታዎች ወደ አንደኛው ጠርዝ ለማጋደል አልያም ሁለቱን በሚያማክል መልኩ ለመዳኘት ግን ነገሮችን ቆመን የምናይበት ቦታና መነጽር ይወስነዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ በተለይ የኦሮሞ ጠርዘኛ ፖለቲከኞች በቀደምት የሀገሪቱ ነገሥታት ላይ በሚሰነዝሯቸው ክሶች ላይ የሚያተኩር ነው፡- በዋናነት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእነርሱ ጋር ወግና የኦሮሞን ሕዝብ ስትበድል እንደኖረች የሚያራግቡትን ማስቃኘት፡፡ እናም ነገሥታቱን ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በሚያገናኟቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር እንቀጥል፡-  

1. ‹‹ጨካኝና ጨፍጫፊ ነገሥታትን ቀብታ አንግሣለች›› 

አንዳንድ ጠርዘኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የጥንቱን ቅብዓ ሜሮን አጥብቀው ሲኮንኑ ይስተዋላሉ፤ ‹‹ጨካኝና ጨፍጫፊ ነገሥታትን ቀብታ አንግሣለች›› በሚል፡፡ እውነት ነው በመጽሐፍ ቅዱሱ መሠረት፣ እነ ነቢዩ ሳሙኤል እነ ዳዊትን ቀብተው ለንግሥና መንበር ባበቁበት አብነት መሠረት (1ሳሙ.16፥13) ቀብታ አንግሣቸዋለች፤ በወቅቱ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት የምትችል ተቋም እርሷ ብቻ ስለነበረች፡፡ በገዳ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥም የአባ ሙዳ (ቃሉ) ድርሻው የብሔረሰቡን ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ማስፈጸምና ለአባ ገዳዎች ‹‹ቁምቢ›› የተሰኘውን ቅዱስ ምግብ አብልቶ ሕዝቡን በርትዕ እንዲያስተዳድሩ ቃል ማስገባት እንደነበር መዘንጋት የለበትም፡፡ 

በተመሳሳይ መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱም ይህን ስታደርግ ቅብዐ መንግሥቱም ‹‹ቅዱስ›› ነውና ሕዝቡን በቅድስና (ያለ ግፍና ጭቆና) እንዲመሩ እንጂ ‹‹ጨፍጫፊ›› እንዲሆኑ አልነበረም፡፡ እንኳንስ ነገሥታቱ ቅብዐ ሜሮን ተቀብተው አመጸኛ መሆን ይቅርና ምዕመናንም የታላቁን ወልደ እግዚአብሔር ሥጋና ደም ተቀብለው በምድር ሰዎችን፣ በሰማይም እግዚአብሔርን ይበድላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ችግሩ የቁርባኑም የአቁራቢ ካህናቱም ችግር ተብሎ አይጠቀስም፤ የራሳቸው የቆራቢዎቹ በምግባር፣ በሃይማኖት አለመጽናት እንጂ፡፡ እንደዚሁ ቤተ ክርሰቲያቱም ቀብታ ‹‹ንጉሥ›› እንዲሆኑ እውቅና ሰጠቻቸው እንጂ ‹‹ፈጽመው የማይበድሉ መላእክት›› አላደረገቻቸውም፤ ልታደርጋቸውም አትችልም፡፡

በዚሁ አግባብ በዚህ ጽሑፍ ሊገለጹ የማይችሉ በርካታ የጭካኔ ተግባራት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ብቻም ሣይሆን በሌሎችም ብሔረሰቦች ላይ ደርሰዋል፡፡ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ የሰውነት ክፍላቸው ጎድሏል፤ እጅና እግራቸው ታስሮ ከአምባ ተራራ ላይ ጭምር በጭካኔ እንዲወረወሩ ተደርገዋል፤ ከነ ነፍሳቸው በእሳት እንዲጋዩም የተደረጉባቸው ክስተቶች ነበሩ፤ እነዚህን መካድ አይቻልም፡፡ ልዩነቱ ያለው ይህ ግፍ የደረሰበት ሕዝብ ‹‹ኦሮሞ ብቻ ነው›› የሚል ሲኖርና ነገሥታቱ ይህንን ያደረጉት ፖለቲከኞቹ እንደሚገልጹት ‹‹በዘር ላይ ተመርኩዘው ነው›› የሚል ድምዳሜ ሲኖር ነው፡፡ 

በቅዱስ መጽሐፋችንም ተመሳሳይ ታሪኮች እናገኛለን፡- በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በእደ ነቢያት ቅዱሳን፣ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከነገሡ በኋላ እግዚአብሔር አምላካቸውን፣ እስራኤል ሕዝባቸውን በድለው ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህልም አባትና ልጅ ነገሥታት ዳዊትንና ሰሎሞንን መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ለንግሥና ይቀቡ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቃዱን በግልጽ ተናግሯል፤ ቅብዐ ዘይቱም በእርሱ ጥበብ የተቀመመ ነውና እንከን አልነበረውም፤ ቀቢዎቹም በራሱ በባለቤቱ የተመሰከረላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ፤ ሰዎቹ በተቀቡበት ቅጽበትም እግዚአብሔርን በሚያስደስት ቁመና ላይ ነበሩ፡፡ ሰዎች ናቸውና ከጊዜ በኋላ ግን በድለዋል! በበደላቸው ምክንያት ግን ተጠያቂ የተደረጉት ራሳቸው እንጂ ትእዛዝ ሰጪው እግዚአብሔር፣ ቅብዐቱና የቀቧቸው ሰዎች አልነበሩም፡፡ በዚሁ አግባብ በኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት እጅ ቅብዐ ሜሮን ተቀብተው ሳለ ፍርድ ያጓደሉ፣ ድሃ የበደሉ ነገሥታት ሲኖሩ ‹‹ጨካኝና ግፈኛ ነገሥታትን ቀብታ ያነገሠችው ኦርቶዶክስ ስለሆነች›› ብሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ማቄም ጤነኛነት አይሆንም!

ቀድሞ ነገር ትክክለኛ ሚናዋና ሥልጣኗ ምን ድረስ ነበር? የሚለውም ነጥብ ከዚሁ ጋር አብሮ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ ‹‹አልቀባም›› የማለት ሥልጣን ፈጽሞ አልነበራትም! ከዚያ በኋላም ነገሥታቱ ለሚፈጽሟቸው ስህተቶች እርሷን ከለላ አድርገዋት ይሆናል እንጂ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ ተጠያቂ የምትሆንባቸው አግባቦች እምብዛም ናቸው፡፡ ምንም እንኳ በዘመኑ የነበሩ መሪዎች የዚህች ሃይማኖት ተከታዮች ስለነበሩ ኦርቶዶክስን እንደ ፖለቲካዊ መሣርያ አልተጠቀሙባትም የሚል ሙሉ ድምዳሜ ሊኖር ባይችልም ይህ የሃይማኖቲቱ ተልእኮ እንዳልነበረ፣ እንዳልሆነ፣ ሊሆንም እንደማይችል ግን ሁሉም ሊያውቅ ይገባል፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ሃይማኖትና ‹‹ሃይማኖተኞች›› (ተከታዮቹ) የተለያዩ መሆናቸውን ነው፤ የሃይማኖት ተከታዮች እንደ ሃይማኖቱ ቃል መኖር ሲያቅታቸው ሃይማኖቱ ራሱ እንደ እነርሱ ቃልና ፍላጎት እንዲመራ ሊያደርጉ ይችላሉና፤ አድርገዋልም፡፡ 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እኮ ‹‹ሰዎች›› እና ‹‹መላእክት›› ያገለግሉባታል፣ ይገለገሉባታልም፡፡ ይህ እውነታ ሁለት ዓይነት ‹‹አካላዊ›› ማንነቶችን ብቻ ሣይሆን ‹‹በስህተት የተሞሉ›› እና ‹‹የማይሳሳቱ›› ሁለቱም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መኖራቸውን ጭምር ይነግረናል፡፡ ዳሩ ‹‹በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል›› (ኢሳ.52፥5፤ ሕዝ.36፥20፤ ሮሜ.2፥24) የተባለው ሆነና ኦርቶዶክስ በትውልድ እንድትነቀፍ ሆነ እንጂ ሃይማኖቲቱስ እንከን አልባ ነበረች፡፡ ‹‹እንከን አልባ›› ስንልም ‹‹ሁሉም ሊቀበላት የተገባ›› ለማለት አይደለም፤ ማንም ቢሆን መዝኖና እና አመዛዝኖ እንጂ ሃይማኖትን ያህል ትልቅ የሕይወት መሥመር በደመ ነፍሳዊ ውሳኔ የሚከተል የለምና፡፡ ለማለት የተፈለገው ግን በ ‹‹መንገደኞች›› ስህተት ምክንያት ‹‹መንገዱ›› ጠመዝማዛ ነው፣ ድጥና ማጥ አለበት፣ አያስኬድም፣ ወደ ገደል ይመራል እየተባለ በአፍም በመጣፍም የመወንጀሉ አካሄድ የሰለጠነ አካሄድ አለመሆኑን ነው፡፡  

2. ‹‹የ ‹ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ› ማዕረግ ለኩሽ ሕዝብ ምኑ ነው?››

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከነገሥታት ጋር ተያይዞ የምትወቀሰው ሥርዓተ ሢመት በመፈጸሟ ብቻም አይደለም፤ በሢመቱ ማዕርግ ስያሜ ጭምር እንጂ፡፡ በጠርዘኛ ፖለቲከኞቹ አስተሳሰብ ሰሎሞናዊው ማዕርግ ‹‹ሴማዊ›› ስለሆነ እንደ ኦሮሞ ያሉትን የኩሽ ሕዝቦች በዚህ ማዕርግ ለማስተዳደር መሞከር ማለት ከቅኝ ግዛት እንደማይተናነስ አድርገው ያስወራሉ፡፡ 

በተለይ አጼ ይኵኖ አምላክ በነገሠ ጊዜ የዛጉዌን ሥርወ መንግሥት ማክተምና የሰሎሞን ሥርወምንግሥት ማንሰራራት ሂደት አንዳንዶች ‹‹ጥቁሮች ለነጮች እጅ የሰጡበት ታሪካዊ ስህተት›› አድርገው ዘግበዋል፡- ‹‹ይኩኖ አምላክ የመጀመርያው (ቀዳማዊው) ሰለሞናዊ ንጉሥ ነኝ በማለት የዘር ግንዱ ከቤተ እሥራኤል ከንጉሥ ሰለሞን እንደሆነ አስታወቀ…(ከዚያን ጊዜ ጀምሮ) የአብሲኒያውያን ነገሥታት ጥቁርነታቸውን ክደው በነጮች መንበር መመካት ጀመሩ›› [ትኩረት የራሴ] እንዲል (ኃሮ ቢያንሣ፤ ኦሮምያ፤ 1985፣ ገጽ.62)፡፡ ይኸው ጸሐፊ ‹‹የክብረ ነገሥት ዋነኛ ተልዕኮ የቀዳማዊ ምኒልክን ከሰሎሞንና ከማክዳ መወለድ አፈታሪክ (ተረት) በመጠቀም አብሲኒያውያን በእግዚአብሔር የተመረጡና ዕጣ ፈንታቸው ሌሎችን ሕዝቦች እንዲገዙ መሆኑን ማብሰር ነው፡፡›› ሲልም ይተቻል (ገጽ.63)፡፡

በመሠረቱ የ ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ›› አገላለጽ ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ከዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች መካከል ‹‹አንበሳ›› የሚል የተቀጸለለት፣ የንግሥና መሥመርም የተነገረለት ይሁዳ ነው፡- ‹‹ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው…በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም…›› እንዲል (ዘፍ.49፥9-10)፡፡ አንበሳ የአሸናፊነት፣ የግርማ ሞገስ አምሳያ ነው፡፡ ከአንበሳ አሸናፊነትን፣ ከነገድ ይሁዳን ጠቅሰው በትረ መንግሥትን የመጨበጥ ወጉ ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ 

ያዕቆብ ልጆቹን ሲባርክ ከሁሉም ለይቶ የንግሥናን በትር ለይሁዳ መስጠቱ አንድ ልጁ ብቻ ‹‹ሴማዊ››፣ ሌሎቹ ግን ‹‹ኩሻዊ›› ስለሆኑ እንዳልነበር ይታወቃል፤ ሁሉም የአንድ አባት ልጆች (ሴማውያን) ነበሩና፡፡ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ነገሥታትም የንግሥና መንበራቸውን ከይሁዳ መሥመር ጋር የሚያያይዙት ፖለቲከኞቹ እንደሚያወሩት የራሳቸውን ሕዝብ ንቀው ሌላውን ሕዝብ (እስራኤላዊነትን) ለመምሰል አይደለም፤ ከስሙም ባሻገር ለግብሩ በሚመጥን አካሄድ እንዲያስተዳድሩ ጭምር ነበር እንጂ፡፡ 

ይኸው ንግሥና በቅዱስ ዳዊት አማካይነት ደግሞ በግዘፍ ታውቋል፤ እሳቤውም ወደ ሐዲስ ኪዳን ሲሻገር ከይሁዳ (ከሰው ልጆች ሁሉ አልፎ) ለአማናዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመስጥሮ ነው፡- ‹‹እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ…›› እንዲል (ራእ.22፡16)፡፡ ‹‹የዳዊት ዘር›› የሚለውም በዋናነት የልደትን ዘር ሐርግ ሳይሆን አማናዊ ገዥነትን የሚገልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ነገሥታትም ራሳቸውን ‹‹ከይሁዳ ነገድ የሆነ አሸናፊው አንበሳ›› በሚል ራሳቸውን ሲጠሩ ‹‹በፈቃደ እግዚአብሔር ለዙፋን በቅተናል›› ማለትን እንደሚያዘወትሩ ልብ ይሏል፡፡  

መረሳት የሌለበት ሌላኛው ነጥብ ግን ምንም እንኳን ከእስራኤላዊነት ጋር መተሳሰሩ እንዳለ ቢሆንም ሁሉም የኢትዮጵያ ነገሥታት ግን ይህንን ስመ ማዕርግ እንደማይጠቀሙ ነው፡፡ ከቅርቦቹ እንኳን ስንመለከት ዐጼ ቴዎድሮስ ‹‹ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ››፣ ዐጼ ዮሐንስ ‹‹ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን›› በሚል ራሳቸውን ሲጠሩ የነበረ ሲሆን ይህንን ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ›› ስያሜ የጀመሩት ዐጼ ምኒልክ መሆናቸውን ከእያንዳንዳቸው ማኅተምና ደብዳቤዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ 

3. ‹‹ነገሥታቱ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ላካሄዱት ጦርነት ይሁንታ ሰጥታለች፤ በዋና መሣርያነት አገልግላለች››

ምንም እንኳን የተጨበጠ ማስረጃ ባያቀርቡም፡- ‹‹ኦርቶዶክስ ነገሥታቱን ቀብታ ያነገሠቻቸውን ያህል ሲያጠፉ ግን አልፈገሰጸቻቸውም፤ እንዲያውም ጥፋቱን በመባረክ ተባብራለች፤ በፖለቲካቸው ማሳለጫ መሣርያነትም አገልግላለች›› የሚለው የጠርዘኛ ፖለቲከኞቹ ሌላኛው ክስ ነው፡፡ የነገሥታቱ ቀኝ እጅ ሆና የኦሮሞን ሕዝብ እንዳስጨፈጨፈች፣ ለቅኝ ቅዛትና ለባርነት እንደዳረገችው፣ በአጠቃላይ የነገሥታቱ የፖለቲካ ማሳለጫ መሣርያ ሆና እንዳለገለገለች በብዛት ጽፈዋል፡፡ 

3.1. ‹‹ለነፍጠኞች ፖለቲካ ማሳለጫ በመሣርያነት አገልግላለች›› 

አንዳንድ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ግንኙነት በራሳቸው ባህል መነጽርነት እየተመለከቱ፡- ‹‹ልክ አውሮፓውያን አፍሪካውያንን ቅኝ እንደገዙት ሁሉ እንደዚሁ አቢሲኒያውያንም [አማራና ትግራይ] በሌሎች ሕዝቦች [እንደ ኦሮሞ ባሉት] ላይ ፈጽመዋል›› ሲሉ ጽፈዋል (Baxter, P.T.W.(1994: 172)፡፡ 

በርካታ ጠርዘኛ ፖለቲከኞችና ‹‹የኦሮሞ ታሪክ›› ጸሐፊዎችም ይኸንኑ አገላለጽ ተቀብለው በማስተጋባት፡- ‹‹ኦርቶዶክስ ለአብሲኒያ ነገሥታት የቅኝ ገዢነት መሣርያ በመሆን ኦሮሞን እንዲገዙ ሁኔታዎችን አመቻችታለች›› ሲሉ ይከሷታል፡፡ አንዳንዶችም ‹‹የገዢዎቹ በትር›› በመሆን የኦሮሞን ሕዝብ ስታጠቃ እንደነበር ጽፈዋል (Misgaanuu Gulummaa Irranaa; Guboo seenaa; 2012 A.L.Aw.; f.55).

ምንም እንኳን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ግንባታ የማይተካ ሚና የነበራት ቢሆንም ይኸ ውለታዋ ተዘንግቶ፣ ‹‹ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ›› በሚያስብል ሁኔታ ከነገሥታቱ አስተዳደር ጋር እያሳከሩ የሚወቅሷት ቀላል አይደሉም፡፡ ለምሳሌም፡- 

‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቤተ ክህነት የአማራ ገዥ መደብ ልሳንና አእምሮ በመሆን ወደር የለሽ ሚና ተጫውታለች፡፡ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ዋነኛ አጋፋሪ በመሆን መሪዎችን መርታለች፡፡ ዐፄ ምኒልክ ወደ ደቡብ ለመስፋፋት ከተጠቀሙባቸው መሣርያዎች መካከል የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ዋንኛዋ ነበረች፡፡… በታሪክም ሆነ በየወቅቱ የፖለቲካ ድራማዎች ውስጥ በስፋት እንደታየው የአበሻ ገዥ መደብ አባላት የኢትዮጵያን ኢምፓየር የፈጠሩት በሦስት ተደጋጋፊ መሣርያዎች በመጠቀም ነበር፡፡ እነርሱም ዘውድ፣ ጦር ሠራዊትና ቤተ ክህነት ነበሩ›› እንደተባለ (ኦሮሚያ የተደበቀው የግፍ ታሪክ፤ ወልደ ዮሐንስ ወርቅነህና ገመቹ መልካ፤ 1986፡22)

3.2. ‹‹ነገሥታቱ በኦሮሞ ላይ ላካሄዱት ጦርነቶች ቡራኬ ሰጥታለች›› 

በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ተከስተው ያለፉትን ግጭቶች ‹‹በሁለት ጠላቶች መካከል የተካሄደ ጦርነት›› አስመስሎ ማራገብ የዘመናችን ጠርዘኛ ፖለቲከኞች ጠባይ ሆኗል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ቀደምት የሀገሪቱ ነገሥታት ሕዝቡን ወደ አንድነት ለማሰባሰብ ያደረጓቸውንም ጥረቶች እንደ ‹‹ቅኝ ግዛት›› አድርገው ይገልጻሉ፡፡ በነገሥታቱ ላይ አላግባብ የሚሰነዝሯቸው ትችቶች ሳያንስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በሕዝቡ ላይ ያወጁትን ጦርነት በይፋ ባርካ እንዳሰማራች አድርገው ከመግለጻቸውም በላይ የገለጹበት መንገድ በወቅቱ ቆመው ሲታዘቡ የነበሩ ‹‹የዓይን ምስክሮች›› በሚያስመስላቸው መልኩ መሆኑ ያስተዛዝባል፡- ‹‹የሀበሻ ነገሥታት የኦሮሞን ሀገር ለመውረር ጦርነት ሲያካሂዱ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ሲያርዱ፣ እንደ በግም ወደ ገበያ ወስደው ሲሸጡ፣ ቤታቸውንም ሲያቃጥሉ….የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት ‹በስመ አብ…› ብለው መሣርያዎቻቸውን ይባርኩላቸው ነበር፤ ታቦት ተሸክመውም ይከተሏቸው ነበር…›› ብለዋልና (Misgaanuu, Guboo seenaa; 2012:53) ፡፡  

አንድ በግልጽ መለየት ያለብን ጉዳይ አለ፡- ነገሥታቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ተገን አድርገው ሕዝቡን መደበላቸውንና ቤተ ክርስቲያኒቱ ይሁንታ ሰጥታለች የሚባለውን፡፡ በመጀመርያው ነጥብ ላይ ያን ያህል መነታረክ አያስፈልግም፡- ነገሥታቱ ይህንን ለማድረጋቸው በርካታ ጠቋሚ ነገሮች ከመኖራቸውም በላይ ለነገሥታቱ ድርጊት ጥብቅና መቆም የጽሑፋችንም ትኩረት ስላልሆነ፡፡ ‹‹ሕዝቡ ይጨፈጨፍ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታ ሰጥታለች›› ብሎ ለመደምደም ግን ከሳሾቿም ቢሆኑ የተጨበጠ ማስረጃ አላቀረቡም፣ ምስክርም አልቆጠሩም፡፡ ኦርቶዶክስ ብሔራዊ ሃይማኖት ስለነበረች፣ ነገሥታቱ የሃይማኖቱ ተከታዮች ስለነበሩ ‹‹ይህንን ሳታደርግ አትቀርም›› የሚል ተራ የግምት ክስን እንዳለ ተቀብሎ ምላሽ ፍለጋ መኳተን ግን አስፈላጊ አይደለም፡፡ 

በእርግጥ ‹‹ይሁንታ ባትሰጥ ኖሮ ሲበድሉ ለምን አልገሠጸቻቸውም?›› የሚለው በአንጻራዊነት ሚዛን ሊደፋ ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ታዲያ በሁለት አቅጣጫዎች የሚታይ ነው፡- በአንድ በኩል ‹‹ፈጽሞ አልገሠጸቻቸውም›› ብሎ ከመደምደም ይህንን ኃላፊነቷን የተወጣችባቸውን ኩነቶች አጥብቆ ማሰስ ይጠይቃል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይህንን ባታደርግ እንኳን ሊገርመን አይገባም፡- ሌላው ቀርቶ ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣ ማግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን መሪ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ሲያግዝና በግፍ ሲገድል እንኳን ድርጊቱን ተቃውማ ድምጽዋን ስለማሰማቷ እስካሁን አልተሰማምና፡፡ ይህ ባህሏ በቀደሙት ጊዜያትም ከነበረ ደግሞ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ በሀገሪቱ በተከሰቱ አለመረጋጋቶች ውስጥም የቤተ ክርስቲያኒቱ አበው በጥብዐት መንፈስ አጥፊውን የገሠጹባቸው ሁኔታዎች አናሳ ናቸው፤ አልያም አልነበሩም ብሎ ለመደምደም ይቻል ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ የመሪዎቹን ድክመት እንጂ የሃይማኖቷን ሕጹጽነት የሚያመላክት ሊሆን አይችልም፡፡  

4. ‹‹ግፈኞቹን አጼዎች ዛሬም በጸሎቷ ትዘክራቸዋለች››

ድሪቢ ደምሴ የተባሉ የብሔሩ ፖለቲከኛ፡- ‹‹የሐበሻ ቄሶች ምሁሮቻችንና ሕዝባችንን የሚገድሉ ነገሥታትን ቀብተው በማንገሥ የአንድ ብሔር የበላይነት እንዲሰፍን ይጸልያሉ…እኛም ስለ ንጉሦቻቸው ፈጣሪን እንድንለምን…ያስገድዱናል›› ሲል ጽፈዋል (Dirribii Damissee Bokkuu; Ilaalcha Oromoo; Barroo Aadaa, seenaafi Amantaa Oromoo; 2009/2016፡130)፡፡ የዚህ ግለሰብ አስተሳሰብ ዛሬ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ውስጥ ባሉት የብሔሩ ተወላጆች ዘንድ እንኳን ተጋብቶ ‹‹የነገሥታቱ ስም እየተጠራ የሚጸለይበትን ቅዳሴ ለምን እናስቀድሳለን?›› ወደማለት አድርሶአቸዋል፡፡ እውነትም ትውልዱ ትምህርት ቤት ሲሄድ ‹‹ጭራቆች›› እንደሆኑ የተነገሩትን የኢትዮጵያ ነገሥታት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ግን ስማቸው እየተጠራ ሲጸለይላቸው አእምሮው ቢታወክ ሊገርመን አይገባም፡፡ 

እውነት ነው፡- ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ድረስ ነገሥታቱ የዋሉባትን ሤራዎች መርሳትን፣ የዋሉላትን ቁምነገሮች ግን ማስታወስን መርጣለች፤ ጋብቻውን ለማጽናት ሳይሆን የጥንቱን አብሮነታቸውን ላለመዘንጋት፡፡ ደግሞም፡- ‹‹ኃጢአት በበዛችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች›› በሚለው አስተምሕሮዋ (ውዳሴ ማርያም፤ ዘሰኑይ) መሠረት ‹‹በድለዋል›› በተባለው መሠረት እንኳን ቢሆን ይልቁን ለእነርሱ መጸለይ ይገባልና ዛሬም በጸሎቷ ሁሉ ትዘክራቸዋለች፡፡ በየመጻሕፍቱ (የጸሎት፣ ገድላትና ድርሳናት) መጀመርያና መጨረሻ ላይ ስመ ንግሥናቸውን መጥራት፤ በየጸሎተ ቅዳሴዋና ጸሎተ ፍትሐታቱ ስማቸውን መጥራቷ አልቀረም፡፡ ይህንኑ ስታደርግ ታዲያ በሀገሪቱ ውስጥ ካለው ነባራዊ የፖለቲካ ማሕቀፍ ጋር ላለመጋጨት ስትል በጥበብ የተጓዘችባቸው ሂደቶችም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ፡- ቀድሞውን በቅዳሴዋ ‹‹ጸግዎ ሰላመ ለንጉሥነ ኃ/ሥላሴ›› ትል የነበረውን ንጉሡ ከዙፋን ሲወርዱ ግን ‹‹ጸግዋ ሰላመ ለሃገሪትነ ኢትዮጵያ›› በሚል ቀይራ ከደርግ ዱላ ተሰውራለች፤ የንጉሡን ስም በደርግ (መንግሥቱ ኃ/ማርያም) ቀይራ ብታዜመው ኖሮ ግን ‹‹አሽቃባጭ›› ሊያሰኛት ይችል እንደነበር አያጠራጥርም፡፡ 

በመሠረቱ ይህንን የምታደርገው የኢትዮጵያ መሪዎችና ነገሥታት ስለሆኑ ብቻ አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዳሴ ጸሎቷ የምታስባቸው እስከ አጼ ኃ/ሥላሴ ያሉትን ብቻ ስለሆነ (በእርግጥ በደርግ ያቋረጠችውን ዝክረ ስመ-መንግሥት አቶ መለስ ሲሞቱና በቅጽሯ ሲቀበሩ ‹‹ኦ አእርፍ ለነፍሰ መራኄ መንግሥትነ ገብረ ማርያም›› ብላ ነበር)፡፡ በእርግጥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎቷ ላይ የአጼ ቴዎድሮስን ስም አትጠራም ነበር፤ በድርጊታቸው ተቀይማ ሳይሆን ራሱን የገደለ ሰው ጸሎተ ፍትሃት እንደማይከናወንለት ሥርዓት ስላላት (ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፤ እነሆ ጀግና፤ 4ኛ እትም፤ 2010፡18)፡፡ ይልቁንም እነዚህ (ይበድሉም ያቅኑም እንጂ) በእጇ የተቀቡ፣ ስመ ክርስትና ያላቸው (እና በተግባር እንዲታወቅላቸውም ያደረጉ) ስለሆኑ ነው፡፡ በዘመነ ንግሥናቸው ምንም እንኳን ‹‹እንከን አልነበራቸውም›› ባይባልም ከእነዚህ የተሳሳተ ምግባራቸው ባሻገር ቢያንስ በተዋሕዶ ሃይማኖታቸው የጸኑ፣ ለሃይማኖቲቱም መስፋፋት የተጉ፣ ከራሳቸው ዜና መዋዕላት አልፈው አያሌ የሃይማኖት እና የታሪክ ድርሳናትን ያስጻፉ/ለትውልድ ያበረከቱ፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጹ እና ገዳማትንም ያስገደሙ በመሆናቸው ለእነዚህ አዎንታዊ ተግባራቸው ሲባል ስማቸው ተጠርቶ በጸሎት እንዲታወሱ ይደረጋል፡፡ 

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ! 

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia 

#ጽሑፎቻችንን በተሻለ ጥራት ለማንበብ #ድረ_ገጻችንን https://ewnet.org/ ይጎብኙ! 

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


Report Page