EwnetMedia 2023

EwnetMedia 2023

EwnetMedia

የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር፦ ከእውቀት የጸዳ ወይስ ከንቀት የተነሳ?!

(ከታከለ ምትኩ ፌስቡክ ፔጅ የተወሰደ https://www.facebook.com/695349046/posts/10160921074894047/)

ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ/ም በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጠ/ሚንስትሩ እንደተለመደው እሳቸው ብቻ ተናግረው ለተከታታይ ጥያቄዎች እድል ሳይሰጡ ተመልሰዋል። ቤተ ክርስቲያናችንን እና ምእመናኑን ያስቆጣው የቀኖና ጥሰት የተከናወነው በመንግሥት እገዛ መሆኑን በሚያመላክት ሁኔታ በደንብ ሳይጠቅሱት አልፈዋል። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦሮሚኛ ቋንቋ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ አገልግሎት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳልተሰጠ በሚመስል መልኩ እና የእነዚያን ቡድን የውሸት ትርክት በሚደግፍ ሁኔታ ሃሳባቸውን ሲያቀርቡ ተሰምቷል። ይህም ከእውቀት ማነስ ይሁን ከንቀት የተነሳ መሆኑን የሚያውቁት እርሳቸው ብቻ ናቸው። በክልሉ ተወልዶ እንዳደገ አንድ ሰው ይሄ ዓይነት ንግግር ችግሩን የበለጠ ካላባባሰው በቀር መፍትሔ አይሆንም ብዬ አስባለሁ።

በቤተ ክርስቲያን ታርክ ከግእዝ ቋንቋ ውጪ አማርኛ ቋንቋ እንኳ ወደአገልግሎት የገባው በቅርብ ጊዜ ነው። እንዲያም ሁኖ ከ20 ዓመታት በፊት በ2003 ዓ/ም ወለጋ፣ ነጆ ከተማ በሥራ ምክንያት ለወራት በቆየውባቸው ጊዜያት ቅዳሴው በግእዝና በአፋን ኦሮሞ ነው። የ”አባታችን ሆይ ጸሎት”ን በአፋን ኦሮሞ የተማርኩት እንኳ ያኔ ነበር። መዝሙር ይቀርብ የነበረው በዋናነት በአፋን ኦሮሞ ነው። በሁለተኛ ደረጃም በቤተ ክርስቲያን ቋንቋ በሆነው በግእዝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በወቅቱም ከነጆ ከተማ ብዙም ሳይርቅ ቅልጡ ካራ በምትባል ቦታ በማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመ ገዳም እና የአብነት ትምህርት ቤት ከሃገረ ስብከቱ ጋር በመተባበር ትልቅ እንቅስቃሴ ያደረግ እንደነበር አስታውሳለሁ። የገዳሙ ዋና ዓላማም በአከባቢው ቋንቋ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት የሚችሉ አገልጋይ ካህናትን ማፍራት ነበር። በቅርቡ እንኳ በህገ ወጥ መንገድ ከተሾሙት ሁለቱ ከዚው ገዳም ተምረው የወጡ ናቸው። በኢሉ አባቦራ ፣ በጂማ፣ በምእራብ እና ምሥራቅ ሸዋም እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ጥረቶች ከተጀመሩ እንደቆዩ ይታወቃል። በሌሎችም ክልሎችም እንዲሁ። በአዳማ/ናዝሬት ከተማም እስከ 2006 ዓ/ም እስከኖርኩበት ጊዜ ድረስ በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ መምህራን ተማሪዎችን በአፋን ኦሮሞ አገልግሎት ከሚሰጡት ውስጥ እኔም አንዱ ነበርኩ። ስለዚህ በቋንቋ አገልግሎት አይሰጥም ያሉት ስህተት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ንግግር ነው። 

የትግራይን ክልል ጉዳይ እሳቸው ካነሱት አይቀር በ1990ዎቹ መጀመሪያ እኔ ለአራት ዓመታት ትግራይ (በተለይም መቀሌ) ለትምህርት በቆየሁበት ጊዜ ሙሉ ቅዳሴው አብዛኛውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ቋንቋ በሆነው በግእዝ ነበር፤ አልፎ አልፎ አማርኛ ይጠቀሙ ነበር። በትግርኛ ግን በዚያን ወቅት እኔ አልሰማሁም። የጠ/ሚ የትግራይ ቤተ ክህነትን እና የአሁኑን ችግር ለማቀራረብ የሄዱብት መንገድም ሂሊና ላለው ሰው ሌላ አደገኛ የብልጽግና ስሌት መሆኑን ይረዳል። ስለዚህ የጠ/ሚንስትሩ ንግግር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ፣ የበለጠ ነገርን የሚያባብስ፣ እሳቸው ለሚደግፉት ቡድን የልብ ልብ የሚሰጥ፣ ኦርቶዳክሳዊያንን የሚያሳዝን እና አሁን በተፈጠረው ችግር የእርሳቸው የብልጽግና ፓርቲ እጅ ያለበት ነው ለማለትም የሚያስደፍር ነው። 

አንዳንድ ቦታዎች ላይማ ገለጻ ሲያደርጉ የልጅ ነገር ወይንም ፌዝ በሚመስል መልኩ “ጣልቃ አትግቡ” እያሉ እዚያው ፊት ለፊት የነበሩትን ባለሥልጣናት ሲመክሩ ለተመለከተ ነገረ-ሥራቸው “ከእውቀት የጸዳ ነው ወይስ ከንቀት የተነሳ ነው?!” ያስብላል። ጠ/ሚንስትሩ በአገራችን የቋንቋ ጉዳይ ስስ ብልትና የልዩነት ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ያውቁታል፡፡ ይህንን ስስ ብልት ተጠቅመው ችግሩን የበለጠ አወሳስበው ተመልሰዋል። “ጣልቃ አትግቡ” እያሉ አንድ ቡድን ተደብቆ፣ ወሊሶና አዲስ አበባ ሲቆዩም የመንግሥት ጥበቃ ተደርጎለት የአንድን ተቋም ሃይማኖታዊ ሥርዓት መናዱን እያወቁ ሳያነሱት መቅረት ለሚሊዮን ምእመናን ያላቸውን ንቀት ያሳያል። በወለጋ በመንግሥት መኪና (በጀት) ጭምር ለዚያኛው ቡድን አቀባበል፣ ድጋፍ እና ሽፋን ሲሰጥ በአደባባይ እየታየ ያንን ሳይኮንኑት እና ሳያነሱት ማለፋቸው ሳይቀር “ጣልቃ አትግቡ” ብለው መሳለቃቸው ንቀት ነው። ለዚያኛው ቡድን ምንጣፍ እያነጠፈ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ጂማ ሊሄዱ የተነሱትን ሊቃነ ጳጳሳትን የመንቀሳቀስ ሕገ መንግስታዊ ነጻነት መከልከል ፤ እንዲሁም አንድ አረጋዊ ሊቀ ጳጳስ (አቡነ እስጢፋኖስ) በሃገረ ስብከታቸው ጂማ ላይ ሲታሰሩና ሲንገላቱ ሰምቶ ምንም አለማለት ለቤተ ክርስቲያኗ ያላቸውን አመለካከት እና ለምእመኑ ያላቸውን ንቀት ካላሳየ በቀር ከእውቀት ነጻ ናቸው ለማለት ያስቸግራል።  

አሁን በጠ/ሚንስትሩ የሥልጣን ዘመን እየተፈጸመ ያለው ተደፍሮ የማይታወቀው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጣስ አንዱ ምክንያት እሳቸው በሚመሩት ፓርቲ በክልሉ ለዘመናት የጎሳ ፖለቲካ ትርክቱ ቤተ ክርስቲያንን በጠላትነት እየፈረጀ ስለመጣ ነው። ቢያንስ ላለፉት አሥርት ዓመታት በተለያዩ መድረኮች በክልሉ ፓርቲ በሥልጠና፣ በሚዲያ እና በሥርዐተ ትምህርት ሳይቀር ሲቀርቡ የነበሩ የሐሰት ትርክቶች ወጣቶቹ ቤተ ክርስቲያንን በትክክለኛው መንገድ እንዳይረዱ አድርጓቸዋል። ክልሉን የሚያስተዳድረውም ሆነ በክልሉ ያሉ ተቃዋሚ ፖርቲዎች በግልጽም ሆነ በስውር፤ በተለያዩ ምክንያቶች ቤተ ክርስቲያኗ ላይም ሆነ በምእመናኖቿ ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ እጅግ ብዙ ነው። የተለያዩ ነገሥታት ሃገሪቷን ሲያስተዳድሩ ቤተ ክርስቲያኗ “ለነገሥታቱ ወገንተኛ በመሆን የኦሮሞን ብሔረሰብ ቋንቋውን፣ ባህሉን እና መብቱን እንዲያጣ አስተዋጽሆ አድርጋለች” በሚል በክልሉ በተለያዩ መድረኮች ቀርቧል። ይህ የውሸት ትርክት በኦሮሚያ ክልል ያሉ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለይቶ የመምታት ተግባር በክልሉ በተለየ እና በተጠና መልኩ የሚካሄድ ሲሆን የክልሉ ተወላጅ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኗን አማኞች እንዲሳቀቁ፣ አገልጋዮች እንዲሸማቀቁ እና አገልግሎት እንዲያቆሙ፣ የተቀሩት ደግሞ ቀስ በቀስ ከቤተ ክርስቲያን እንዲሸሹ የማድረግ ሥራ ሲሰራ ከርሟል። አሁንም ቢሆን ይህ ጫና የመፍጠር ሥርዓት በጠ/ሚንስትሩ ዘመን በስፋት ቀጥሎ ፍሬ እያፈራላቸው ይገኛል። ንግግራቸውም ይሄው ነበር። 

የመሬት ክፍፍሉን ፍትሃዊነት በተመለከተ ያቀረቡት የተንሸዋረረ መረጃም (crooked data and wrong data interpretation) ገራሚ ነው። በአጭሩ እሳቸው ያቀረቡትን የካሬ ሜትሩ ብዛት በእምነት ተከታይ ቁጥር መሰረት አድርገው ቢያቀርቡት የማን እንደሚሻል ግልጽ ይሆን ነበር። ይህንንም በዚህ መልኩ ያቀረቡበት አደገኛው ምክንያት ከሌላ ተቋሟት ጋር ለማነካካት እና ድጋፍ ለማግኘት ነው እንጂ እሳቸውም ነገሩን አጥተውት አይደለም።  

በአጠቃላይ አሁን ያለው የቤተ ክርስቲያን ችግር ሃይማኖታዊ ሁኖ ሳለ አስተዳደራዊ ጉዳይ አድርጎ ማቅረባቸው፤ በወለጋ ግንቢ ከተማ ያለውን የሃገረ ስብከቱን ጽ/ቤት ቀድሞ ሰብሮ ሕገ ወጦቹን ያስገባ የክልሉ ልዩ ኃይል ሳይሆን የፌድራል መከላከያ ሰራዊት መሆኑ፣ በብዙ ቦታዎች የአዲሶቹ ሕገ ወጥ ተሿሚዎች አቀባበል አስተባባሪዎች በምንም መልኩ ሃይማኖቱ የማይመለከታቸው የሌላ እምነት ተከታዮች እና የመንግሥት አካል መሆናቸው፤ እሳቸው ከዚህ በፊት የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉለት ዮናታንም ቀድሞ በብልጽግና የታቀደውን በትንቢት ሥም የተናገረውን ላስተዋለ፤ በፌድራል መንግሥት ጳጳሳቱ ወደጂማ እንዳይሄዱ መደረጋቸው፤ እንዲሁም ነገሩን ለማድበስበስ ጠ/ሚንስትሩ ያደረጉት ጥረት ሁሉ እሳቸው የሚመሩት የፌድራል መንግስት እና የእርሳቸው መልካም ፈቃድ ያለበት የብልጽግና መንግሥት የሚያራምደው የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ከውስጥ ገብቶ የማዳከም ብሎም የመውረስ የረጅም ጊዜ እቅድ እንደሆነ ያመለክታል። ስለዚህ ይሄ ነገር በጊዜ ‘መታረም’ አለበት።

በቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር ችግር የለም ብሎ የሚያምን የለም። የዚህ ጽሁፍ ዋና ትኩረት ግን በጠ/ሚንስትሩ ንግግር ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ሁሉም እንዲገነዘብ የሚያስፈልገው ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀለም፣ ቋንቋ፣ ዘውግና ጾታ ሳትለይ ሁሉንም የሰው ልጅ በምሥጢራት በመቀደስ ለመንግሥተ እግዚአብሔር ለማብቃት የምትተጋ በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ናት፡፡ ሁሉም ምእመናን በሚሰሙት ቋንቋ መማር አለባቸው፤ በሚሰሙት ቋንቋ የመማሩ ዓላማ ግን ቋንቋው ከሌሎች እኩል መሆኑን ወይም የተሻለ መሆኑን ለማረጋገጥ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በነፍስ ለመዳን ነው፡፡

#በዛ

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


Report Page