EwnetMedia 2022
EwnetMedia
ሲቄ (Siiqqee)—የሴቶች መብትና ክብር መገለጫ በትር
==================================
ይህች ረዘም፣ ቀጥ ያለች፣ ቀጭንና አንጓ አልባ የክብር በትር ስትኾን የኦሮሞ ሴቶች ካገቡበት ቀን ጀምረው የሚይዟት ናት፡፡ በሴቷ ቁመት ልክ ከተቆረጠች በኋላ እንድትቀላና እንድትጠነክር በሚል ጭስ ባለበት ቆጥ ላይ እንድትሰነብት ይደረጋል፡፡[1] በተለይ ሴቷ ስታገባ የሙሽሪት እናት፥ ‹‹ከዚህ በኋላ እኔ ካጠገብሽ የለሁምና ራስሽን ቻዪ›› በሚል የምትሰጣት የድጋፍ ምልክት ናት፡፡ የክብር በትር በመኾኗም እንደ ሌላው አውሬ ለመምታት፣ ውሻ ለመከላከል፣ ከብት ለመንዳት፣ ለምርኩዝና መሰል አገልግሎቶች አትውልም፤ ለጌጥ፣ ለሠርግ፣ ለለቅሶና ገበያ ቦታዎችም አትያዝም፡፡[2] ከላይ እስከ ታች እኩል ውፍረት ያላትና ቀጥ ያለች መኾኗ፥ ‹‹ያለማወላወል የታማኝነትና ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን ሕግና ሥርዓት ጠብቆ መጓዝን ይወክላል›› ብለው የተረጎሙ አሉ፡፡[3]

ሲቄ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች አሏት፡- የሴቶች መብት ማጎናጸፊያ ናት፤ ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ክብር የምታስጠብቅ ናት፤ እርቅን ለማውረድና ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ ናት፤ በምርቃትና ጸሎት ወቅቶችም ትያዛለች፡፡ እናት ልጇን ሲቄ አስይዛ ለባዕድ ስትድራት ወንዱ ይጎዳታል ብላ አንዳች ሥጋት አይገባትም፤ ከየትኛውም ጥቃት የምትድንበትን መሣሪያ (ሲቄ) አስታጥቃታለችና! በትሯ የፍትሕ ርትዕ ምልክት እንደመኾኗ በዚያች ንብረቶቿን ትጠብቃለች፤ ይዞታዎቿን ታስከብራለች፤ አካሏን ከጥቃት ትከላከላለች፡፡ ሴቷ አንዴ የመጠቃት ድምጽ (ililfannaa) አሰምታ፣ ሲቄ ይዛና በባልንጀሮቿ ታጅባ ከቤት የወጣች እንደሁ መመለሻው ከባድ ነው፤ አጥቂው (ባል) በሲቄ ሕግ (“Seera Siinqee”) ተገቢውን ቅጣት የሚቀበል ይኾናል፡፡ አለበለዚያ ግን ሴቷ ወደ ቤቷ ስለማትመለስ ሕጻናት እየራባቸው ያለቅሳሉ፤ ያልታለቡ ላሞች ይጮሃሉ፤ እርሱም ቢኾን በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ የተናቀ ይኾናል፡፡
ሲቄ የምትይዝ ሴት (“Haadha Siinqee”/የሲቄ እናት) በማኅበረሰቡ ዘንድ እጅጉን ትከበራለች፡- መንገድ አያቋርጧትም፤ ቀድመዋት ወንዝ አይሻገሩም፤ ካልፈቀደችላቸው ከመንገድ አያልፏትም፤ በፈረስ ጀርባ ያለ ሰውም ወርዶ “na ofkalchi” (ይቅርታ ይደረግልኝ) ብሎ አክብሮ ያስፈቅዳታል፡፡ በሰዎች መካከል አንዳች አለመግባባት ሲፈጠር፥ በዕድሜ የገፉ ሴቶች ሲቄ፣ ጮጮና ለምለም ሣር ይዘው በሁለቱ ተፋላሚ አካላት መካከል ሲገቡ ተፋላሚዎቹ ጠባቸውን አቁመው ድርድር ይጀምራሉ፡፡[4] ከኹሉም ሴቶች ቀድማ ትመርቃለች፤ ሲቄዋን ይዛ ፈጣሪን ትማጸናለች፤ ዋቃም ለሲቄዋ ክብር ስላለው ይሰማታል ተብሎ ይታመናል፡፡
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] Dirribii, Ilaalcha Oromoo, 2009: 30.
[2] ድሪቢ ደምሴ ቦኩ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ.264፡፡
[3] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.197፡፡
[4] እሸቱ ኢረና ዲባባ፤ የኦሮሞ ታሪክ፤ 2001 ዓ.ም፣ ገጽ.170፡፡
