EwnetMedia 2022
EwnetMedia
በአስማታዊ ቃላት ፍረጃ ለቀጣይ ጥቃት ማመቻቸት!
==================================
በዓለም ታሪክ ውስጥ አጥቂዎች ተጠቂዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን፣ የዘር ማጥፋት ርምጃዎችን ከመውሰዳቸው በፊት የድርጊታቸውን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥላቸው መሠረት (justifying ground) ማመቻቸታቸው የተለመደ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰው በተፈጥሮው ለባዊ (የሚያስብ ኅሊና፣ የሚያስተውል ልቦና ባለቤት) ነውና፥ ‹‹እነዚኽን አካላት አጥቃ፣ ግደል፣ አስወግድ!›› ሲባል፡- ‹‹ይኽንን የጭካኔ ድርጊት በሰው ላይ የማደርሰው ለምንድን ነው?›› ብሎ የማሰብ አዝማሚያ አለውና በሚፈለገው መጠን ሊጨክን አይቻለውም፡፡ እናም፥ ዋናው ስልት እንዲጠቁ (እንዲጠፉ) የሚፈለጉትን አስቀድሞ አስማታዊ ቃላትን (magic words) በመጠቀም ከሰውነት ተራ ማውረድ (dehumanization)፣ ከእንስሳት አንዱ አድርጎ በማስቆጠር ማሸማቀቅ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በሩዋንዳው ጭፍጨፋ ሁቱዎች ቱትሲዎችን ከመጨፍጨፋቸው በፊት ቱትሲዎቹ ‹‹መጤ›› እና ‹‹ዲቃላ›› እንጂ ትክክለኛ ሰው እንዳልኾኑ፣ ይልቁንም ግእዛን ከሌላቸው እንስሳት መካከል እንደሚመደቡ፣ ከእንስሳም ኀይል፣ ጥቅምና ዕውቅና የሌላቸው ‹‹ኢንየንዚ››/በረሮዎች (cockroaches) እንደኾኑ አድርገው ጨፍጫፊዎቹን አሳመኑ፡፡[1] ቱትሲዎች በምድር ከኖሩ ለሁቱዎች ተናዳፊና መርዘኛ አውሬ መኾናቸውን ለማሳመን በሚመስል መልኩም ‹‹እባብ ናቸው›› አሏቸው፡፡ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ሁቱዎቹ ቱትሲዎቹን ሲገድሉ ሰው እየገደሉ ሣይኾኑ አላስፈላጊ በረሮዎችን እያጸዱ (“wiping out the cockroaches”) እና አደገኛ እባቦችን እያስወገዱ እንደኾነ፣ በዚኽ ድርጊታቸውም ለምድሪቱ ውበትና ሰላም አስተዋጽዖ እንዳደረጉ ጭምር ያስቡ ነበር፡፡[2]

ናዚ መራሹ የጀርመን ቡድንም በአይሁዳውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀሉን ከማካሄዱ በፊት አይሁዳውያኑን ከሰውነት ተራ በማውጣትና ‹‹ባክተርያ›› እንደኾኑ በመስበክ ነበር፡፡[3] ባክተርያን ማጽዳት ደግሞ ጤንነትንና ቀጣይ ሰላማዊ ኑሮን ከማረጋገጥ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመኾኑ ማንኛውም ጀርመናዊ ይሁዲ የኾነን ሰው ከገጸ ምድር ለማጥፋት አያቅማማም ነበር፡፡ ሌላው ክፍለ ዓለም ‹‹ዘር ማጥፋት›› (Genocide) ብሎ ሲከሳቸውም ጉዳዩ በእነርሱ ብሶ ይገረሙ ነበር፤ ‹‹ባክተርያን ማጽዳት እንዴት ወንጀል ይኾናል?›› ይሉ ነበርና፡፡ በዚኽ መልኩ ድርጊቱን መግለጽ ደግሞ የዘር ማጥፋት የመጨረሻ ደረጃ (The last phase of genocide) የሚባለውን ‹‹መካድ›› (denial) ያመለክታል፡፡
በጥቅሉ የሩዋንዳውንም፣ የናዚ ጀርመኑንም ሒደት ስንመለከት ወደ አካላዊ የዘር ማጥፋት ሒደት ከመገባቱ በፊት ለዚያ መንገድ የሚጠርጉ፣ ወንጀሉን በጎ አስተዋጽዖ የሚያስመስሉ የፍረጃ ቃላት (coined magic words as crime code) መፍጠር የመጀመሪያ ተግባር ነበር፡፡ እነዚህ ቃላት የግለሰቦችን ሰብአዊ ክብር ይሽራሉ፤ የዜግነት መብታቸውን ይገፍፋሉ፤ ለቀጣዩ ጥቃት አመቻችተው ያስረክባሉ፡፡
በሀገራችንም መሰል የማጥፊያ ቃላት (labelled codes) በተለያዩ ዘመናት፣ በተለያዩ አካላት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ለምሳሌ፡- በደርግ ጊዜ ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ፣ አድኃሪ፣ ቡርዣ፣ ኢሕአፓ፣… በሚሉ የፍረጃ ቅርጫት ውስጥ ከከተቱ በኋላ መረሸን ጀግንነት ነበር፤ ድርጊቱን ግን ከወንጀልነቱ ይልቅ ‹‹የሀገር ጠላቶችን ማስወገድ›› ተብሎ ያስተረጎመው አስቀድሞ የተሠራው የፍረጃ ሒደት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በነበረው ዘመነ መንግሥት ደግሞ ‹‹የድሮ ሥርዓት ናፋቂ!››፣ ‹‹አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት ባዮች!››፣ ‹‹ጠባብ››፣ ‹‹ትምክህተኛ››፣ ‹‹ነፍጠኛ››፣ ወዘተ. የሚባሉ የፍረጃ ቃላት ተፈጠሩ፡፡ እነዚህ ቃላት ለጊዜው እንደ ማሸማቀቂያ፣ ለዘላቂነቱ ደግሞ ለዘር ማጥፋቱ መንገድ ጠራጊ ኾነው ያገለግላሉ ማለት ነው፡፡
አይደለምና በተለያዩ ብሔሮችና ሕዝቦች መካከል ቀርቶ በኦሮሞ ሕዝቦች ውስጥ እንኳን መሰል የቃላት ፍረጃ ተከስቶ ቦረናዎች ጉጂዎችን እንደ አውሬ እያደኑ መግደል ጀምረው ነበር፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ገዳዮቹ ተይዘው በሕግ ፊትም ቀርበው ሲጠየቁ (በቦታው ከነበረ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን እንደተሰማው)፡- ‹‹ጋብራን [ባርያ] እንጂ ሰው አልገደልንም!›› ማለታቸው ነበር (የክሕደት/denail ደረጃ መኾኑ ነው)፡፡
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሁለት ዞኖች (በምዕራብ ወለጋ/ጊምቢ እና በቄለም ወለጋ/ደምቢዶሎ) በአማራው ማኅበረሰብ ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋም መነሻው ‹‹ነፍጠኛ›› የሚል የዘር ማጥፋት አስማታዊ ቃል ነው! ይኸንን የተሳሳተ ትርክት ከምንጩ እስካላደረቅን ድረስ የሕዝባችን ሰቆቃ እና እርስ በርስ መጠፋፋት ይቆማል ብሎ ማሰብ የዋሕነት ነው፡፡ ለሞቱት ወገኖቻችን ዕረፍተ ነፍስን፣ ለገዳዮችና አስገዳዮች ማስተዋልን እንዲያድልልን ፈጣሪን እየተማጸንን፥ በቀጣይ ጽሑፋችን፡- ‹‹ነፍጠኛ እየተባሉ በኦሮሚያ ምድር የሚቀጠፉ ነፍሳት!›› በሚል ርእስ እንመለስበታለን፤ እያነበባችሁ እና ለሌሎችም ሼር እያደረጋችሁ ጠብቁን!
ምንጭ፡- ‹‹ጊንጊልቻ›› መጽሐፍ፣ ኹለተኛው ክልስ ዕትም፣ መጋቢት 2014 ዓ.ም፣ ገጽ 242-243፡፡
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] የሁቱ ባለሥልጣናት፡- ‹‹እነዚኽ በረሮዎች የናይልን ወንዝ ተከትለው መጥተው ሀገራችንን አቆሸሹት፡፡ አኹን ኹላችን በአንድነት ኾነን ማድረግ ያለብን አለ፡፡ ይኸውም፥ በበረሮዎቹን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ነው፡፡ ቶሎ ሀገራቸው እንዲገቡ ናይባሮንግ ወንዝ ውስጥ እንጨምራቸው›› ማለታቸው ተጽፏል (Malvern, Linda. A People Betrayed. The Role of the west in Rwanda’s Genocide, Zek Books; 2000: 47, London).
[2] Haworth, Marcus Timothy, "Church and State in Rwanda: Catholic Missiology and the 1994 Genocide Against the Tutsi" (2018), P. 30.
[3] BOSMAJIAN, HAIG A. The Magic Word in Nazi Persecution. ETC: A Review of General Semantics; Vol. 23, No. 1 (March 1966), pp. 9-23.
