EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

ኦሮሞዎች ስለ ሞት ያላቸው እምነት እና ድኅረ ሞት የሚፈጽሟቸው ሥርዓቶች

==================================

1.    ስለ ሞት እና ሙታን ያላቸው እምነት፡-

ኦሮሞዎች አንዲት ተወዳጅ ብሂል አለቻቸው፡- ''kan sodaatanis du'a, kan hin oolles du'a'' የምትል፤ ‹‹የሚፈራው ሞት ነው፣ የማይቀርም ደግሞ እርሱው ነው›› ማለት ነው፡፡ የማኅበረሰቡ አዛውንት (ኹሉም ማለት ይቻላል) ስለ ገነትና ሲዖል ግልጽ ባለ ኹኔታ አያስረዱም፤ ግን ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ በተዘዋዋሪ ቃላት ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ሰው በሌሎች ላይ መጥፎ ነገር ሲሠራ ካዩ፥ ‹‹ነፍሱን ለምን ለኵነኔ ይዳርጋል?!›› እያሉ ይገረማሉ፡፡ የሟችን ሰው ልጅም መበደል አይፈልጉም፡- ‹‹በሰማይ ትጠይቀኛለች›› ይላሉ፤ የሞቱት ይገናኛሉ የሚል እምነት ስላላቸው፡፡ ባላምበራስ ጀቤሣ ደግሞ ቡሩስ የተባለው የውጭ ዜጋ ስለ ማኅበረሰቡ የጻፈውን ጠቅሰው የሚከተለውን ጽፈዋል፡-[1]

‹‹ኦሮሞች በአካለ ትንሣኤ ያምናሉ፡፡ አካሉም ሲነሣ ከሕመም፣ ከሐዘንና ችግር ነጻ እንደሚኾንና አሁን ካለው አካል የበለጠ ፍጹም አካል እንደሚኾን፣ እንደገናም እንደማይሞት ያምናሉ፡፡ አንዳንዶቹም ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር እንደገና ባልታወቀ ቦታ እንደሚኖሩና አንዳንዳቸው ደግሞ ያልታወቀ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ያምናሉ፡፡››

2.  ‹‹ሬሳ ያረክሳል››፡-

ኹሉም የማኅበረሰቡ አባላት ባይኾኑም ቃሉ በተስፋፋባቸው አከባቢዎች ለሬሣ ያለው አመለካከት የተለየ ነው፡፡ እንኳንስ ሬሣ የነካ ቀርቶ በዓይኑ ያየ ሰው ‹‹ይረክሳል›› ተብሎ ስለሚታሰብ እስከተወሰኑ ቀናት ወደ ቃሉ ቤት እንዲገባ አይፈቀድለትም፡፡ ይኸውም በኦሪት፥ ‹‹የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይኾናል...ባይነጻ የእግዚአብሔርን ድንኳን ያረክሳል...›› የተባለውን ያስታውሰናል (ዘኁ.19፥11-22)፡፡

በተለይ ደግሞ የቃሉ መንፈስ ያረፈባቸው (አያንቱ የሚባሉት) ወደ ለቅሶ ቤት ፈጽሞ አይሔዱም፡፡ ምናልባት የሞተው ከዘመዶቻቸው ከኾነ እንኳ ወደ ሌላ ቦታ ያሸሹአቸዋል፣ አልያም በተለየ ቤት ይዘጋባቸዋል፡፡ አለበለዚያ መንፈሱ በከፍተኛ ኹኔታ ያስጨንቃቸዋል (ይታመማሉ)፤ ከባሰም እነርሱን ወደ አላስፈላጊ ኹኔታ መርቶ ራሱ ሊርቃቸው ይችላል፡፡ በብሉይም ስለ ካህናቱ ቅድስና፡- ‹‹...ከወገናቸው በሞተ ሰው ራሳቸውን እንዳያረክሱ ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ንገራቸው... ስለሞተ ሰው ራሳቸውንና ጢማቸውን አይላጩ፣ ሥጋቸውንም አይንጩ፣... ወደ ሞተሰው ኹሉ አይግባ...›› የሚል ትእዛዝ ነበር (ዘሌዋ.21፥1፣5፣11)፡፡ 


እንዲያውም፥ በአንዳንድ ቦታዎች የእውቅ ቃሉ መንፈስ ተሸካሚዎች ሲሞቱ እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይወሰዱም፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ አለመወሰዳቸው ሳይኾን ከቤተ ክርስቲያኑ በተሻለ ኹኔታ መቃብር ቤት በስማቸው በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሸቆጥቁጦ (አምሮ) ተዘጋጁቶላቸው እያለ እነርሱ ሲሞቱ ግን ሬሣቸው እዚያው መንደር አከባቢ እንዲቀበር ይደረግና ለማስመሰል ያህል የታረደ በግ በሳጥን በሕዝብ ታጅቦ መቀበሩ ነው፡፡

3.  ‹‹ቀበኔሣ››—ጸሎት በእንተ ሙታን፡-

በማኅበረሰቡ ዘንድ ለሟች ተዝካር ማውጣት የተለመደ ሲኾን ከዋናው ተዝካር በፊት ቀበኔሣ (Qabbaneessaa) ማድረግ የተለመደ ነው፡፡[2] ‹‹ቀበኔሣ›› በቁሙ ‹‹ማብረድ›› ማለት ነው፤ ‹‹የሟችን ነፍስ አብርድ›› ተብሎ የሚጸለይበት ሥርዓት ነው፡፡ በእርግጥ ‹‹አብርድ›› የሚባለው የሚተኩስ (የሚያቃጥል) ነገር ስላለ መኾኑ ግልጽ ቢኾንም አብዛኞቹ የማኅበረሰቡ አዛውንት ግን ይህችን ምሥጢር በደንብ ማብራራት ይሳናቸዋል፡፡ ብቻ ሰዎች ተጠርተው የተደገሰውን ድግስ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ‹‹ነፍሷ ይብረድ፣ነፍስ ይማር›› ብለው መርቀው ይሔዳሉ፡፡ 

4.  ‹‹ኤኬራ››— የኦሮሞ ሙታን መንፈስ፡-

በኦሮሞዎች ዘንድ ነፍስ ‹‹ሉቡ›› የምትባል ሲኾን ከሥጋ ስትለይ ግን ‹‹ኤኬራ›› (Ekeraa) ትባላለች፡፡ በማኅበረሰቡ እምነት ደግሞ ይህችን የሞተች ነፍስ የሚያናግሩ፣ ከሕያዋን ቤተ ዘመዶቹ ጋር አገናኝተው ሳይጨርሷቸው የቀሩ ጉዳዮችን መረጃ የሚያለዋውጡ ''ekeraa dubbistuu/Jarjituu'' (ኤኬራ አናጋሪዎች) አሉ፡፡ በዚህ መንገድ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ለዚሁ አገልግሎት በተመረጡ (አያንቱዎች) አማካይነት ‹‹ይናገራል›› ተብሎ ስለሚታመን ቤተ-ዘመድ ተሰብስቦ ወደ መናፍስት ጠሪዎቹ ይሔዳል፡፡

የዚህ ሥርዓት ዋና ዓላማ፥ ምናልባት ሳይናገር የቀረው ምሥጢር አልያም ሳይናዘዝ የሞተው ውርስም ካለ በዚሁ ኤኬራ አማካይነት እንዲጠየቅና ምላሹን ለመስማት፣ በዚያው ቃል መሠረትም ተፈጻሚ እንዲኾን ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ሰው በማይታወቅ ምክንያት (ድንገት) ቢሞትና የሞተበት ምክንያት (ሰው ገድሎትም ከኾነና ገዳዩ ካልታወቀ) በኤኬራ አማካይነት ይለያል፤ ‹‹እከሌ ገደለኝ ብሎ ይናገራልና!››፡፡ በተጨማሪም ትቷቸው ስለሞተ ልጆቹም ለሚመለከታቸው ቀሪዎች ‹‹አደራ›› የሚልበትና ተገቢውን መመሪያ የሚያስተላልፍበት አጋጣሚም ሊኾን ይችላል፡፡ 

አፈጻጸሙ፡- የሟች ቤተሰብ አንድ ቁና ገብስና የሚጫጫሱ (ልዩ መዓዛ ያላቸው) ነገሮችን ይዘው ወደ ኤኬራ ዱቢፍቱ ይሔዳሉ፡፡ ጠሪው/ዋ ገብሱን በእንቅብ አድርጎ በእጁ እያፈሰ ወዲያና ወዲህ በመበተን ዕፅዋቱን ያጫጭሳቸዋል፡፡[3] በዚሁ መሠረት የሟቹ ኤኬራ ‹‹ትመጣለች››፡፡ ከዚያ በኋላ በጠሪዋ አማካይነት ከቤተሰቦቿ ጋር ትነጋገራለች፡፡

መምጣቷ ደግሞ የሚረጋገጥባቸው ኹኔታዎች አሉ፡- ሟች በሕይወተ ሥጋ እያለ የሚጠቀምባቸውን ቁሳቁስ በመጠቆም፣ ይወዳቸው የነበሩ ምግቦችን በመጥራት፣ በተለይም ባልና ሚስት ብቻ በጋራ የሚያውቁትን ምሥጢር በምልክትነት ስትጠቁም ትክክለኛዋ የሟች ኤኬራ መገለጧን ኹሉም ያምናሉ፡፡   

አስቀድሞ እንደተገለጸው በዚህ ሥርዓት ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ባህላዊ እምነት ‹‹የሟቹ መንፈስ ተነስቶ/መጥቶ ይናገራል›› የሚለው ነው፡፡ ይህ እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ሲመዘን እውነትነት ያለው ይመስላል፤ የነቢዩ ሳሙኤልን ‹‹መንፈስ›› ታሪክ እናውቃለንና! (1ሳሙ.28፥3-19)፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቅዱስ መጽሐፍ ይህ ሊኖር እንደሚችል በሚያረጋግጥ መልኩ እስራኤል በእንዲህ ዓይነት ተግባር አምላካቸውን እንዳያሳዝኑት አስጠንቅቋል፡- ‹‹ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሒዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጓቸው...›› (ዘሌዋ.19፥31)፤ ‹‹በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም፣ በወፍም የሚያሟርት በአንተ ዘንድ አይገኝ›› (ዘዳ.18፥11) በማለት፡፡

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!

[1] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.185)፡፡

[2] ዝኒ ከማሁ (ገጽ.189)፡፡

[3] ዝኒ ከማሁ (ገጽ.184)፡፡ 



Report Page