EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

ቀነፋ (Qanafaa)— የእመጫት መከበሪያ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ

==================================

ቀነፋ ማለት ከጠንካራ እንጨት ተፈልፍላ በቀጭን የቆዳ ጠፍር በወላድ ሴቶች ግንባር ላይ ከወለዱበት ቀን ጀምሮ እስከ አምስት ወራት ድረስ የምትታሰር የወላድ ሴት የክብር ምልክት ናት፡፡[1] ከእንጨት፣ ጨሌ፣ ቀንድ እና ሲባጎ የተውጣጣ እንደኾነ የጻፉም አሉ፡፡[2] ከለቻ በወንዶች ግንባር ላይ እንደሚደረግ ኹሉ፥ ቀነፋም በሴቶች ግንባር ላይ የሚታሠር ነው፡፡ ቀነፋ የሚያስሩት የወለዱ ሴቶች ብቻ ሲኾኑ በተለይ በአርሲ ወላድ ሴቶች ዘንድ የሚዘወተር ነው፡፡ ምንም እንኳ ኹሉም ሴቶች ክብር የሚቸራቸው ቢኾኑም፥ ዘጠኝ ወራት በሙሉ አርግዛ ሕይወትን የሰጠች እናት ደግሞ ይበልጥ ትከበር ዘንድ ይገባልና ቀነፋ የክብሯ ምልክት ተደርጎ ተሰጥቷታል፡፡[3]

በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ቀነፋ ላሰረች ሴት የሚሰጠውን ከበሬታ በሚከተሉት ነጥቦች ማጠቃለል ይቻላል፡-

(1)   አትሰደብም፣ አትመታም፣ ሸክም እንድትሸከም አትደረግም፣ ረጅም መንገድ አትሔድም፣ በፈረስ የሚሔድ ሰው እንኳ ሲያያት ወርዶ ያስቀምጣታል እንጂ አያልፋትም፡፡[4]

(2)   የሌላ ሰው ቤት በሔደች ጊዜ መጋረጃ ተጋርዶላት አልያም ሰወር ባለ ቦታ እንጂ ፊት ለፊት አትቀመጥም፤ ቅቤ ሳይቀቧት መሸኘት ነውር ነው፤ ቤታቸው ገብታ መመገቧ በራሱ መልካም ገድ ነውና ኃይለ ቃል እንኳ አይናገሯትም፡፡[5]

(3)   ባለቤቷ ፈጽሞ ሊመታት አያስብም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ይኽንን ለማድረግ ቢሞክር ግን፥ ለጎረቤቶቿ የድረሱልኝ እልልታ ታሰማለች፤ ሴቶች ኹሉ ሲቄአቸውን ይዘው ይወጣሉ፡፡ ‹‹ወላድ ተመታች! እናት ተደበደበች…!›› የሚል ዜማ[6] እያዜሙ ይደርሱላታል፡፡ ነገሩ እዚህ ደረጃ ደረሰ ማለት ባልዬው ወጥመድ ውስጥ ገብቷል፡፡ እጥሩን ከብበው በቁጥጥር ሥር ያውሉታል፤ ዳግም ይህንን በመሰለ ጸያፍ ተግባር ላይ እንዳይገኝ ያስምሉታል፤ ወይፈን ወይም ጠቦት እንዲያርድላቸው አድርገው ይቀጡታል፡፡

(4)   ደግሞም፥ (በተለይ በቀደመው የማኅበረሰቡ እሴት መሠረት) አንዲት ቀነፋ ያሰረች ሴት ታርሳ መጠንከር ስላለባት ቀነፋው ራሱን በቻለ የድግስ ሥነ-ሥርዓት በክብር ከግንባሯ ላይ እስከሚወርድ (አምስት ወራት) ድረስ በባሏ ጋር እንኳ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አትፈጽምም፡፡[7] ባሏም በእነዚህ ጊዜያት ኹሉ አልጋውን ለቅቆላት መሬት፣ ብቻውን ይተኛል፤ ሕጻኑ በወጉ ጡት ጠብቶ ሳይጠነክር ሌላ እንድታረግዝ ማድረግም እንደነውር ይቆጠር ነበር፡፡ እናም፥ የቀነፋ ሥርዓት እንደ ቤተሰብ ምጣኔ ዘዴም (“Family Planning Method”) ያገለግል ነበር ማለት ነው፡፡[8] ይህንን ማኅበራዊ ሕግ ጥሶ ለማስገደድ የሚሞክር ወንድ ቢኖር ግን ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል፡- ከቅጣቱ ለማምለጥ ቢሮጥ እንኳ ተሳድዶ ይያዝና ጉዳዩን ለመዳኘት የተሰበሰቡትን አርዶ ከማብላትም አልፎ ወጣቶች ልብሱን ቀድደው ዘንጋቸው ላይ በማውለብለብ ይዘፍኑበታል፤ እስከ 15 ቀናት ድረስ እየሰደቡትና እየገረፉት ገበያ ለገበያ ያዞሩታል፤ በዚህ መልኩ የተዘፈነበት ደግሞ በማኅበራዊ ጉዳዮች ኹሉ ከሰውነት ደረጃ ዝቅ ይላል፤ የገዳ ሥርዓትን አይካፈልም፤ በአምልኮ ቦታዎች አይመርቅም፤ ለዋስትናም አይበቃም![9]

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


[1] ድሪቢ ደምሴ ቦኩ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ.265፡፡

[2] Saafii Tamaam, Qaaccessa Raawwii Sirna Ulmaa Dubartii Oromoo Godina Arsii, Aanaa Xannaa; 2009:iii.

[3] Hayiluu Bantii, Cooraa Aadaa Jimmaa,Oromiyaa, 1997:19

[4] ድሪቢ ደምሴ ቦኩ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ.265፡፡

[5] https://hornaffairs.com/om/2014/12/07/siinqee-kabachiiftuu-mirga-dubartootaa/ (Charinnat Hundeessaa).

[6] ይህ ‹‹የሲቄ ዜማ›› በአፋን ኦሮሞ፡- “Hanshooshillee…deessuu aannanii, harmee aannanii, maaliif dhaananii, anaan waamanii…” እያለ የሚቀጥል ነው፡፡

[7] ድሪቢ ደምሴ ቦኩ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ.265፡፡

[8] Akka barreessaan Amsico jedhutti (https://oromiatiyya.wordpress.com/2015/07/11/qanafa)

[9] ድሪቢ ደምሴ ቦኩ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ.266፡፡ 



Report Page