EwnetMedia 2022
EwnetMedia
‹‹ነፍጠኛ›› እየተባሉ በኦሮሚያ ምድር የሚቀጠፉ ነፍሳት!
=========================================
በመዝገበ ቃላዊ ትርጉሙ መሠረት ‹‹ነፍጠኛ›› ማለት ‹‹የጦር መሣሪያ የያዘ›› ማንኛውም አካል ማለት እንጂ ከአንድ ሕዝብ ጋር ብቻ የተያያዘ አልነበረም፡፡ በዚህ አረዳዱ ደግሞ፥ የኦሮሞም፣ የአማራም፣ የትግራይም፣ የአፋርም፣ የሱማሌም፣ የደቡብ ሕዝቦችም፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝም፣ የጋምቤላም ‹‹ነፍጠኞች›› መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡
ዛሬ ላይ ግን የ ‹‹ነፍጠኛ›› ትርጉም ሌላ መልክ ይዟል፡፡ በተለይ ከሕወሓት መራሹ ኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት (1983 ዓ.ም) በኋላ፥ ‹‹ነፍጠኛ›› በስፋት የታወቀው ‹‹ለአማራው ሕዝብ ብቻ የሚቀጸል››፣ በማሸማቀቅያ ስድብነቱ እና በተገዳይ ጠቋሚነቱ ኾነ፡፡ ይልቁንም፥ በሕወሓት መዝገበ ቃላትና በጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ‹‹ነፍጠኛ›› የሚለው ቃል በሌላው ሕዝብ ነጻነትና እኩልነት የማያምን፣ በድሮው አስተሳሰብና አገዛዝ ሥርዓት ለመጓዝ የሚፈልግ፣ የሌላውን ሕዝብ ድምፅ በማፈን የዐማራውን ገዢ መደብ የበላይነት ለማስፈን የሚፈልግ አስተሳሰብ (ሰው)፣ አልያም የሕዝቦችን አንድነት ለመጠበቅ የሚተጋ ማንኛውም ተቋም (ኦርቶዶክስ ዓይነቱ) ተብሎ ተተረጎመ፡፡

በዚህ መልኩ ፖለቲካው የሀገሪቱን ሕዝቦች ከፋፍሎ ለመግዛት ይመቸው ዘንድ አንዱን ጨቋኝ፣ ሌላውን ተጨቋኝ አድርጎ በዜጎች ኅሊና ከቀረጸ በኋላ ይኽንን መሰል ቃል እየተማዘዙ እንዲሰዳደቡ፣ እንዲደባደቡና እንዲገዳደሉ በር ከፈተላቸው፡፡
‹‹ነፍጠኛ›› የሚለውን ቃል ወደ ማሸማቀቅያነት ከቀየሩት የዘመናችን ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ ሲነገር ለመገመት እንደሚቻለው ‹‹የነፍጠኞች ዘመን›› እየተባለ የሚረገመው ከትግራዋዩ ዐፄ ዮሐንስ በኋላ የነገሡት ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሕወሓት ሥልጣን ላይ እስኪወጣ ድረስ ያለው ጊዜ መኾኑ የሴራውን ምንነት በግልጽ ይጠቁማል፡፡
ከዘመነ ኢህአዴግ በኋላ የመጣው ትውልድም ይኽንኑ ትርክት ደጋግሞ ከመስማቱ የተነሣ ‹‹ነፍጠኛ›› ለዐማራ ብቻ የሚቀጸል አድርጎ አመነ፤ በማንበብና በመጠየቅ ወደ እውነታው ከመድረሴ አስቀድሞ እንደዚያው ከሚመስላቸው መካከልም እኔው አንዱ ነበርኹ፡፡ በዚኹ አግባብ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች (በተለይም ኦሮሞ) ‹‹ነፍጠኛ›› የሚለውን ቃል በዋናነት ዛሬ ‹‹ዐማራ›› ተብሎ የሚታወቀውን ሕዝብና ክልል ለመስደብ እንዲጠቀምበት ተቀርጾ ተሰጥቶታል፤ ትውልዱም ስድብ መሰለውና ይዞት ቀጠለ፡፡ የሚገርመው ከዐማራው የኾነው ትውልድ ራሱም ይኽንኑ ትርክት ተቀብሎ ማፈሩና መሸማቀቁ ነው (ምንም እንኳን አኹን አኹን ‹‹አዎን ነፍጠኛ ነኝ!›› ብለው መፎከር የጀመሩ ቢኖሩም)፡፡
በዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ ጥናቶች መሠረት ‹‹ዋና ዋና የዘር ማጥፋት እርከኖች›› (stages of Genocide) ከሚባሉት መካከል የጥፋት ቃላት ስያሜ (Assigning Derogatory Words or Speech Wars) አንደኛው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃም የተደገሰልን የጥፋት ተልእኮ ይኸው ነው፤ እግዚአብሔር የሰይጣንን ተንኮል በማክሸፉ (በአንጻራዊነት) ሴራው በተቀነባበረበት ልክ ባይኾንም በዚኹ ‹‹ነፍጠኛ›› ስያሜ ሽፋንነት የበርካቶች ነፍስ ተቀጥፏል፡፡ በ2012 ዓ.ም ብቻ፣ በኹለት ዙር (ጥቅምትና ሠኔ) በምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ውስጥ ኦርቶዶክሳውያንን እየለዩ ጭካኔ በተሞላበት ኹኔታ ሲያርዱ የነበሩት አክራሪ ሙስሊሞች ‹‹ነፍጠኞች ከኦሮሚያ ምድር መወገድ አለባቸው!›› ብለው በመዛት ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ለወሊድ የተቃረበች ነፍሰ ጡሯን ኦርቶዶክሳዊት ሲገድሉ እንኳን ‹‹ቢያንስ ሆዴ ውስጥ ስላለው ልጄ ብላችሁ ተውኝ?›› ብላ ስትማጸናቸው የእርሷ መገደል ብቻ ሳይኾን ‹‹እንዲያውም ‹ነፍጠኛ› መወለድ የለበትም›› ብለው የጭካኔአቸውን መሠረት መናገራቸው ይኽንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ‹‹እኔ ኦሮሞ ነኝና አትግደሉኝ›› ብለው ነፍሳቸውን ለማትረፍ የሞከሩትም አልተሳካላቸውም፤ ‹‹የነፍጠኞችን ሃይማኖት የሚከተል ኦሮሞ አናውቅም!›› ብለው ኦሮሞ ለመባል ሙስሊም መኾን የግድ መኾኑን ነግረው ገድለዋቸዋል፡፡ ((እነሆ ዘንድሮ፣ በ2014 ዓ.ም ደግሞ፣ በቀናት ልዩነት ብቻ በሁለቱ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሓን የአማራ ማኅበረሰብ አዛውንት፣ ሴቶች፣ ሕጻናት ሳይቀሩ በአሰቃቂ ኹኔታ ተጨፈጨፉ፤ በወጉ ለመቀበር እንኳ ዕድል ተነፈጋቸው))፡፡
ወንጀለኞቹ ይኽንን የጥቃት መለያ ተጠቅመው ወንጀል ከመፈጸማቸው በፊት ግን በርካታ ሂደቶች ነበሩ፡፡ መጀመሪያ ፖለቲከኞቹ ‹‹ነፍጠኛ›› የሚለውን ቃል ወደ ስድብና ማሸማቀቅያነት ቀይረው ‹‹ዐማራ›› ለሚባል ሕዝብ ቀጸሉ፤ በትጥቅ ትግል ማኒፌስቶ ጭምር አጥላሉ፤ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥም ወሽቀው በትውልዱ አእምሮ ውስጥ አደላደሉ፡፡ ከዚያ ቀጥለው ኦርቶዶክስን ‹‹የነፍጠኛው ዐማራ ሃይማኖት ናት›› ብለው ከማንነቷ በተቃራኒ ገለጹአት፡- ‹‹ኦርቶዶክስ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ውኃ በመርጨት ዐማራ ታደርጋለች›› የሚሉ ፕሮፌሰሮች በሕዝብ ሚዲያ ላይ ጭምር ወጥተው በይፋ እንዲደሰኩሩም ተደረገ፡፡[1] ይኸንኑ አስተሳሰብና አነጋገርም ተከታዮቻቸው ተቀባብለው አራገቡት፤ በርካቶችም እንደ ‹‹እምነት›› ተቀበሉት፡፡ በዚኹ መልኩ የሰውን ኅሊና ካሳመኑ በኋላ ‹‹የነፍጠኞችን አከርካሪ ሰብረናል!›› ብሎ በአደባባይ አሽሙር መናገር የትግሉ አካል ኾነ፡፡ እነሆ በዚኹ መልኩ ‹‹ነፍጠኛ›› የሚለውን ቃል ማየት የማይፈልጉትን ሥርዓት፣ ግለሰብ፣ ሕዝብና የሃይማኖት ተቋምም ለማጥፋት ተጠቀሙበት፡፡
ሌላው ቀርቶ፥ ለአማራው ሕዝብ ተለይቶ መጨፍጨፍ፣ በኦሮሚያ ውስጥ ላለችዋ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መቃጠልና ለኦርቶዶክሳውያንም በአሰቃቂ ኹኔታ መታረድ ቁልፉ ምክንያት ይኸንኑ የጥላቻ ቃል በኦፊሴል ደረጃ ያራገቡ የሀገሪቱ ባለሥልጣናትና ምሁራን ነን ባይ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ጭምር መኾናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ አውቀውም ይኹን ሳያውቁ አማራንና ኦርቶዶክስን ከኦሮሚያ ማጽዳት፣ ኢስላሚክ ኦሮሚያን መመሥረት ለሚለው የአክራሪዎች ሴራ ኹኔታዎችን ያመቻቹትም መሪዎቹ ራሳቸው ናቸው፤ እጅግ በርካታ ታዳሚዎች ባሉበት መድረክ ላይ፡- ‹‹ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት ‹ነፍጠኛ› ኦሮሞን ባሸነፈበት ቦታ እኛም ነፍጠኛውን ሰብረናል›› ብለው የተሳለቁ ነበርና፡፡[2] በሀገር መሪ ደረጃ በተነገረው በዚኹ መርዘኛ አገላለጽ መሠረትም በከፍተኛ የደስታ ስሜት ተውጠው ሲያጨበጭቡ የነበሩ የመኖራቸውን ያህል በአገላለጹ ከመሸማቀቅም አልፈው በሀገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ክፉኛ ያዘኑ ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡
ሲጠቃለል፥ ጥንቱን የሀገር ዳር ድንበር መጠበቂያና የዜጎች ደኅንነት ዋስትና የነበረው ቃል (‹‹ነፍጠኛ››) ዛሬ ላይ ኹሉ ነገሩ ተገለባብጦ ኢትዮጵያውያኑ ወንድማማቾች ከመሣሪያው በላይ እርስ በርስ የሚገዳደሉበት ቃል መኾኑ አሳዛኝ ነው! አኩሪውን ቃል አሳፋሪ ማድረግ በራሱ ታሪክን አለማወቅና እና ውድቀት ኾኖ ቃሉን ተጠቅሞ ሌላውን ወገን ማሸማቀቅና መግደል ደግሞ ከሰውነትም በታች መውረድ ነው፡፡ ወደ ትክክለኛው ጽንሰ ሀሳቡ ብንመለስ ግን በአባቶቻችን ጀግንነት ከመኩራታችንም በላይ ‹‹ነፍጠኛ!›› እየተባባልን በተሞጋገስን፣ ጠላቶቻችንንም ባሸማቀቅን ነበር! ዛሬ ግን፥ አልታደልንምና፤ ጀግኖች አባቶቻችን ጠላትን ድል በነሡበት ቃል እና እርስ በርሳችን እየተጫረስንበት ነው!
‹‹ነፍጠኛ›› እየተባሉ ባላወቁት ፖለቲካ ለተቀጠፉ ነፍሳት ዕረፍተ ነፍስን፣ ለገዳዮችና አስገዳዮች ደግሞ ማስተዋልን ያድልልን!
ምንጭ፡- ‹‹ጊንጊልቻ›› መጽሐፍ፣ ኹለተኛው ክልስ ዕትም፣ መጋቢት 2014 ዓ.ም፣ ገጽ 245-246፡፡
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] ዶ/ር ገመቹ መገርሣ፤ መስከረም 2012 ዓ.ም ከ LTV ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ልብ ይሏል፡፡
[2] ይህንን የተናገሩት የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሣ ሲኾኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በዐዲስ አበባ ከተማ በተከበረው ‹‹ኢሬቻ ፊንፊኔ›› ላይ (መስከረም 2012 ዓ.ም) ነበር፣ ይኽም ንግግራቸው በቀጥታ ሥርጫት ከመተላለፉም ባሻገር በኋላም በተለያዩ ሚዲያዎች ተደጋግሞ በመራገቡ ዜጎች በድጋፍና ተቃውሞ ጎራዎች ተቧድነው እንዲነታረኩ ምክንያት ኾኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
