EwnetMedia 2022
EwnetMedia
እውነት ሚዲያን በ ‹‹ኦሮሙማ›› ፖለቲካ መጠርጠር?
==================================
አንዳንዶች የእውነት ሚዲያን ማንነትና ዓላማ ካለመገንዘብ፣ በርካቶችም የጽሑፎቹን ሙሉ ሐሳብ ሳያነቡ አሉታዊ አስተያየቶችን ሲሰጡ አስተውለናል፡፡ በተለይም፥ ከወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካ ሴራ ጋር በማገናኘት፡- ‹‹ኦርቶዶክስን በኦሮሙማ አስተሳሰብ ልታጠምቁ ነው!›› በሚል የተጠራጠሩትን አስተውለናል፡፡ ‹‹ባለጊዜዎች እና ተረኞች ናችሁ!›› ብለው ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ኹሉ የአሁኑ ፖለቲካ ሥርዓት ተጠቃሚ እንደኾኑ አድርገው ለመፈረጅ የሞከሩትንም ታዝበናል፡፡ ‹‹ኦርቶዶክስ መስላችሁና ዙርያ ጥምጥም እየኸዳችሁ ባዕድ አምልኮን ወደ ቤተ ክርስቲያን ልታስገቡ ነው!›› በሚል ስኁት ድምዳሜ፥ ‹‹ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ግንኙነት አለው?›› የሚለውን መጽሐፋዊ ቃል ሊጠቅሱልን የሞከሩም አሉ፡፡

በመሠረቱ፥ እውነት ሚዲያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባለችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች ላይ እንድታተኩር ያደረጓት አንገብጋቢ ምክንያቶች ነበሩ፣ አሉም፡፡ በሌላው ክልል ተመሳሳይ ችግር የለም ተብሎ ባይታመንም፥ ኦርቶዶክስንና ኦርቶዶክሳውያንን ከኦሮሚያ ክልል ለማጽዳት እየተኬደበት ያለው ሴራ ግን ከኹሉ የከፋ ነው፡፡ በተለይ፥ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች (በ ‹‹ምሁርነት›› ስም የሚናገሩና የሚጽፉትን ጨምሮ) በቤተ ክርስቲያኗ ላይ በርካታ ክሶችን እየሰነዘሩ፣ የጥላቻ ትርክቶችን እየዘሩ የክልሉን ወጣቶች አእምሮ በርዘዋል፡፡ ክሶቹም ታሪክ-ነክ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ርዕዮተ-ዓለማዊና እምነት-ተኮር ናቸው፡፡
ከእነዚህ የትርክት ምድቦች መካከል ታሪክ-ነክና ፖለቲካዊ ለኾኑት ክሶች ‹‹ጊንጊልቻ›› በተባለ መጽሐፍ በመጠነኛ ዳሰሳ ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ በቀጣይ ትኩረታችን ደግሞ ማንነት (‹‹ኦሮሙማ›› የሚባለውን ጨምሮ)፣ ቋንቋ እና ባህል ከክርስትና አኳያ ምን አንድምታ እንዳላቸው ለመጠቆም እየተሞከረ ነው ((በመጽሐፍ መልክ እየተዘጋጀ ነው))፡፡ ይልቁንም፥ ‹‹ኦርቶዶክሳዊነት እና ኦሮሞነት ፈጽመው የማይገናኙ ማንነቶች ናቸው፤ ኦሮሞ የኾነ ሰው ኹሉ ‹ዋቄፈና› እምነትን እንጂ ኦርቶዶክስን መከተል የለበትም›› ለሚሉት አካላት የማያዳግም ምላሽ መስጠት አስፈልጓል፡፡ እንዲያውም፥ ነባሩ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በባህሉ እና በሥርዓተ-እምነታዊ ድርጊቶቹ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ-አምልኮ ጋር የሚመሳሰል (የተወራረሰ) መኾኑን በጥናት አስደግፎ ለማቅረብ እየተጣረ ነው፡፡
እናም፥ የተከበራችሁ የእውነት ሚዲያ አንባቢያን የሚከተሉትን ነጥቦች እንድትገነዘቡልን በትህትና እንጠይቃለን፡-
(1ኛ) በኦሮሚያ ክልል ያሉትን ኦርቶዶክሳውያን ከቤተ ክርስቲያናቸው ለማስኮብለል ለዘመናት የተደረጉና አሁንም እየተደረጉ ያሉ በርካታ የሐሰት ትርክቶችን ለማክሸፍ የሚቻለው በጥናትና ምርምር ላይ በተመረኮዙ ማስረጃዎች በመሞገት ብቻ ነው፡፡ እናም፥ የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያኗ እንግዳ እንዳልነበር የሚጠቁሙ በርካታ ፍንጮችን በጽሑፎቻችን ለማሳየት እየሞከርን ነው፡፡ ጉዳዮቹ ግን የ ‹‹ጥናት እና ምርምር›› አካል ተደርገው የሚወሰዱ እንጂ እንደ ‹‹ዶግማ›› የሚታመኑ አይደሉም፡፡ ‹‹የኦሮሞ ባህላዊ ድርጊቶች ኹሉ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ-እምነት ጋር አንድ ናቸው›› ወደሚል ድምዳሜም አያመሩም፡፡ ስለዚህም፥ መለወጥና ድርድር የሌለባቸውን ዶግማዊ ጉዳዮችን ሳይንሳዊ ጠባይ ካላቸው ጥናታዊ ግኚቶች ለይተን መገንዘብ ተገቢ ይኾናል፡፡
(2ኛ) እውነቱን ለመናገር፥ የኦሮሞን ሕዝብ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለመነጠል ለበርካታ ዘመናት፣ በተለያዩ አካላት የተሠራው ሴራ በቀላሉ የሚቀለበስ አይደለም፤ ሐሰቱ ተደጋግሞ ከመነገሩ የተነሣ ‹‹እውነት›› መስሎ በትውልዱ አእምሮ ተደላድሎ ተቀምጧልና፡፡ ከዚህ አኳያ፥ ቤተ ክርስቲያኗ ሁለት አማራጮች ይኖሯታል፡-
(ሀ) በኦሮሞ ሕዝብም ኾነ በሌላው ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ነባር አስተሳሰቦች እና የሚከወኑ ባህላዊ ድርጊቶች ኹሉ፥ ‹‹ከእምነቴና ሥርዓቴ ጋር ግንኙነት የላቸውም፤ ከፈለጉ ወደእኔ ይምጡ እንጂ እኔ ወደ እነርሱ መኼድ የለብኝም›› ብላ የራሷን ዶግማና ቀኖና ብቻ ማስተማር፤
(ለ) በማኅበረሰቦቹ አስተሳሰብ፣ እምነትና ባህላዊ ድርጊቶች ውስጥ፥ ‹‹ከእምነቴና ሥርዓተ-አምልኮዬ ጋር የሚዛመዱ ስላሉ ቀርቤ ላቅርባቸው›› የሚል ሐዋርያዊ ውሳኔ፡፡
የእውነት ሚዲያ አቋምና አቅጣጫ ሁለተኛው ምርጫ (‹‹ለ››) እንደሚሻል ነው፡- ኹሉንም ነገር ‹‹ባዕድ አምልኮ›› ብሎ ከመፈረጅና ከሕዝቡ ከመራቅ ይልቅ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና እስካልተጋፋ ድረስ ለመቅረብና ለማቅረብ መሞከሩ ለቀጣይ ሐዋርያዊ ተልእኮ ስኬት ያግዛል የሚል፡፡ ‹‹ሐዋርያ›› የሚለው ቃል በራሱ ‹‹ወደ ሕዝብ መኼድን›› እንጂ ሕዝቡ ወደ እኛ እንዲመጣ መጠበቅን የሚያመለክት አይደለም፡- ‹‹ወደ ዓለም ኹሉ ሒዱ….›› እንዲል (ማር.16፥15፤ ማቴ.28፥19)፡፡ ወደ ሕዝቡ መሔድ ደግሞ በእግር ብቻ ሳይኾን፥ እነርሱን ወደ ክርስትና ሊያቀርቡ በሚችሉ አስተሳሰቦች እና ድርጊቶች ጭምር መኾኑን ልብ ይሏል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- ‹‹እኔ ከኹሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እስባቸው ዘንድ እንደ ባሪያ ራሴን ለኹሉ አስገዛሁ፡፡ አይሁድን እጠቅማቸው ዘንድ ለአይሁድ እንደ አይሁዳዊ ኾንኹላቸው፤ ከኦሪት በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከኦሪት በታች እንዳለ ሰው ኾንኹላቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋሁ ሳልኾን፣ በክርስቶስ ሕግም ሳለሁ ሕግ የሌላቸውን እጠቅማቸው ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ኾንኹላቸው፡፡ ደካሞችንም እጠቅማቸው ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ኾንኹላቸው፤ በኹሉ መንገድ አንዳንዶቹን አድን ዘንድ ከኹሉ ጋር በኹሉ ነገር እንደ እነርሱ ኾንሁ፡፡ በወንጌልም ትምህርት አንድነት ይኖረኝ ዘንድ ስለ ወንጌል ትምህርት ኹሉን አደርጋለሁ፡፡›› ያለው ለዚህ ነው (1ቆሮ.9:19-23)፡፡ ወደ ሕዘቡ ለመቅረብ በምናደርጋቸው ጥረቶቻችን ኹሉ ግን ዋና ግባችንን (ነገረ ክርስቶስንና ድኅነተ ነፍስን) ልንዘነጋ እንደማይገባን ግልጽ ነው፡፡
(3ኛ) ለሐዋርያዊ ተልእኮ መሳካት ቁልፉ የምናገለግላቸውን ሕዝቦች ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ መልክዓ ምድር፣ አስተሳሰብ እና እምነት ማወቅ ነው፡፡ በተለይም፥ ከክርስትናው ይዘቶች ጋር የሚዛመዱ የማኅበረሰብ እሴቶች፣ እምነቶችና ድርጊቶች ሲኖሩ ‹‹አዲስ መሠረት›› ለመጣል ከመጋጋጥ ይልቅ እነዚህን እንደመነሻ (መንገድ ጠራጊነት) መጠቀም የምንፈልገው ግባችንን ስኬት ያሳልጥልናል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ እንደ ኦሮሞ ማኅበረሰብ ከክርስትናው (በተለይ ከኦሪቱ) እምነትና ሥርዓት ጋር ዝምድና ያለው የለም ቢባል ማጋነን አይኾንም፡፡
ምንም እንኳ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ እውነቱን ‹‹እውነት››፣ ሐሰቱን ‹‹ሐሰት›› የማለት አካሔዷ የነበረ፣ ያለና የሚኖር አቋሟ ቢኾንም፥ ‹‹ሐሰት›› እና ‹‹ባዕድ አምልኮ›› ተብለው በተፈረጁት ውስጥ መልካም ነገሮች ይኖሩ እንደሁ በጥናትና ምርምር መፈተሹ ግን ክፋት የለውም፡፡ ደግሞም፥ ዓላማችን ነፍሳትን ማዳን እስከኾነ ድረስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግሪክ/አቴና የተከተለውን ጥበብ መተግበር ተገቢ ነው፡- በመጀመሪያ፥ ምንና እንዴት እያመለኩ እንደኾነ በጥንቃቄ መረመረ፤ ቀጥሎ፥ ‹‹በእምነት የተሞሉ›› መኾናቸውን አደነቀ፤ ነገር ግን ደግሞ፥ የሔደበትን ነገረ-ክርስቶስ ሳይዘነጋ ‹‹ሳታውቁ የምታመልኩትን አምላክ እርሱን ስሙን ልነግራችሁ ነው የመጣሁት›› ብሎ በጥበብ ገባባቸው! (ሥራ.17:22-23)፡፡ ወቅሶ ሳያሸማቅቃቸው፣ ከነበሩበት አካሔድም ብዙም ሳያዛንፋቸው፥ ‹‹ዓላማውንና ይዘቱን ብቻ›› ቀይሮ ኮሽታ ሳያሰማ ጣዖታውያኑን ክርስቶሳውያን ያደረገበት ጥበቡ የሐዋርያዊ ተልእኮአችን መርሕ ነው፡፡ ሲጠቃለል፥ ወንጌል ልናስተምረውና ወደ መንግሥተ ሰማያት ልንመራው የምንፈልገውን ሕዝብ በአግባቡ እንወቅ፤ ነባር እሴቶቹንና ባህላዊ ድርጊቶቹን ኹሉ ‹‹ባዕድ አምልኮ›› ብለን ከማውገዝ በፊት ጥናትና ምርምር እናድርግ፤ ከዚያም አቧራውን አራግፈን በክርስትና አስተሳሰቦች እናጥምቃቸው!
(4ኛ) የኦሮሞን ሕዝብ ነባር ባህላዊ እሴቶችና እምነታዊ ድርጊቶች ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ጋር በማዛመድ ጥናታዊ ጽሑፎችን ስናቀርብላችሁ የነበርነውም አስቀድሞ በተገለጸው የሐዋርያዊ ተልእኮ አቅጣጫ መሠረት መኾኑን ልብ ይሏል፡፡ እውነት ሚዲያን፡- ‹‹የተረኝነት ፖለቲካ አራማጅ!››፣ ‹‹ኦርቶዶክስን በኦሮሙማ አስተሳሰብ ለማጥመቅ የምትሞክር!›› የሚሉ ክሶች የማይመጥኗትም ለዚሁ ነው፡፡ እንዲያውም፥ በጽንፈኛ ፖለቲከኞች፣ ‹‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እንቋቁማለን›› ባዮች እና አክራሪ ሙስሊሞች በቀንደኛ ጠላትነት ከተፈረጁት ኦርቶዶክሳዊ ሚዲያዎች እውነት ሚዲያ ቀዳሚዋ ናት፤ ለዚህም ምስክሮቿ እናንተው አንባቢያን ናችሁ!
እንደ እውነቱ፥ በቅን ኅሊና ለመረዳት ከሞከርን እና የጥናታዊ ጽሑፎቹን ኹኔታ ብናጤን አሁን ካለው የፖለቲካ ሥርዓት ጋር በጊዜም፣ በአስተሳሰብም፣ በዓላማም የማይገናኙ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ ‹‹ጊዜው የኦሮሞ ነው›› በሚል ፖለቲካዊ መነሻ ብቻ ኦሮሞ የኾኑትን ኹሉ መጥላት፣ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ የሚጻፉ ሐሳቦችን ማውገዝ፣ የክልሉንም ምእመናን ከኦርቶዶክሳዊነታቸው መግፋት በሰው ዘንድ የሚያስገምት፣ በእግዚአብሔር ፊት ደግሞ የሚያስፈርድ ተግባር ነው፡፡ ይልቁንም፥ ሳናውቅና ሳይታወቀን ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያንን ከቤተ ክርስቲያናቸው ለማስበርገግ ከሚሰሩት አካላት ጋር እንዳንተባበር ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል! የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠላቶች፡- ‹‹ኦሮሞ እና ኦርቶዶክስ ግንኙነት የላቸውም›› ሲሉ፥ እኛም ደግሞ፡- ‹‹እምነትን ከሌላ ባህላዊ ድርጊት ጋር ለማዛመድ አትሞክሩ›› የምንባባል ከኾንን የጠላቶቻችን ሕልም በተዘዋዋሪ እየተሳካ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ የእርስ በርስ መገፋፋት ድርጊታችን የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ይበልጥ እናወሳስባቸው ይኾናል እንጂ ልንቀርፋቸው ፈጽሞ አይቻለንም!
በአጠቃላይ፥ ቤተ ክርስቲያናችን በኦሮሚያ ክልል የገጠሟትን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ርዕዮተ- ዓለማዊና ሥርዓተ-እምነታዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ለክልሉ ምእመናን ብቻ መተው የለብንም፤ ኹላችንም የአንዱ አካል የክርስቶስ ልዩ ልዩ ብልቶች ነንና! ከምንም በላይ ደግሞ፥ በኦሮሚያ ክልል በመሰል ፖለቲካዊ እና ታሪክ-ነክ የሐሰት ትርክቶች እየተፈተኑ ላሉት ኦርቶዶክሳውያን ልናዝንላቸው፣ በጸሎት ልናግዛቸውና ኦርቶዶክሳዊ ኅብረታችንን ልንገልጽላቸው ይገባል! ይኸንን ማድረግ ባይቻለን እንኳ፥ እነርሱ ከአጽራረ-ቤተ ክርስቲያን ሴራ ለመትረፍና በሃይማኖታቸው ለመጽናት የሚያደርጉትን ተጋድሎ ከማደናቀፍ መቆጠብ፣ በወቅቱ ፖለቲካ ላይ ያለንን አቋምና ብስጭት በክልሉ ምእመናን ላይ እንዳንገልጽ የምንናገረውን፣ የምንጽፈውን፣ የምናደርገውንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል!!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
